2006 ዓ/ም የኢትዮጵያውያን የሰማእታት ዓለም አቀፍ አከባበር

የ2006 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሰማእታት ቀን በየካቲት ወር 12 ሐገሮች በሚገኙ በ27 ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከናውኗል። የአከባበሩም ስነሥርአት በሰላማዊ ሰልፍ፤ በሕዝባዊ ጉባኤ፤ ወይም በጸሎት ነበር። አዲስ አበባ የተከናወነው የካቲት 12 አደባባይ ሲሆን የአበባ ጉንጉን ኃውልቱ ሥር በማስቀመጥና ንግግር በማሰማት ነበር።

እንደሚታወቀው፤ የሰማእታት ቀን በየዓመቱ የሚከበረው፤ በየካቲት 19-21፣ 1929 ዓ/ም ፋሺሽቶች አዲስ አበባ በሶስት ቀኖች ውስጥ 30፣000 ሰው ጨፍጭፈው ስለ ነበር ነው። በተጨማሪም፤ በኢጣልያ አሰቃቂ የወረራ ዘመን አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችና 525000 ቤቶች ወድመዋል። ብዙ የኢትዮጵያ ንብረት ተዘርፎ አሁንም በቫቲካንና በኢጣልያን መንግሥቶች እጅ ይገኛል። እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ፤ ለዚህ ሁሉ ግፍ ኢትዮጵያ ተገቢውን ፍትሕ አለማግኘቷ ነው።

ክብረ በዓሉን በማዘጋጀት እንዲሁም በስነሥርዓቱ በመሳተፍ ለተባበሩት ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ ምሥጋናውንና አክብሮቱን በትሕትና ይገልጻል።
ክብረ በዓሉ የተከናወነባቸው ሐገሮችና ከተሞች፤ (1) በኢትዮጵያ (አዲስ አበባ)፤ (2) በአሜሪካ (ዋሺንግተን ዲ.ሲ፤ ኒው ዮርክ፤ ዳላስ፤ ሒዩስተን፤ አትላንታ፤ ሲያትል፤ ሎዛንጀለስ፤ ቦስተን፤ ታምፓ፤ ማያሚ፤ አውሮራና፤ ላስቬጋስ)፤ (3) ኢጣልያ (ሮም)፤ (4) ጀርመን (ኮሎኝ)፤ (5) ስዊድን (ስቶክሆልም)፤ (6) እሥራኤል (ኢየሩሳሌም፤ ቴል አቪቭ)፤ (7) አውስትራሊያ (አደሌይድ፤ ሲድኒ)፤ (8) ካናዳ (ቶሮንቶ፤ ቫንኩቨር)፤ (9) ታላቋ ብሪታኒያ (ለንደን)፤ (10) ደቡብ አፍሪካ (ጆሐንስበርግ፤ ፕሪቶሪያ)፤ (11) ስዊትዘርላንድ (ጅኒቫ)ና (12) ጃሜይካ (ኪንግስተን)።

የአንዳንድ ከተሞች የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች፤ በዓለም አቀፍ ሕብረት አማካኝነት የተዘጋጀውን አቤቱታ ለኢጣልያንና ለቫቲካን ኤምባሲዎች አቅርበዋል።
ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚታገልባቸው መሠረታዊ ዓላማዎች፤ (ሀ) ቫቲካን የፋሺሽቶች ተባባሪ ስለ ነበረች የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤ (ለ) ኢጣልያ ለፈጸመችው ግፍ ተገቢውን ካሣ እንድትከፍል፤ (ሐ) በይዞታቸው የሚገኘውን የተዘረፈ የኢትዮጵያ ንብረት ኢጣልያና ቫቲካን እንዲመልሱ፤ (መ) የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የፋሺሽት ግፍ በይፋ እውቅና እንዲሰጥና (ሠ) በቅርቡ የተመረቀው የግራዚያኒ ኃውልት እንዲወገድ ናቸው።

ኢትዮጵያ የሚገባትን ፍትሕ እንድታገኝ የሁላችንም ሕብረት አስፈላጊ ነው። ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ዓለም አቀፍ አቤቱታውን ለመፈረም www.globalallianceforethiopia.org መመልከት ይቻላል።

“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሀ ሐበ እግዚአብሔር”