ፍኖት – የአዳማ/ናዝሬት ከተማ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ ወጣት ምርቱ ጉታ ታሰረ
በአዳማ/ ከተማ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ምርቱ ጉታ፣ ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 ገደማ በተለምዶ ዝቋላ ተብሎ በሚጠራው ገበያ አካባቢ መታሰሩን፣ የከተማዋ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ተስፋዬ ዋቅቶላ ለፍኖተ ነፃነት ገለፀ፡፡ 
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደገለፀው ዝቋላ ተብሎ በሚጠራው ገበያ አካባቢ የሚገኙ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ የገበያ ስፍራው እንዲለቁ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሲያሰሙ የነበረውን ብሶት እንደዜጋ ለማዳመጥ ከሞከሩ የአንድነት አባላት መካከል ወጣት ምርቱ ጉታን አስረውታል፡፡
ወጣት ምርቱ ጉታ በአሁኑ ሰዓት በአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወረዳ 4 ፖሊስ ጽ/ቤት ውስጥ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን፣ በአዳማ ከተማ የአንድነት ጽ/ቤት ለማሰራጨት የተዘጋጀውን በራሪ ወረቀትና “ግጥም ለነፃነት” በሚል መሪቃል፣ በአዳማ የአንድነት ጽ/ቤት በወሩ መጨረሻ ለሚዘጋጀው የኪነጥበብ ምሽት የተዘጋጀውን የፖስተር ንድፍ፣ በእጁ ይዞ በመገኘቱ፣ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑም ታውቋል፡፡
የአዳማ ከተማ የአንድነት ፓርቲ “ግጥም ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል በጽ/ቤቱ በወሩ መጨረሻ የሚያደርገውን የኪነጥበብ ምሽት የከተማው ተወላጅ ለሆነችውና በህገወጥ እስር ለምትገኘው ለርዕዮት አለሙ መታሰቢያ እንደተሰየመ የከተማዋ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ተስፋዬ ዋቅቶላ ለፍኖተ ነፃነት ጨምሮ ገልጧል፡፡