ሰበር ዜና “ቀሲስ” ታደሰ ሲሳይ ስልጣነ ክህነታቸውን ተገፈፉ

 “ቀሲሲ” ታደሰ ሲሳይ ስልጣነ ክህነታቸውን ተገፈፉ  

ጽሁፉን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ።  አቶ ታደሰ ሲሳይ 

በአሌክሳንደሪያ፣ ቨርጂኒያ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተዳዳሪ የነበሩት “ቀሲስ” ታደሰ ሲሳይ በመባል ይታወቁ የነበሩት ግለሰብ ከዛሬ የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. (ማርች 9, 2014) አንስቶ የክህነት አገልግሎት ማከናወን እንደማችሉ የተወገዙ መሆኑንና በዚህም መሠረት ከአሁን በኋላ አቶ ታደሰ ሲሳይ ተብለው በተራ ስም እንደሚጠሩ ከስፍራው የደረሰን ሪፖርት ያመለክታል። አቶ ታደሰ ሲሳይ ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸውን ትዳር አፍርሰው ከህገ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ውጭ የክህነት አገልግሎት ሲፈጽሙ መገኘታቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ታደሰ ሲሳይ ለብዙ ዓመታት ከክህነት አገልግሎት፣ ተግባርና ሥነምግባር ውጭ የሆኑ ተግባራትን በመፈጸም ላይ በመሆናቸው ስሞታዎችና ተቃውሞዎች ሲሰነዘሩባቸው የቆየ ቢሆንም በማን አለብኝነትና በዕብሪት የክህነት አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ የቀጠሉበት መሆናቸውም ተጠቁሟል። ሆኖም በተደጋጋሚ ተመክረው ሊመለሱና ንስሃ ሊገቡ ባለመፈለጋቸው ምክንያት ለዛሬው ውግዘት መዳረጋቸው ታውቋል።

ውግዘቱን ያወጁት ካህናት የካንሳስ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፣ የዋሽንግተን ዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ማዕምራን ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሳዬና በቨርጂኒያ የአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ አባ ኃይለ ሚካኤል ተከለሃይማኖት ናቸው። የውግዘቱ ሥነ ሥርዓት በተካሄደበት ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ እንዲከታተል ከዚህ በፊት  የተቋቋመው ኮሚቴ አባላትና  ከተለየዩ አድባራት የመጡ  ምዕመናንም ተገኝተዋል።