በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ኅቡእ እንቅስቃሴ ተማሪውን የርስ በርስ ግጭት ወደሚያስገባ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

  • በቅ/ሲኖዶሱ በይፋ ከተወገዙና በኑፋቄ አራማጅነት ከሚጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋራ ግንኙነት ያላቸውና በኅቡእ በሚንቀሳቀሱ ጥቂት ተማሪዎች የሚራመድ ነው
  • ‹‹ችግሩን በዝምታ ለመመልከት ኅሊናችም ሃይማኖታችንም አይፈቅድልንም›› /ብዙኃኑ ደቀ መዛሙርትና የደቀ መዛሙርት ምክር ቤት አባላት
  • ለእምነትና ሥርዓት የሚቆረቆሩ መምህራንና ተማሪዎች ‹ማኅበረ ቅዱሳንና ፖሊቲከኞች ናችኹ› በሚል እንዲሸማቀቁ ይደረጋሉ

(ዕንቊ፤ ቅጽ ፮ ቁጥር ፻፲፬፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)

Enqu magazine logoየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በዘመናዊ አቀራረብ ከሚሰጡት ሦስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱና አንጋፋ በኾነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው የተባለ አስተምህሮ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ተማሪውን የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ወደሚያስገባ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኮሌጁ ምንጮች አስታወቁ፡፡

በቅ/ሲኖዶሱ በይፋ ከተወገዙና በኑፋቄ አራማጅነት ከሚጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋራ ግንኙነት እንዳላቸውና በኅቡእ በሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች የሚራመድ ነው የተባለው አስተምህሮ፣ በአስተዳደሩ ተመርምሮ አልያም በመድረክ ተጋልጦ እልባት እንዲሰጠው የደቀ መዛሙርቱ ም/ቤት በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለኮሌጁ አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳይሰጠው መቅረቱን የኮሌጁ ምንጮች ለዕንቊ መጽሔት ተናግረዋል፡፡

የም/ቤቱ አባላት ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ መመረጣቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ፣ አገልግሎታቸውን በቅንነትና በትጋት እንዲፈጽሙ ከፍተኛ ሓላፊነት ከተጣለባቸው አንዳንዶቹ ሃይማኖትን ለማጽናትና ለማስፋፋት ቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት መድባ አገልጋዮቿን በምታስተምርበት ተቋም ከአስተምህሮዋ ውጭ ኑፋቄ ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ የጋራ አቋም እንዳይደረስበት ይሠራሉ ብለዋል፤ ለእምነታቸውና ሥርዓታቸው የሚቆረቆሩ መምህራንና ተማሪዎችን ‹ማኅበረ ቅዱሳን›ና ‹ፖሊቲከኞች› እያሉ በተለያዩ ስልቶች በማሸማቀቅ ከሚታወቁት ችግር ፈጣሪ ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው የሚፈጽሟቸው ተግባራትም እንዳሳሰባቸው ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

ለኮሌጁ አስተዳደር ዲን ከኹለት ወራት በፊት የገባው ደብዳቤ ምላሽ ሳይሰጠው በመዘግየቱና የችግሩ አያያዝ በም/ቤቱ አባላት መካከል ሳይቀር የአቋም ልዩነት በመፍጠሩ ይህንኑ የሚያስረዳ ሌላ ደብዳቤ በዚሁ ሳምንት በኹለት የም/ቤቱ አባላት ለዋና ዲኑ ጽ/ቤት መቅረቡ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ችግሩን በዝምታ ለመመልከት ኅሊናችም ሃይማኖታችንም አይፈቅድልንም›› ማለታቸው የተጠቀሰው እኒኽ የም/ቤት አባላት፣ በአቋም ተለይተናቸዋል ያሏቸው የም/ቤቱ አባላት ከእንግዲኽ በም/ቤቱ ስም ለሚያስተላልፉት ማንኛውም ውሳኔ ሓላፊነት እንደማይወስዱ፣ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ አመዝኗል ያሉት ም/ቤትም ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርትም እንዲተካ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡