ዴር ሡልጣን፡- ዐሥር ነገሮች(ክፍል አራት)
5. መዝየም
ኢትዮጵያውያን አባቶችና ምእመናን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለመፈጸምና መንፈሳዊ ርስትን ለትውልድ ለማኖር ታላቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህንን የዘመናት ተጋድሎ የሚያሳይ አንዳች ሙዝየም ግን የለንም፡፡ የገዳሞቻችንን ታሪክ፣ የተጻጻፍናቸውን ደብዳቤዎች፣ በየጊዜው ከሀገር ቤት የተላኩትን መጻሕፍትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ የዘመናቱን አሻራ የሚያሳዩ የሥዕልና የፎቶ ግራፍ መረጃዎች፣ ካርታዎች፣ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የከተቧቸው ማስረጃዎች፣ በየዘመናቱ የተሰጡ ስጦታዎችን የሚያሳዩ መዛግብት፣ የተሾሙ ራይሶችንና ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያሳዩ ዝርዝሮችና ፎቶዎች፣ የተሳላሚዎችን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎችና መዛግብት የተከማቹበት፤ ከዚያም አልፎ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣ ታሪክና ቅርሶች የሚያሳይ አንድ ታላቅ ሙዝየም በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ግቢ ውስጥ ወይም በአካባቢው ያስፈልገናል፡፡
ይህ ሙዝየም ሦስት ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የቅድስት ሀገር ርስታችንን ታሪክ በተጨባጭ የምናሳይበት፣ ከንግግር የዘለለ ማስረጃ እንዲኖረንና ያንንም ለዓለም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንድናሳይ ያደርገናል፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆንም የኢትዮጵያውያንን የተጋድሎ ታሪክ ለጎብኝዎች እናሳይበታለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሩሳሌም የመላው ዓለም አማኞች መናኸሪያ በመሆኗ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቂያ ወሳኝ መድረክ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንዋን በተለይ ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቋት የኢየሩሳሌም(በተለይም የዴር ሡልጣን) ገዳማት አባቶች ነበሩ፡፡
ሦስተኛ ደግሞ ለገዳሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ የዓመቱን ፋሲካ ጠብቆ ጧፍ ከመሸጥ ይልቅ ራቅ አድርጎ አስቦ ታሪካችንን የሚያሳዩ ፖስት ካርዶችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ ኢየሩሳሌም ገዳማት የተጻፉ መጻሕፍትን፣ የጎብኝዎች መመሪያዎችን(Tourist Guide)፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊት ያላቸው ቅዱሳት ሥዕላትን፣ የላንቲካ ዕቃዎችን(የሀገሪቱን ባሕል፣ የእምነት ሥርትዓቷንና ታሪኳን የሚያሳዩ ሰሐኖች፣ ቲሸርቶች፣ ኩባያዎች፣ የወግ ዕቃዎች፣ ጌጣ ጌጦች) ለቱሪስቶች በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ያስችላል፡፡
እስካሁን በታየው ልማዳችን ዕቃ ቤት እንጂ ሙዝየም በብዛት የለንም፡፡ በሀገር ቤት እንኳን ያሉን ሙዝየሞች ከታሪካችንና ከቅርሳችን ጋር ሲወዳደሩ ዓባይን በጭልፋ የሚያስብሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሙዝየም ብቻ ሳይሆን የጥናትና ምርምር ተቋማት ጭምር እንዳሏቸው የኢየሩሳሌም የቱሪዝም መሥሪያ ቤት የሚያሳትማቸው የቱሪስት መርጃ መጻሕፍት ያሳያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የቅርብ ዘመን ታሪክ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ቱሪስት እንደ ጎርፍ የሚፈስበት ሙዝየም አላቸው፡፡ ለተመራማሪዎችም ኢየሩሳሌምን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ፡፡
![]() |
|
የአርመን ሙዝየም ሕንጻ
|
ወደ ኢየሩሳሌም ምእመናንን የሚያጓጉዙ ተቋማት ከገዳማቱ አስተዳደር ጋር በመመካከር ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሙዝየሙ ጉዳይ ነው፡፡ ‹ታሪክ እንደ ነጋሪው ነው› በሚል ያረጀ ብሂል ስለ ራሳችን ታሪክ ለእኛ እንኳን የሚገርመንን ዓይነት ያልነበረ ታሪክ እንደነበረ እየተደረገ፣ የነበረውም እየተዘነጋ እየቀረበልን መሆኑን ካየን ለቱሪስቶችማ ምን ሊነገር እንደሚችል መገመት ነው፡፡
ይህንን ሙዝየም እንዴት ባለ መንገድ ልናቋቁመው፣ ልናካሂደው ምን ምን እንዲሠራ ልናደርገው እንደምንችል በሚገባ በዓይን ዓይቶ ለመረዳት በግሪክ ፍጥሞ ደሴት የሚገኘውን የቅዱስ ዮሐንስ ገዳም መጎብኘቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ያም ካልተቻለ በኢየሩሳሌም አሮጌው ከተማ የሚገኙትን የአርመንንና የግሪክን ፓትርያሪኬት ሙዝየሞች ማየቱ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡
6. ሴሚናሪ
ምንም እንኳን የገዳማቱ መነኮሳት የቀድሞ አባቶች ገዳሙን የጠበቁት ተምረው አይደለም ቢሉም አባባሉም ስሕተት ነው፣ ትምህርትም የግድ ነው፡፡ የቀድሞ አባቶች አልተማሩም የሚለው ብሂል ከሁለት ነገሮች የሚመነጭ ነው፡፡ አንድ ካለማወቅ ሁለትም ከንቀት፡፡ የቀድሞ አባቶች ለትምህርት ታላቅ ቦታ እንደነበራቸው ባከማቿቸው መጻሕፍት ብቻ እንኳን ማወቅ ይቻላል፡፡ እንኳን የክርስትና መጻሕፍት የአይሁድ፣ የግሪክ፣ የሂንዱስታንና የእስልምና መጻሕፍትን ሳይቀር ወደ ግእዝ እየተረጎሙ አስቀምጠውልናል፡፡ ተተኪዎቻቸው እንደነ እርሱ ዕውቀት ወዳጆች መስለዋቸው፡፡ ታላቁ ንጉሥና የዴር ሡልጣን ገዳም ባለ ውለታ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› በተሰኘው መጽሐፉ ‹‹እስመ ጽሙዐን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን – ምርጦቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው›› እንዳለው ኢትዮጵያውያን ትምህርትን የተጠሙና ለዕውቀት ማንኛውንም ዓይነት ዋጋ የሚከፍሉ ነበሩ፡፡
ዛሬ ባለው ዓለም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ቅኔ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ፣ ትርጓሜና አቋቋም እጅግ አስፈላጊዎች ቢሆኑም ብቻቸውን ግን ወንዝ ሊያሻግሩን አይችሉም፡፡ ዛሬ በልዩ ልዩ የሀገራችንና የዓለም ቋንቋዎች ማስተማርና መጻፍ የሚያስፈልግበት፣ ጥንታዊ ሀብታችንን በዘመናዊ መንገድ ማቅረብ የሚጠየቅበት፣ ሕዝቡን ለመድረስ ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን መጠቀም የግድ የሚልበት፣ ከትውልዱ ጋር ለመግባባትና የትውልዱን ጥያቄ ለመመለስ ሁለገብ ዕውቀት የሚያሻበት፣ ዘመን ነው፡፡
የኢየሩሳሌም ገዳማት አባቶችና እናቶች ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች የሠለጠኑ፣ በሚገባ የታጠቁና በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች እንዲሆኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ አንድም ‹‹መልክ ከእግዚአብሔር ሞያ ከጎረቤት›› ነውና ከጎረቤቶቻቸው ልምድ ለመቅሰም ስለሚችሉ፤ አንድም የትምህርት መርጃዎችን ከልዩ ልዩ ተቋማት ለማግኘት ቀላል ስለሆነ፤ አንድም በአንድ አካባቢ መኖራቸው በፈረቃ ለመማር ስለሚያስችላቸው፤ አንድም ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለመማር ኢየሩሳሌም አመቺ በመሆኗ፡፡ ሌላው ቀርቶ በሀገር ቤት የሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶቻችንንም ከኢየሩሳሌም ትምህርት ቤት ጋር በማቀናጀት የተሻሉ ለሚባሉ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ መስጠት ይቻላል፡፡
ዛሬ ዛሬ ከፍ አድርጎ ማሰብ እየጠፋ ነው መሰል የአባቶቻችን ሃሳብ አሜሪካና አውሮፓ መሄድ፣ ከግሪክ ንዋያተ ቅድሳት ማምጣት፣ ቤት መሥራት፣ ዘር መዝራት እየሆነ ነው፡፡ ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትፈልገኛለች፣ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጆች ሄጄ አስተምራለሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እተረጉማለሁ፣ ሕዝቡን በወንጌል እደርሳለሁ፤ የመነኮስኩበትን ገዳም ኑሮና አሠራር አሻሽላለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን በዓለም መድረክ አስጠራለሁ፣ ብሎ ከፍ አድርጎ የሚያስብ እያጣን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢየሩሳሌም መነኮሳት የነበራቸውን ቦታ ባለፈው ጊዜ በመጠኑ ጠቅሰነዋል፡፡ የኢትተጵያ ታላላቅ ገዳማት አባቶች አብዛኞቹ ኢየሩሳሌም መጥተዋል፡፡ እዚህ ያዩትንና የሰሙትን ይዘው በሀገራቸው ተግብረውታል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ንዋያተ ቅድሳትን ወደ ሀገር አምጥተዋል፡፡ ሌላው ቢቀር አፈሩንና የዮርዳኖስን ጠበል እየያዙ በመምጣት ከገዳሞቻቸው አፈርና ጠበል ጋር አዋሕደውታል፡፡ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉትም ምድራዊትና ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ከተመለከቱ በኋላ ‹ከመዝ ግበር› በተባሉት መሠረት የኢየሩሳሌምን አምሳል በሀገራቸው ሠርተዋል፡፡
ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም መነኮሳትና መነኮሳዪያት ብዙ ትጠብቃለች፡፡ በዕውቀት የበሰሉ፣ በቋንቋ የተካኑ፣ ዓለም ዐቀፋዊ ልምድ ያላቸው፣ በሁለት በኩል የተሳሉ ሆነው እንዲያገለግሏት፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሴሚናሪ ያስፈልጋል፡፡ የተቋሙን አመሠራረትና አሠራር ለመረዳት ከሌሎቹ ልምድ መቅሰም ነው፡፡ ወጭውን ለመሸፈን ደግሞ ምእመናን አንድም ሁለትም ተማሪ ስኮላርሺፕ እንዲሰጡ ማስረዳት ነው፡፡ ዛሬ ሰው ያጣንበት ዘመን ስለሆነ ሰው ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመርዳት ምእመናን ዝግጁ ናቸው፡፡ ብቻ የቆረጠ፣ የገባውና፣ ዓላማ ያለው ሰው ይኑረን እንጂ፡፡
አሁን አሁን በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ በብቃት ሊሳተፍ የሚችል ሰው እያጣን ነው፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የእምነት ውይይት (Inter – church dialogue) ይደረጋል፤ በልዩ ልዩ እምነቶች መካከልም ውይይት ይደረጋል(Inter – faith dialogue)፣ የአፍሪካና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ይደረጋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጉባኤ ይደረጋል፤ በሌሎች የዓለም መድረኮችም የሃይማኖት አባቶች ይጋበዛሉ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎም ሥራም ከግሪክ፣ ከዕብራይስጥ፣ ከላቲንና ዐረብ ጋር ማነጻጸር ይጠይቃል፤ ለዚህ ሁሉ ትምህርትና ሥልጠና ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢየሩሳሌም ላይ አንድ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሰው ሊያፈራ የሚችል፣ ሴሚናሪ ይኑረን የምለው፡፡
(ይቀጥላል)
ኢየሩሳሌም


