የፍትህ ሳምንት እየተከበረ ፍትህ ስትሰቀል!!! ዳዊት ሰለሞን
በማዕከላዊ የሚገኙ የዞን ዘጠኝ አባላትን ከተፈቀደልን ለመጠየቅ ካልሆነም የታሰሩበትንና ፍርድ ቤት የሚቀርቡበትን ቀን ለማወቅ ወደ ስፍራው ዛሬ ማለዳ አምርተን ነበር፡፡የጦማርያኑ ቤተሰቦች ያመጡትን ምግብ ከማቀበል ውጪ ማንንም ሊያናግሩ እንደማይችሉ ተነግሯቸው በሐዘን እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
መቼ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ለሚለው ጥያቄም ኃላፊነት ወስዶ የሚናገር አካል በመጥፋቱ ማወቅ አልተቻለም፡፡ለምን ታሰሩ ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ ከተባለ‹‹ ተረጋጉ መስማታችሁ መቼ ይቀራል››ተብሏል፡፡
የበፍቃዱ ኃይሉ እናት መረጃ ለመጠየቅ በማለታቸው በተአምር ወደ ውስጥ እንዲዘልቁ ተፈቀደላቸው፡፡መረጃ ለመጠየቅ ያንን ባለጣውላ ደረጃ እየወጡ ከአንድ ቢሮ ፊት ለፊት ልጃቸው(አቡሽ በማለት ነው የሚጠሩት)ሁለት እጆቹ በካቴና ታስረው አገኙት፡፡በደስታ ተውጠው እላዩ ላይ በመጠምጠም በእናትነት ፍቅር ሳሙት፡፡በድንገት የቢሮው በር በመከፈቱ ግን ከዚህ በላይ ከበፍቄ ጋር መቆየት አልቻሉም፡፡
ጉዞ ወደ ፍርድ ቤት
ዞን ዘጠኞች እሁድ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል የሚል ወሬ ጆሯችን በመድረሱ ጊዩርጊስ ቤተክርስቲያንን ከፊት ለፊቱ ወደ ሚመለከተው አራዳ ፍርድ ቤት አመራን፡፡በመንገዱ ቁልቁል እየወረድን በአዲስ አበባ ፖሊስ ቅጥር ግቢ(በማዕከላዊ) ውስጥ ትልቅ ነጭ ድንኳን ተጥሎ አየን የድግስ አገር እያልን ጉዟችንን ስንቀጥል የፖሊስ የማርሽ ቡድን ሙዚቃውን እያስደመጠ አገኘን፡፡ምክንያቱ ምን ይሆን ስንል አረንጓዴ ኮፊያ ያጠለቁ ቦርጫቸው የከበዳቸው ብዙ ሰዎችን ተመለከትን አይ ቦርጭ ለጤንነት ጠንቅ መሆኑ ተደርሶበት እርምጃ ሊወሰድበት ይሆናል ከማለታችን ትልቅ ባነር የያዙ ፖሊሶችን አየን፡፡ባነሩ የፍትህ ሳምንት እየተከበረ መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡
ፍትህን የት ነበር የምናውቀው?ምናልባት ባነሩን የያዙት ፖሊሶች ፍትህ ሲሉና እኛ ፍትህ ስንል ካልተለያየ በስተቀር ‹‹ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በቤተሰቦቹ፣በወዳጆቹ፣በጠበቃው፣ በሐኪሙና በሐይማኖት አባቱ›› የመጎብኘት መብቱን ማግኘት ከሚለው የሚጀምር አይደለምን?ታዲያ ፖሊሶቹ አይናቸው ስር በሚገኘው የወንጀል ምርመራ እንዲህ አይነት የፍትህ እጦት እየተከሰተ የትኛውን ሳምንት ይሆን የሚያከብሩት?አጃኢብ አያሰኝም ትላላችሁ፡፡
በአራዳ ፍርድ ቤት የዞን ዘጠኝ ቤተሰቦች ቀድመውን ደርሰው ኖሮ ሁሉን አጣርተው ጠበቁን፡፡ዘጠኙን ወጣቶች በሶስት ምድብ በመክፈል ፖሊስ ክስ በማቅረብ ማንም ባልተገኘበት በትናንትናው ዕለት (በዕለተ እሁድ) ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ በመጠየቅ ለሚያዚያ 29 እና 30 እንዲያቀርባቸው መታዘዙን አረዱን፡፡ፖሊስ በእሁድ ቀንም ቢሆን ልጆቹን ፍርድ ቤት ማቅረቡ ጥሩ ሊሰኝ ቢችልም ቤተሰቦቻቸው ወይም የልጆቹ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሁሉ በተገኙበት በክፍት ችሎት ጉዳያቸው እንዳይታይ ማድረጉ አሳፋሪ ነው፡፡
ከዞን 9 ጦማርያን ጋር ከታሰሩት መካከል የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃ/ጊዩርጊስና በሶሻል ሚዲያ በተለይም በትዊተር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ያለ ፍርሃት ሐሳቧን ትገልጽ የነበረችው ኤዶም ካህሳይ ትገኝበታለች፡፡አስማማውና ኤዶም በኤፍ ኤም 96 አዲስ መዝናኛ የተሰኘ መረጃ ሰጪና አዝናኝ ፕሮግራም ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ኤዶም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር በመሆንም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የተመለከቱ ዘገባዎችን ትሰራ ነበር፡፡