የኛና የነሱ ኢትዮጲያ በናትናኤል ካብትይመር ከኦስሎ ኖርዌይ

እኛ የምናውቃት ኢትዮጲያ ከግማሽ በላይ ህዝቧ በመብራትና በውሃ እጦት የሚሰቃይባት ፣ በስልክና በኔትወርክ ችግር የሚማረርባት ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት አሳሩን የሚበላባት ፣ አብዛኛው ህዝቧ የዛሬን እንጂ የነገን ማቀድ የማይችልባት ፣ የተለያዩ ተንታኞችና አለማቀፍድርጅቶች “ችግር አለ” ብለው የሚያስጠነቅቋት ፣ ለዲሞክራሲ ፈር ቀዳጅ መሆን የሚገባው የፖለቲካ ስርዓት የሚያስፈራና ደም ደም የሚሸትባት፣ ብዙ ዜናና ትንታኔ ስለ አንዲት የመንግስት ፕሮጀክት ለአመታት የሚነገርባት ፣ ከአንዲት ፕሮጀክት ብዙ ሚሊዮን ብር በሙስና ተዘርፎ ጥቂቶችየሚከብሩባት ፣ መንግስት ተብየው ሃገርና ህዝብ ከማስተዳደር ይልቅ ስልጣኑን ለማደላደል ተግቶ የሚሰራባት ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቿንበየአመቱ በስደት የምታጣ ፣ ለቁጥር በሚታክቱ አሰቃቂ የመኪና አደጋዎች በየቀኑ ዜጎቿ የሚረግፉባት ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቿ በህክምናእጥረት በሞት የምትነጠቅ ፣ ችግሮቿ ለቁጥር የሚታክቱ ነገር ግን ኩሩ ታሪክ ያላት ጥቂት ሆዳሞች በፈጠሩት ችግር አንገቷን የደፋች ሃገር ናት።

እነሱ ግን ልክ እንደማናውቃት ሌላ ሃገር ኢኮኖሚዋ አለምን ባስገረመ መልኩ ለተከታታይ ብዙ አመታት የተመነደገባት ፣ የአለማችንመዓት ሃገራት የሚቀኑባትና ልምድ የሚቀስሙባት ናት ይሉናል። ለመሆኑ ይህች እነሱ የሚሏት ሃገር የት ነው ያለችው? ለምን ይሆን ስለገዛሃገራችን ከአመት አመት ልክ እንደማናውቃት በሞኝ ውሸት የሚሰብኩን?

ሃገራችን ችግር ላይ መሆንዋን ችግርዋም ከግዜ ወደ ግዜ እየተወሳሰበ ለመፍታት ወደሚያስቸግር ሂደት ውስጥ እየገባ መሄዱን የተለያዩምሁራን ፣ ፖለቲከኞች ፣ ተንታኞች እንዲሁም አለማቀፍ ድርጅቶች ሲወተውቱ በአንፃሩ ደግሞ መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል የዝሆንጆሮ ይስጠኝ እያለ ነው። ሁላችንም የምናውቀው አንድ እውነት ከጥቂት ሆዳሞች በስተቀር ኢትዮጲያዊ ሆኖ ሃገር እንድታድግለት የህዝቡም ኑሮእንዲሻሻልለት የማይፈልግ የለም። ነገር ግን መንግስት ተብየው የሃገራችንን ችግር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የባሰ እያወሳሰበውና ጭርሱንምእየሸፋፈነ ወደ መፍትሄ አልባነት እየገፋው ይገኛል። የችግሩንም መኖር የሚጠቁሙ ዜጎችና አለማቀፍ አካላት እንደመንግስት ተቀራርቦ መፍትሄከመፈለግ ይልቅ እንደሃገር ጠላት እየፈረጀ ይገኛል።

ሃገራችን ለዘመናት ለተጫናት ችግር የህወሃት መንግስት በጉልበት መመካት መፍትሄ ሳይሆን ሌላ ችግር ፈጣሪ መሆን ነው። ይህንንምመንግስት ተብየው በሚገባ ያውቀዋል። ነገር ግን ሃገር ወዳድነት ወደጎን ተብሎ በራስ ወዳድነትና አድር ባይነት ውድ ሃገራችን ኢትዮጲያ ወደአጓጉል ሁኔታ ውስጥ እየተገፋች ነው። ጥቂት ራስ ወዳዶችና በግለኝነት የተዋጡ ተራ ብልጣ ብልጦች ለሃገር እድገት ከመጣር ይልቅ አንዲት ነገርእየተቀባበሉና ቅርፅ እየቀያየሩ ትንታኔ በመስራት የማናቃት ኢትዮጲያ በመፍጠር ህዝባችንን የህልም ዳቦ እየበላህ ኑር እያሉት ነው።

የሃገራችን ህዝብ ከመቼውም ግዜ በበለጠ የለት ተለት ኑሮው እጅግ አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተይዟል። በመንግስትቴሌቪዥን የሚያይዋት ኢትዮጲያ የት እንዳለች አያውቁም። ደስተኝነት ከአብዛኛው ህዝባችን ርቋል። የሃገራችን ህዝብ በመንግስት ሚዲያየሚነገረው የህልም የኢኮኖሚ ትሩፋት የት እንዳለ አያውቅም። በዋና ከተማ እየኖረ የሚጠጣው ያጣን ህዝብ ፣ በዋና ከተማ እየኖረ ለወራትበመብራት እጦት ሳቢያ በሻማ ለሚኖር ህዝብ ፣ በትራንስፖርት እጦት እየተሰቃየ ለሚኖር ህዝብ ፣ በመኪና አደጋ ፍራቻ በሰቀቀን ውሎ ለሚገባህዝብ በጥቂት ሆድ አደር ብልጣ ብልጦች ስለ ሃገር ኢኮኖሚ መመንደግ ፣ ስለ ከተማ ውበትና ስለትራንስፖርት መትረፍረፍ ይነገራዋል።

ሃገራችን ችግር ላይ ነች። ይህን ማለት ችግር መፍጠር አይደለም። መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል የተሞላው በራስ ወዳዶች ፣ብልጣ ብልጦችና የህዝብ ብሶት በማይሰማቸው ሆዳም ግለሰቦች ነው። ይህንን የሃገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ማስወገድ የማንኛውም ሃገርወዳድ ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ሃገራችን ጭርሱን የማይፈታና ወደውሃላ የማይመለስ አደጋ ውስጥ ከገባች በውሃላ ጣት መጠቋቆሙ ከክፉፀፀት ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እኛም ሆነ እነሱ የምናወራው ስለ አንድ ሃገር ነው። ስለ ኢትዮጲያ። ኢትዮጲያን ከችግር የማውጣትግዴታ ያለብን ደግሞ እኛው ኢትዮጲያውያን ነን። አዎ ኢትዮጲያችን ከመቼውም ግዜ በላይ ችግር ላይ ነች።