አቡጊዳ – የመኢአድ መሪ አቶ አበባዉ ዉህደቱን ላለመፈረም ያቀረቡት ምክንያት በቂ አይደለም ተባለ

የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባዉ መሃሪ በደብተራው ፓልቶክ ክፍል ቀርበዉ ባደረጉት ሰፊ ዉይይት፣ በመኢአድ እና በአንድነት መካከል ስላለዉ የዉህደት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። «አንድነቶች እኮ ልጆቻችን ናቸው። መኢአድ የነበሩ ናቸው» ያሉት አቶ አበባዉ በመኢአድ እና በአንድነት መካከል የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶች እንደሌሉ ተናገረዋል።

«ታዲያ የሁለቱም ፓርቲዎች ምክር ቤቶች ከወሰኑ በኋላ ምንድን ነው ምክንያቱ መኢአድ ለመፈረም ያልቻለው ? » በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አበባዉ ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል ሁለቲ ተደጋግመው ተገልጸዋል።

የመጀመሪያ የፓርቲዉን ስምን በተመለከተ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አበባዉ «አዲስ ስም ከሚሆን፣ መኢድም፣ አንድነት የሚታወቁ እንደመሆናቸው መኢአድ/አንድነት ይሁን ብለን ነበር፣ እነርሱ ግን በስሙ ንቅናቄ የሚል ቃል ይግባባት ብለዋል» ሲሉ ያልፈረሙበትን አንዱ ምክንያት አስረድተዋል።

«የዉህዱ ፓርቲ መሪዎች ሲመረጡ ፣ መመዘኛ መኖር አለበት» የሚል አቋም መኢአድ እንደያዘ የተናገሩት አቶ አበባዉ፣ በዚህም ጉዳይ አንድነት እንዳልተስማማ ተናግረዋል።

አሁንም የዉህደቱ እንቅስቃሴ እንዳልተቋረጠ የገለጹት አቶ አበባዉ «በሂደት ላይ ነው ያለነው፤ ትግል ነው፤ ተስፋ መቁረጥ የለብንም» ሲሉ በዜናዉ ያዘነዉን የክፍሉ ታዳሚ ለማረጋጋት ሞክረዋል።

የደብተራዉ ክፍል ታዳሚዎች የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደት አለመፈጸሙ እንዳሳዘናቸው እየደጋገሙ ገልጸዋል። የቀረቡት ምክንያቶች በጣም ቀላል እና ትንሽ እንደሆኑ የገለጹት አንዳንድ የክፍሉ ታዳሚዎች ፣ አቶ አበባዉ ያልገለጹት ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም ክፍሉ የአንድነት አመራርን አቅርቦ እንደሚያወያይም አሳዉቋል።

ከመኢአድ ጋር ለዉህደት የሚደረገው ድርድር ከሁለት አመታት በላይ እንደፈጀ ይታወቃል። «ለዚህ ታሪካዊና የሕዝብ ጥያቄ መደናቀፍ ምክንያቱ የመኢአድ ፕሬዘዳንት ሲሆኑ ይህን ሁኔታ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ለሁለቱ ፓርቲዎች አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በግል ተነሳሽነትና በሀገር ተቆርቋሪነት ስሜት ሁለቱን ፓርቲዎች ለማደራደር ሲደክሙ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችና ለሕዝቡ ጥሩ ዜና ባይሆንም ላለመፈረሙ ኃላፊነቱን የሚወስዱት የመኢአድ አመራሮች በተለይም ፕሬዘዳንቱ መሆናቸውን ማሳወቅ እንወዳለን» ሲል አንድነት ባወጣው መግለጫ የመኢአድ ሊቀመንበርን በዋናነት ተጠያቂ አድርጓል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ የመኢአድ ዉስጣዊ አሰራር ለዉህደቱ መጓተትና አለመሳካት አስተዋጾ እንዳለው ይናገራሉ። የድርጅቱ ላእላይ ምክር ቤት የወሰነዉን ሊቀመንበሩ ከቀለበሱ፣ በመኢአድ ዉስጥ ሊቀመንበሩ ከምክር ቤቱ በላይ ስልጣን እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሰራር ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ። በመኢአድ ዉስጥ የመኢአድ የበላይ ጠባቂ የሚባል አቶ ኃይሉ ሻዉል ያሉበት አካል እንዳለ የሚናገሩት እኝህ ተንታኝ፣ ይህ የመኢአድ የበላይ ጠባቂ በሊቀመንበሩ ላይ ግፊት አድርጎም ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።

«አንድነት ጉልበትና ጊዜ በዚህ ላይ መጨረስ የለበትም። ከመኢአድ ጋር ከሁለት አመታት በላይ ድርድር ተደረገ። ከዚያ በላይ መሄድ አያስፈልግም። መኢአዶች በዉስጣቸው ያለውን ችግር አስተካክለው ከመጡ እጅ ዘርግቶ ይቀበላቸው። አለዚያ ግን እነርሱን ማስታመም መቆም አለበት» ያሉት እኝህ ተንታኝ፣ ፓርቲው በሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ፣ በኑሮ ዉድነት ዙሪያ በአዲስ አበባ በሚደረግ የ«እሪታ» ሰልፍ፣ በምርጫ ዘምቻ ላይ እንዲያደርግና በመኢአድ ጉዳይ መጠመድ እንደሌለበት በመግለጽ አስተያየታቸውን ያቀርባሉ።

የአንድነት ፓርቲ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !