የትግራይ ሕዝብ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ነዉ በሚለው ላይ የቀረበ አስተያየት – አብርሃ ደስታ
እስቲ በግልፅ እንነጋገር:
ለተጋሩ
==============
አንዳንድ ተቃዋሚዎች የትግራይን ህዝብ በህወሓት ዘመን የተለየ ጥቅም እንዳገኘ አስመስለው ሲያቀርቡ እንወቅሳቸዋለን። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በህወሓት ዘመን እንደተጠቀመ ሳይሆን እንደተጎዳ ጠንቅቀን እናውቃለንና። በሌላ በኩል ህወሓት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ እንደሆኑ ይሰብካል። ህዝብና ገዢ ፓርቲ በምንም ስሌት አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልፅ ነው። ፓርቲና ህዝብ አንድ አድርጎ የማሰብን ያህል ድንቁርና የለም። ግን ይሁን ብለን እንቀበለው። የህወሓት መሪዎች ስልጣናቸው በመጠቀም የኢትዮጵያን ሃብት እየመዘበሩ የራሳቸው ስርዓት ተጠቃሚ መሆናቸው ግልፅ ነው (ለዚህም ነው ስልጣን መልቀቅ የማይፈልጉ፤ ስልጣን ላለመልቀቅም ህዝብና ፓርቲ አንድ እንደሆኑ አድርገው ፕሮፓጋንዳ የሚሰሩ)።
እሺ:
ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ከሆኑ፣
ህወሓቶች በስርዓታቸው ተጠቃሚ ከሆኑ፣
የትግራይ ህዝብ የስርዓቱ ተጠቃሚ ነው ቢባል ለምን ይደንቀናል?
ምክንያቱም ህወሓቶች ተጠቃሚ መሆናቸው እናውቃለን። የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው ካልን የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ነው ልንል ነው ማለት ነው።
ስለዚህ የትግራይን ህዝብ ሁኔታ በቂ መረጃ የሌላቸው ተቃዋሚዎች የትግራይን ህዝብ በተለየ የስርዓቱ ተጠቃሚ ነው ብለው ቢደመድሙ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም መረጃው የሚያገኙት ከህወሓት ነው። ህወሓት የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ታድያ ተቃዋሚዎች የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ነው ቢሉ ችግሩ ምንድነው? ችግሩ ያለውኮ ህወሓቶች ጋ ነው። ህዝብና ፓርቲ አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ እየታወቀ አንድ ናቸው ይላል። ህወሓት “የኢትዮጵያ ሃብት እየዘረፍክ ነው!” ሲባል “አይ እኔ ብቻ አይደለሁም የምዘርፈው፣ የትግራይ ህዝብም አብሮኝ እየዘረፈ ነው፣ ከትግራይ ህዝብ ነጥላቹ አትዩኝ፣ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው …” ይለናል (የራሴ አገላለፅ መሆኑ ነው)። የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ከሆኑ ታድያ ህወሓቶች በተጠቀሙት ቁጥር የትግራይ ህዝብም ተጠቃሚ ነው ማለት ነው።
እኛ ተጋሩ ህዝብና ፓርቲ አንድ የሚያደርገውን ህወሓት የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳውን እንዲያስተካክል ማድረግ አለብን። የትግራይ ህዝብ በህወሓት ዘመን ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ መሆኑ ማስረዳት አለብን። ህዝብና ፓርቲ በየትኛውም መለክያ አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ ልናስረዳቸው ይገባል። የትግራይን ህዝብ ችግር በቅርበት የምናውቀው እኛ የትግራይ ሰዎች እስከሆንን ድረስ ችግሩን ማጋለጥ ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓት የትግራይን ሁኔታ አስመልክቶ በሚሰጠው የተሳሳተ መረጃ እንዳይታለል የበኩላችን ሚና መጫወት አለብን።
የትግራይን ህዝብ ድምፅ ማሰማት አለብን። ህዝብን ለመጨቆን ገዢዎችን መተባበር ሳይሆን ህዝብን ለመርዳት የሚደርስበትን ዓፈናና በደል ማጋለጥ ይኖርብናል። ህዝብ ለሚበድሉ ገዢዎችን መተባበር ከወላጆቻችን የወረስነው ባህላችን አይደለም። ባህላችን ለህዝብ ነፃነት ሲባል ጨቋኝ ገዢዎችን መታገል ነው። አሁንም ጠቃሚ ባህላችንን እንተግብር።