የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር (ከሰንደቅ ጋዜጣ የተወሰደ)
በአዲስአበባ በተለይም በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓታት የሚታየው የትራንስፖርት ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ብቻም ሳይሆን ሠራተኞች በሰዓት ወደስራ ገበታቸው እንዳይገቡ በማድረግ በምርታማነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንዲሁም አብዛኛውን ሠራተኞች ላልተፈለገ ወጪ በመዳረግ የኑሮ ውድነትን በማባባስ ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ የሚታወቅ ነው። 
ከታክሲ የዞን ስምሪት አንስቶ ተጨማሪ አውቶብሶችን ወደመስመር በማስገባት በመንግስት በኩል የተደረጉ ጥረቶች
ቢኖሩም ችግሩን በአስተማማኝ መልኩ ለመፍታት ያስቻሉ አልነበሩም። በተለይ በአዲስ አበባ ከባቡር መስመር ዝርጋታና ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የታክሲ መስመሮች በመዘጋታቸውና በተለዋጭ መንገድ እንዲሄዱ በመገደዳቸው ብዙዎች ባለንብረቶች የራሳቸውን የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ ሕብረተሰቡን ላይ ተጨማሪ ወጪ አስከትለውበታል።
ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የቀላል ባቡር እና የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ማስፋፋት በቁልፍ ተግባርነት አስተዳደራቸው ይዞ እየሰራበት መሆኑን ያስረዳሉ። “ከባቡሩ መሠረተ ልማት በተጨማሪ የአንበሳ አውቶቡስ አቅም ለማሳደግና ሌሎች የከተማን የትራንስፖርት አቅርቦት አማራጮች ለማስፋፋት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከዓለም ባንክ በተገኘ የሙያ ድጋፍ በመታገዝ የተለያዩ ጥናቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።
በጥናቱም መሠረት አቅርቦትን ማሻሻል ብቻም ሳይሆን ከትራንስፖርት ጋር ተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመፍታት የትራንስፖርት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁመው የተለያዩና ተስፋ ሰጪ የሚባሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል። ከነዚህ መፍትሔዎች መካከል ጥቂቶቹ ፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት በግል ኩባንያዎች በኩል ማስፋፋት፣ ዘመናዊ የትራፊክ ኮርፖሬሽን ማዕከል መገንባት ፣የትራፊክ መብራት መትከልና ዘመናዊ ከተማ የትራንስፖርት አመራር አቅም ለመገንባት እንዲሁም ከመንገድ
ውጪ የፓርኪንግ አገልግሎት ማስፋፋት ወዘተ ሥራዎችን ለመስራት እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።