አቡጊድ -የሰማያዊ ፓርቲ በዳግማይ ትንሳኤ ቀን ሚያዚይ 19 በአዲስ አበባ ሰልፍ ጠራ
የሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19 ቀን በአዲስ አበባ ሰልፍ እንደሚያደርግ አሳወቀ። ሰልፉ የሚደረግበት ቀን የዳግማይ ትንሳኤ ቀን ሲሆን፣ ለሰልፉ እውቅና ከአስተዳደሩ፣ ይገኝ አይገኝ ገና የታወቀ ነገር የለም።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ከአንድ አመት በፊት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ከአራት ኪሎ እስከ ጥቅር አንበሳ ጋር እስካለዉ ሃዉልት ድረስ፣ ሰልፍ እንዲያደርግ እውቅና መስጠቱ፣ ይታወቃል። ለሰማያዊ ተፈቅዶ በነበረበት ቦታ፣ መጋቢት 28 ቀን ሰልፍ ለማድረግ፣ አንድነት ቢያሳወቅም፣ አስተዳደሩ እውቃን አልሰጠም በሚል የዜጎችን ሕጋዊ መብት እንደረገጠ በስፋት የተዘገበ ነው።
ከብዙ ግፊት በኋላ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ በአዲስ አበባ ሚያዚያ 4 ቀን ሰልፍ እንዲያደርግ ከአስተዳደሩ እውቅና ያገኝ ቢሆንም፣ ቀኑ ቅዳሜ በመሆኑና ግማሽ ቀን ስለሚሰራ፣ አንድነት በፍቃዱ፣ ሰልፉን ለሚያዚያ 26 ቀን ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወቃል። ሚያዚያ 12 ቀን ፋሲካ/ትንሳኤ፣ በሳምንቱ ደግሞ ሚያዚያ 19 ቀን፣ ደግማይ ትንሳኤ በመሆኑ እነዚህን ቀናት ማሳለፉን የአመራር አባላቱ መርጠዋል።
ከሰልፉ ጋር በተገናኘ 4 የአንድነት አባላት የተደበደቡ ሲሆን፣ አምስት አባላት በአዲስ አበባ ሲቀሰቅሱ፣ ለሳምንት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መታሰራቸው ይታወቃል።
የሰማያዊ የሚያዚያ 19 ቀን እና የአንድነቱ የሚያዚያ 26 ቀን ሰልፎች ከተደረጉ፣ አዲስ አበባ፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ሁለት ሰልፎችን ታስተናግዳለች ማለት ነው።