የሚከራዩ አማት
(አማትና ምራት በአንድ ላይ የሚያነቡት)
አንድ ጊዜ አንዲት እናት ይህንን ታሪክ ነግረውኝ ነበር፡፡
እኔና ባለቤቴ የተጋባነው ልጆች ሆነን ነው፡፡ ያኔ እንዳሁኑ ተያይቶ፣ ተጠናንቶ፣ ሰንብቶ፣ ቆያይቶ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያውም የኛ ጊዜ ዘመናይ ነው ተብሎ የተወሰነ ጊዜ ትተያይና ወላጆቹ ለወላጆቿ ሽማግሌ ይልኩና፣ በስንት መመላለስ፣ አጥንትህ ጉልጥምትህ ተጠንቶ፣ ሀብት ንብረትህ ታይቶ ነበር የሚፈቀድልህ፡፡ ዛሬማ መንገድ ላይ ተንበርክኮ አንዲት የሃምሳ ብር አበባ ይዞ መለመን ነው አሉ፡፡ በኛ ዘመን በሬ ጎትተህ፣ መኪና አንጋግተህ፣ ጥሎሽ አግተልትለህም ከተሳካልህ ነው፡፡
ታድያ መጋባት አይቀርም ተጋባን፡፡ የእርሱ ወላጆች የሚያከራዩት ቤት ነበራቸው፡፡ አንዱን ቤት ሰጡንና ኑሮ ጀመርን፡፡ መቼም ፍቅርና ትዳር ለየቅል ነው፡፡ ታድያ እኛ ትዳር እንደጀመርን ባለቤቴ የልጅነት ነገር ሆነበትና ከጓደኞቹ እየተማረ ውኃ ቀጠነ ማለት ጀመረ፡፡ ባልነት ማለት መኮሳተር፣ መጎማለል፣ አንቺ እያሉ መጣራት፣ አምሽቶ መምጣት መሰለው፡፡ ይህን ጠባይ እርሱ እንዳላመጣው ዐውቅ ነበር፡፡ ጓደኞቹ ናቸው ያስተማሩት፡፡ በጊዜ ገብቶ አብረን ነበር ስንስቅና ስንጫወት የምናመሸው፡፡ እንዲያውም የኔ ባልኮ ዘመናይ ነው እያልኩ ነበር ለሰው የምናገረው፡፡ ወጥ ስሠራ እንኳን የሚያቀራርብልኝ እርሱ ነበር፡፡ በኋላ ጓደኞቹ ጠምደው ያዙት፡፡ ‹ለምን ቀሚስ አትለብስም› እያሉ መሳቂያ መሳለቂያ አደረጉት፡፡
የእነርሱን ወሬ መቋቋም ሲያቅተው እንደ እነርሱ ሆነ፡፡ ያገባሁትን ባል ወሰዱብኝና ሌላ ባል አጋቡኝ፡፡ አየህ ብዙ ሚስቶችኮ ባሎቻችንን ተነጥቀናል፡፡ እኛ ስናገባ ያገኘናቸውን ባሎች ወይ ጓደኞቻቸው ወይ ወላጆቻቸው ወይም ደግሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው ነጥቀውናል፡፡ ያላገባናቸውን ሌሎች ባሎችም አጋብተውናል፡፡ አንዳንዶቻችንኮ ከተፈራረምናቸው ባሎቻችን ውጭ ነው የምንኖረው፡፡ የኔም እንደዚያ ሆነልህ፡፡
ይህንን ሲተርኩልኝ ባልየው እያሳቁ ያዩናል፡፡ አማትዬው ደግሞ ‹‹መቼም አትረሽም አንቺ›› ይላሉ እርጅና እንኳን ብልቀነሰው ጆሯቸው እየሰሙን፡፡ እርሳቸውም ‹‹ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃል›› ብለው በባላቸው ተረቱና ቀጠሉ፡፡
ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ አምሽቶ መምጣት፣ ጠጥቶ መምጣት፣ የት እንደሄደ ሳይናገር ሶደሬና ላንጋኖ ጠፍቶ መክረም፤ የት ገባሽ የት ወጣሽ ማለት አመጣ፡፤ በእርሱ ቤት መቀናቱ ነው፡፡ ጓደኞቹ ሲያወሩ የሰማውን ሁሉ እውነት አደረገው፡፡ እኔም እየመረረኝም እየሰለቸኝም መጣ፡፡
የእርሱ እናት እንዴት ጥሩ ሰው መሰሉህ፡፡ ምናለ እንደርሳቸው ያለውን አማት እንደ ካሴት አባዝቶ በየቤቱ ቢያድሉት፡፡ በዚያ ዘመን እንደ አጤ ቴዎድሮስ ቀድመው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከቤታችን አይጠፉም፡፡ ምን ጎደለ? ምን ጠፋ? ነው ሐሳባቸው ሁሉ፡፡ በዚያ ዘመን አማት ልጅ ቤት የሚመጣው እንድም ሊያንጓጥጥ አንድም ሊያመናጭቅ ነው፡፡ አማት ሲባሉ ደርሰው መጥተው ሞያህን፣ ቤትህን ይገመግሙና ይዘረጥጡሃል፡፡ እርሳቸው እቴ፡፡ አንድ ቀን ክፉ ቃል ወጥቷቸው አያውቁም፡፡ ኧረ እንዲያውም ክፉ ቃል የሚባለውን ራሱን የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ የሚጨነቁት ለእኔ ነበር፡፡ ቁጭ ብለው ይመክሩኛል፣ ሞያ ያስተምሩኛል፣ ታሪክ ይተርኩልኛል፡፡ አቤት ቀልዳቸው፡፡ የባሌን ችግር የምረሳው በእርሳቸው ቀልድ ነበር፡፡ ከነገሩኝ በኋላ እንኳን ብዙ ጊዜ ብቻዬን እስቅ ነበር፡፡ ታድያ የቤቱን ችግር ነግሬያቸው አላወቅም፡፡ ለምን ይጨነቁ ብዬ፡፡
በኋላ ግን ባሰብኝ፡፡ ‹‹ቡችላው ሲጮህብሽ ዝም ካልሽው ውሻው ይነክስሻል›› ይባላል፡፡ ጭቅጭቁን ስታገሠው ጊዜ ዱላ ጀመረ፡፡ እርሱን ግን መቋቋም አቃተኝ፡፡ ሲብስብኝ ለእማማ ነገርኳቸው፡፡ አረሩ፣ ደበኑ፡፡ ምን አድርገሽው ነው እንኳን አላሉኝም፡፡ እስኪመጣ ድረስ አብረውኝ ቁጭ አሉ፡፡ አጅሬው አገር ሰላም ነው ብሎ ማታ ነበር የመጣው፡፡ እናቱን ይወዳቸዋልም ያከብራቸዋልም፡፡ ለእናት ለአባቱ አንድ ልጅ ነው፡፡ ከአባቱ ይልቅ እናቱን ነበር የሚፈራው፡፡ እርሳቸውን እንኳን ልጃቸው የሠፈር ሰው እንደ ንጉሥ ነው የሚያከብራቸው፡፡
ሲመጣ እሳት ጎርሰው እሳት ልሰው ጠበቁት፡፡ ‹‹አንተ ይህችን ትመስል ልጅ ያጋባንህኮ ተንከባክበህ፣ አክብረህ እንድትይዛት ነው፡፡ እንድትጫወትባት አይደለም፡፡ በእርሷ ላይ ነው ዱላ የምታነሳው፣ በእርሷ ላይ ነው አምሽተህ የምትመጣው፡፡ አየሁህኮ፣ በዓይኔ በብረቱ አየሁህ፡፡ ይህችን ትመስል ልጅ እንድታበላሽ አልፈቅድልህም፡፡ እኔ ጥሩ ሰው መስለህኝ ነበር የዳርኩልህ፡፡ ለካ እንደዚህ ሆነሃል፡፡ በይ ተነሽ፤ እኔ ምን የመሰለ ባል ፈልጌ እድርሻለሁ፡፡ ያዥ ልብስሽን›› አሉና ያን ጊዜ ሞባይል የለም በቤት ስልክ ለባላቸው ደወሉ፡፡ ባላቸው ፔጆ መኪናቸውን ይዘው መጡና ተነሥቼ ወደ አማቴ ቤት፡፡
እዚያ ስደርስ የእንግዳ ክፍል ተከፈተልኝ፤ ልብሴ ተጣጥፎ ተቀመጠልኝ፡፡ ‹‹አይዞሽ የኔ ልጅ፤ እርሱ የእኔ ልጅ አይደለም፡፡ ልጄ አንቺ ነሽ፡፡ እንኳን መምታት ዘወር ብሎ ሊያይሽ አይችልም›› ተባልኩ፡፡ መቼም የእርሳቸውን ነገር አውርቼ አልጠግበውምኮ፡፡ የእኔ እናት እንጂ የእርሱ እናት አይመስሉኝም፡፡ የእኔ እናትና አባትማ ናዝሬት ስለነበሩ እንዲህ በቶሎ መምጣት አይችሉም፡፡ እናቴም ‹‹ምን ከእኔ የበለጠ እናት አግኝተሻል፤ እኔ ምን አደርግልሻለሁ›› ነበር የምትለኝ፡፡
ባለቤቴ ጨነቀው፡፡ ምን ያድርግ፡፡ መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ነው የወረደበት፡፡ እናቱን ያውቃቸዋል፡፡ አይወስኑ እንጂ ከወሰኑ ማንም አይመልሳቸውም፡፡ እንደፎከሩት ለሌላ ቢድሯትስ ብሎ ፈራ፡፡ማን ተከራክሮ ይመልሳቸዋል፡፡ እንደ ዘንድሮ ባልና ሚስት ፍርድ ቤት መሄድ ያኔ አይታወቅ፡፡ ምን ያድርግ? ወስከንቢያው ነው የተደፋበት፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ የእርሱ ሽማግሌዎች የነበሩት ታላላቅ ሰዎች መጡ፡፡ እማማ እሽ ሊሉ ነው፡፡ ‹‹ልጄን እንዲያበላሽ አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ጓደኞቹ ካዋጡት ይዳሩት፡፡ እኔ የሚሳደብና የሚደባደብ ልጅ አልወለድኩም፤ አላሳደግኩም፡፡ ይቺን ትመስል ልጅ ብንድርለት በእርሱ ብሶ ሊማታ፡፡ የለም የለም፤ ልጄን እኔ ምን የመሰለ ጠባይ ከመልክ የተሰጠው ፈልጌ እድራታለሁ እንጂ እርሱማ አይጫወትባትም›› ብለው አሻፈረኝ አሉ፡፡ የእኔ እናት እንጂ የእርሱ እናት አይመስሉም ነበር፡፡ ሽማግሌዎቹም ተጠራጠሩ፡፡ እኛ ቤት የመጡ ነበር የመሰላቸው፡፡ እማማኮ ስለ ምራታቸው የሚያወሩ አይመስሉም፡፡
በሁለተኛው ሳምንት አጅሬ ለካ እናቴ ጋር ደውሏል፡፡ ስትሰማ ደነገጠች፡፡ ለአባቴ ነግራው ሲበሩ መጡ፡፡ ከቤት መውጣቴን ሰሙ፡፡ ደግሞ ወጥቼ የገባሁት አማቶቼ ጋ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ አቤት እማማ የሠሩት ሥራ፡፡ የእርሱ እናት እኔን አልሰጥም ብለው የእኔ እናትና አባት ለእርሱ አማላጅ ሆነው መጡ፡፡ ተገላበጠ፡፡ እማማ እንደ ባሕሉ አስተናገዱና ምን ልታዘዝ? አሉ፡፡ ‹‹ልጃችሁ ሽምግልና ልኮን ነው›› አሉ፡፡ እማማ አልሰጥም ብለው እምቢ አሉ፡፡
‹‹ምንም ብትወልዷት አልፈቅድላችሁም›› አሏቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲለምኑ ዋሉ፡፡ አባቴ ብልሃተኛ ነው፡፡ ‹‹እንጥራውና እዚሁ ዋስ ጠርቶ ቃል ይግባ›› አለ፡፡ እማማ ተስማሙ፡፡ ተጠርቶ መጣ፡፡ እየተንቀጠቀጠ ነበር የገባው፡፡ ወዳደገበት ቤት የሚገባ አይመስልም ነበር፡፡ ‹‹ሁለተኛ አንዳች ነገር አልናገራትም፣ እጄን አላነሣም፣ አላመሽም፣ አልጠጣም፣ ከቃሏ አልወጣም ብለህ ቃል ግባ›› አሉት እማማ፡፡ ቃል ገባ፡፡ ዋስ ጥራ ተባለ፡፡ ዋስ ማንን ቢጠራ ጥሩ ነው፤ የእኔን አባት፡፡ እዋሰዋለሁ አለ አባቴ፡፡ ‹‹በል ሁላችንምም ጉልበት ሳም›› አሉት እማማ፡፡ ሳመ፡፡ ‹‹አንድ ነገር ቢልሽ ደውይልኝ፤ ልጄን እወስዳታለሁ፡፡›› አሉ እማማ በማሠሪያው፡፡
እኔም ቤቴ ተመለስኩ፡፡ ኩሽ የለ፤ ዱሽ የለ፡፡ ሰላም፡፡ ጠባዩ ለወጥ ሲል ‹‹ለእማማ እደውላለሁ›› ነበር የምለው፡፡ እንዲህ ‹‹ለእማማ እደውላለሁ›› እያልኩ ይኼው ዐርባ ዓመት ኖርን፡፡ ስናስበው እንስቃለን፤ ለእኛ በሰላም መኖር ምክንያቱ እማማ ናቸው፡፡ ብዙ አማቶች ለልጃቸው አግዘው ከምራታቸው ጋር ነው የሚጣሉት፡፡ እንዲህ እንደርሳቸው ከዝምድና በላይ የሚያስብ አይገኝም፡፡ እናቴ ለእኔ በትረዳ ምን ይገርማል፡፡ አማቴ እናት ሲሆኑ ግን እንዲህ ትዳርን ያዘልቃል፡፡ እርሱማ ልጃቸው ነው፡፡ የት ይሄድባቸዋል፡፡ አሁን አሁን ነገሩ ሲነሣ ‹‹እማማ ግን እውነት ለሌላ ሊድሩኝ ነበር›› እላቸዋለሁ፡፡ ‹‹ባክሽ ላስፈራራው ብዬ ነው፡፡ ስቆርጥ ያውቀኝ የለ፡፡ ጉድ ትሠራኛለች ብሎ ነውኮ የፈራው፡፡ እናቱ ሚስቱን ወሰዱበት ቢባል እነዚህ ጓደኞቹ የሚለቁት ይመስልሻል?ጳውሎስ ኞኞ ነበር በጋዜጣ የሚያወጣው›› ይላሉ እየሳቁ፡፡
መከራየት እኒህን አማት ነበር፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው