አቡጊዳ – የአንድነት ፓርቲ ለዞን ዘጠኞች ያለውን አጋርነት ገለጸ

አንድነት ፓርቲ ትላንት ሚያዚያ 21 ቀን ባወጣዉ መግለጫ በዞን ዘጠኖች እና ጋዜጠኖች ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ተግባር አዉግዟል። አገዛዙ ሆን ብሎ በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ በተለይም ወጣቶችና የተማሩ እንዳይሳተፉ ለማስፈራራት ያደረገዉ እንደሆነ በመገልጽ እስረኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

«ፓርቲያችን ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ዞን 9 በተሰኘ ድረ ገጽ (ብሎግ) ላይ በሳል ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትችቶችን በማቅረብ ከሚታወቁትን ወጣት ጋዜጠኞች ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ዘላለም አጥናፍ ብርሀን፣ አቤል ዋበላ እንዲሁም ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ ጋዜጠኛ አስማመው ኃ/ጊዎርጊስ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚሸረሽር እንደሆነ እናምናለን፡፡ አፈናው ግን ሌሎችን በሺዎች የሚቆጠሩ ብሎገሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እንደሚፈጥር አንጠራጠርም» ሲል ያተተው የአንድነት መግለጫ መንግስት ዞን ዘጠኞችን በማሰሩ ሌሎች በሺሆች የሚቆጠሩ የሰባአዊ መብት ተሟጋቾችን የሚፈጠር እንደሆነ ገልጿል።

አንድነት በመግለጫ፣ ዘላቂው መፍትሄ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል አፋፍሞ መቀጠልና በሰላማዊ ትግል አምባገነኑን ስርኣት ማስወገድ ብቻ እንደሆነ አስምሮበታል።

የአንድነትን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !