በመናፍቅነት የተከሰሱት የቪዝባደን ቅ/ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ «ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ ዛሬ በቋሚ ሲኖዶሱ ይታያል
- በአ/አ የሚገኙት ተከሳሹ ከፓትርያርኩ ጋራ በቅዳሴ እየተሳተፉ በመታየት ለማምታት እየሞከሩ ነው
- የግለሰቡን ኑፋቄ አስመልክቶ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተደጋጋሚ የተላኩ ማስረጃዎች ‹እንደጠፉ› ሲገለጽ መቆየቱ ተከሳሹ ከዓላማ ተባባሪዎቹ ጋራ የጥቅም መረብ ለመዘርጋቱ ማሳያ ኾኗል
- በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ?!
በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ የኾኑትና በመናፍቅነት አቤቱታ የቀረበባቸው የ«ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ ከበርካታ ዓመታት ያላሰለሰ የአካባቢው ምእመናን ተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ዛሬ ረቡዕ በቋሚ ሲኖዶሱ እንደሚታይ ተገለጹ፤ ተከሳሹም ከዚኹ ጉዳይ ጋራ በተያያዘ አዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ ሰሞኑን መታየታቸው ተጠቁሟል።
አቤቱታው የቀረበባቸው የደብሩ አስተዳዳሪ ለረጅም ዓመታት በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ ሲኾን ፥ በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሓላፊ በኾኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ፳፻፭ ባለጉዳዩ ይቅርታ መጠየቃቸውና ወደ ቀደመች ሃይማኖታቸው መመለሳቸው በዐውደ ምሕረት በግላጭ ተነግሮ በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአቡነ ዮሴፍን ዕውቅና ሳያገኝ ዛሬ ባሉበት ሓላፊነት ክህነታቸው ተመልሶላቸው እንዲቀመጡ ተደርጓል።
«ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ በፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ውስጥ በይፋ በነበሩበት ጊዜ ሁለት መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲኾን ሌሎች ሁለት ተጨማሪ መጻሕፍትን «ተመልሰዋል» ከተባሉ በኋላ መጻፋቸው ታውቋል። መጻሕፍቱ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የኾኑ የኑፋቄ ትምህርቶችን የያዙ ቢኾኑም ከልካይ ሳይኖራቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሚያስተዳድሩት አጥቢያና በአንዳንድ አድባራት ውስጥ በሽያጭ ሲሰራጩ ቆይተዋል።
‹‹ያላግባብ ክህነታቸው ተመልሶላቸዋል፥ የኑፋቄ ትምህርታቸውንም በቃል ከሚያስተምሩት ባሻገር ስሕተት በተሞላቸው የራሳቸው መጻሕፍትና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት ውጤት በኾነው በጮራ መጽሔት በኩል ምእመናንን እየበከሉ ነው፤›› በማለት ሕዝበ ክርስቲያኑ በተደጋጋሚ ከአካባቢው ሊቀ ካህናት አንሥቶ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድረስ በርካታ ደብዳቤዎችንና የምእመናን ፊርማዎችን አሰባስበው ሲልኩ ቆይተዋል። ይኹንና አቤቱታቸው ምላሽ ሳያገኝ ከሦስት ዓመታት በላይ ዘልቋል፤ ይህም ተከሣሹ በአስተዳዳሪነት ባሉበት ደብር ጥቂት የማይባሉ ምእመናንን ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ለማስኮብለል ኹኔታውን የተመቸ እንዳደረገላቸው ተጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን በጀርመን ሀገር ያደረጉት የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ፥ የምእመናኑን አቤቱታ ለሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የምእመናን አንድነት በኩል የቀረበላቸውን የጽሑፍ ፣ የምስል እና የድምፅ መረጃዎች በመያዝ ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት ጥያቄውን በደብዳቤ በማቅረብ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል። ብፁዕ አቡነ ሙሴ የምእመናኑን አቤቱታ በቀጥታ ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት በደብዳቤ ከማቅረባቸው በፊት የምእመናን አንድነቱ በተደጋጋሚ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሲልካቸው የነበሩ ደብዳቤዎች የውኃ ሽታ እየኾኑ ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል። በአውሮፓ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከልም ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ደብዳቤ ከማስረጃ ጋራ አያይዞ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት መላኩ ተገልጧል።
ይኹንና ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ በተደረገ ክትትል ደብዳቤው ከቤተ ክህነቱ እንደጠፋ ቢገለጽም ጠፋ የተባለው ደብዳቤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ባለው አፍራሽ ተልእኮው በሚታወቅ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ ላይ ወጥቶ ሊታይ ችሏል። የዋሃን ምእመናንን ለማሰናከልና የክሕደት እንክርዳድን ለመዝራት ዘወትር የሚታትረው ይኽው ብሎግ ደብዳቤውን ከማውጣቱም ባሻገር ከቪዝባደኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አለቃ ጋራ ያለውን የዓላማ አጋርነት ይህንኑ ደብዳቤ ይዞ በወጣው ዘገባ ርእስ «የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳደዱን ቀጥሏል» በማለት በግላጭ አሳይቷል።
ቀናዒ አገልጋዮችና ምእመናን የግለሰቡን ኑፋቄ ለመከላከል ካደረጓቸው ጥረቶች መካከል ‹‹መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ›› በሚል ርእስ በኅዳር ወር ፳፻፬ ዓ.ም. መ/ር ኅሩይ ኤርሚያስ ተከሳሹ ያለከልካይ በመጽሐፍ ላሰራጩት ኑፋቄ ምላሽ የሰጡበት መጽሐፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዓመታት የጀርመን ምእመናን ልቅሶና ጩኸት ሲሰማበት የነበረው የመናፍቁን «ቄስ» ጉዳይ የክርስቶስን መንጋ ከነጣቂ ተኩላዎች በበትረ መስቀላቸው እንዲጠብቋት እግዚአብሔር የሾማቸው ብፁዓን አባቶች በቅዱስነታቸው መሪነት ይኽን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንደሚሰጡት የመላው ምእመናን ጸሎት እና ምኞት ነው።
«አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።» (ግብ. ሐዋ.፳ ÷፳፰)
