ሰንደቅ – አራት ምሁራን አንድነት እና መኢአድን እንዲዋሃዲ እያሸማገሉ ነው !

በመኢአድ ጽ/ቤት እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም የመኢአድ እና የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት በእነ ዶክተር ያእቆም ኃይለማሪያም፣ በዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አደራዳሪነት የተጀመረው የቅድመ የፓርቲዎች ውህደት ድርድር ውጪ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች የቀመሩት አይደለም ሲሉ ከአደራዳሪዎቹ አንዱ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለፁ።

ስማቸው አይጠቀስ ያሉ ዶክተር አሁን የያዙትን ኃላፊነት በምን መልኩ እንዳገኙት ለሰንደቅ እንደገለፁት፤ “እኛ ይህን ኃላፊነት የወሰድነው በራሳችን ተነሳሽነት እና በአንዳንድ ሰዎች ድርድሩን በሽምግልና ለምን አትገቡበትም የሚል ጥያቄዎች ስለቀረበልን ነው። በምርጫ አሸንፎ ለመውጣት በጋራ መስራት ተገቢ ነው ብለንም ስለምናምንም ጭምር ነው። ከዚህ ውጪ እኛ በራሳችን ተነስተን በእነሱ ላይ የምንጭነው ነገር የለም።”

“በውጭ ሀገር የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎችን ተልዕኮ ይዛችሁ በድርድሩ ላይ እንዲሁም ከፕሮፌሰር አስራት እስከ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ድረስ የነበረውን መኢአድ ቅርጽና ይዘት ለመለወጥ እንደምትሰሩ አንዳንድ ወገኖች እየገለፁ ነው። በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው” ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “እኔ የምዋሽበት አንድም ሁኔታ የለም። በተለይ ከውጭ ኃይሎች ጋር ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ከማናቸውም ጋር ግንኙነት የለኝም። እኛ የተነሳነው በሀገራችን ሰላም ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የአንድ አምባገነን ፓርቲ የበላይነት እንዲጠፋ፣ ተቃዋሚዎች በትብብር ሆነው ወይም በምርጫ ብቻቸውን ተሳትፈው ይህን ስርዓት እንዲለውጡ ወይም እንዲያስወግዱት ነው። በራሳቸው በፓርቲዎቹና በአንዳንድ ወገኖች ጥያቄ እንጂ ውጪ ይገኛሉ ከሚባለው ኃይሎች ጋር በፍፁም ግንኙነት የለንም። ዳኛቸውም ሆነ አቶ ይልማም ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት የላቸውም” ሲሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ ተከላክለዋል።

“ፖለቲካ ፓርቲዎች የያዙትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መስመር በሽምግልና መፍታት ይቻል ይሆን?” ብለን ላቀረብነው ጥያቄ ዶክተሩ የሰጡን ምላሽ፣ ፓርቲዎቹ በፕሮግራማቸው ተመሳሳይ ናቸው። በአባሎቻቸው ተመሳሳይ ናቸው። ሁለት ሆነው የሚኖሩበት በቂ ምክንያት የለም። በሁሉም ነገር ይመሳሰላሉ። በርዕዮተዓለም ሆነ በአስተሳሰብ አንድ ናቸው። በተናጠል መኖራቸው ለእኔ ትርጉም አልባ ነው” ብለዋል።

በመኢአድ ፓርቲ ፕሬዚዳንት በአቶ አበባው መሐሪ በኩል ውህደቱ ጥልቅ ውይይት አድርገን ብንፈጽመውና የተወሰነ ጊዜ ብንወስድ የተሻለ ነው። ሐሙስ የጥድፊያ እንዳይሆን የሚል ሃሳብ ቢሰነዝሩም፤ በዶክተሮቹ በተደረገ ጫና የግድ ከሐሙስ ማለፍ የለበትም በሚል ለሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም ቀን ተቆርጧል ሲሉ በስበሳባ ውስጥ የተካፈሉ አባላት ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ እንዴት ታለፈ ብለን ለዶክተሩ ጥያቄ አቅርበንላቸው፤ “እንደዚህ አይነት ቅሬታ አሁን ከእናንተ ነው የሰማሁት” ብለውናል።

በዚህ ነጥብ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የመኢአድ ፕሬዝደነት የሆኑት አቶ አበባው መሐሪን ደውለን አግኝተናቸው ነበር። ሆኖም እሳቸው፤ “በዚህ የውህደት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል። በዚህ ድርድር ላይ ፓርቲያቸውን
ወክሎ የሚደራደረውን ሰው ስልክ ቁጥር ደውለው እንደሚያገናኙን ቃል ገብተው ተለያየን። ሆኖም ደግመን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

የአንድነት እና የመኢአድ ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ በተካሄደው የድርድር ሂደት ላይ በአደራዳሪነት እየተሳተፉ የሚገኙት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አለማየሁ ረዳ እና አቶ ይልማ ይፍሩ ናቸው። ነገ ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በፓርቲዎቹ መካከል የቅድመ ፓርቲ ውህደት ፊርማ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።