አቡጊዳ – ሚያዚያ 19 ቀን ለአንድነት ተከልክሎ ለሰማያዊ እንዲፈቀድ፣ ከከንቲባዉ ጽ/ቤት ዉጭ ባሉ፣ መመሪያ ተሰጠ ተባለ

ማንነታቸው ግልጽ ያልሆኑ የደህንነት ሰራተኞች፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ባስተላለፉት መመሪያ መሰረት፣ ሚያዚያ 19 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲያደርግ እውቅና ሊሰጥ እንደሆነ፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ያሉ ምንጮቻችን ገለጹ።

አስተዳደሩ ሚያዚያ 19 ቀን ሰልፉን ለማድረግ፣ አስቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ደብዳቤ ቢያስገባም፣ በዚያ ቀን ሌሎች ዝግጅቶች ስላሉ ለሚያዚያ 26 ቀን ለሰልፉ እውቅና እንደሚስጡ ባሳወቁት መሰረት፣ የአንድነት ፓርቲ ሰልፉን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንዳለ ይታወቃል።

አስተዳደሩ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ለሚያዚያ 19 ቀን እውቅና እንደማይሰጥ በመግለጽ ለሰማያዊ ፓርቲ ደብዳቤ የጻፋ ሲሆን በደብዳቤዉም ሰማያዊ ቀኑን እንዲያስተላለፍ መጠየቁ ይታወሳል።
ነገሮች በዚህ ሁኔታ እንዳሉ ፣ ድንገት ከከንቲባ ጽ/ቤት ዉጭ በመጣ ልዩ መመሪያ፣ የሰማያዊ ፖርቲ ሰልፍ እንዲያደርግ እውቅና እንዲሰጠው መታዘዙ፣ በአስተዳደሩ ዉስጥ ማን ነው ወሳኙ የሚል ዉዝግብ እንደጫረም ለማወቅ ችለናል። ለአንዱ ፓርቲ እየተከለከለ ለሌላው ፓርቲ መፈቀዱም፣ አገዛዙ ብልጠት ባለበት ሁኔታ፣ በተቃዋሚዎች መካከል እሳትን የበለጠ ለመጫር የሚያደርገዉን ስትራቴጂክ ሥራ የሚያሳይ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

እስከ አሁን የሰማያዊ ፓርቲ፣ ለሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ ገና በእጁ ያልያዘ ቢሆንም ፣ በአስተዳደሩና በደህንነት ሃላፊዎች መካከል የተፈጠረው ዉዝግብ ነገሩን በሌላ አቅጣጫ ካልወሰደው በስተቀር፣ ሰማያዊ የእውቅና ደብዳቤ በጥቂት ቀናት ዉስጥ ያገኛል ተብሎ ይጠብቃል።

በተያያዘ ዜና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ በሸገር ራዲዮ ቀርበው እንዲናገሩ የተደረገ ሲሆን፣ የሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ «ገዢው ፓርቲ ሳይወድ በግዱ ሰልፉን ይፈቅዳል» ሲሉ መደመጣቸውም ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ የአንድነት ፓርቲ ትእግስትና አስተዋይነትን አድንቀው፣ የአንድነት አመራሮች በሰማያዊ ፓርቲ በኩል ያለዉን ሁኔታ ለሕዝብ ትተዉ ፣ ስራቸው ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ይናገራሉ። «እርግጥ ነው ፍትሃዊነት የለም። ለአንዱ ተከልክሎ ለሌላው ሲፈቅድ በደል ነው እየደረሰ ያለው። ነገር ግን ሕዝብን የማደራጀት ሥራ ከፊታቸው ተቀምጦ፣ እኛ ተከልክለን ለምን ለሌላው ተፈቀደ የሚል ሙግት ዉስጥ በመግባት ጊዜና ጉልበት ማጥፋት አያስፈልግም። አገዛዙ ከፋፋይ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው» ሲሉ አንድነት ከፊቱ የተደቀነበትን መሰናክል በጥበብ እንዲሻገር አሳስበዋል።