እየጠፋ ያለው የመጽሐፈ መነኮሳት ትምህርት ቤት
| ‹እኔ እንግዲህ የሚቻለኝን ደክሜያለሁ፤ ከዚህ በላይ ለማድረግ ዐቅሙም ዕውቀቱም የለኝም፡፡ ይህን ጉባኤ ቤት ደርቡሽ ፈተነው፣ መንግሥት ፈተነው፣ እሳት ፈተነው፣ ረሃብ ፈተነው፤ ይህንን ሁሉ ተቋቋመ፡፡ አሁን ግን እኔም አልፋለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱም ይዘጋል፡፡ ሁላችንም ታሪክ ሆነን እንቀራለን›› |
ጎንደር ከተማ በሄድኩ ጊዜ ሠለስቱ ምእት እየተባለ ወደሚጠራው አካባቢ ተጉዤ ነበረ፡፡ በዐፄ ቴዎፍሎስ (1700-1704 ዓም) ተሠርቶ በ1880 እና በ1881 ዓም በተደጋጋሚ በደርቡሽ ተቃጥሎ የጠፋውን የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ ለማየት፡፡ ይህ በአንድ ወቅት እንደ ኒቂያ 318 ሊቃውንት ተሰባስበው ይመክሩበት ነበር የሚባለው ዋናው የጉባኤ ቦታ ደርቡሽ ካፈረሰው በኋላ እንደገና ሳይሠሩ ከቀሩት የጎንደር አድባራት አንዱ ነው፡፡
ከዚሁ ፈርሶ ከቀረውና ዛሬ መጸዳጃ ቤት ከሆነው የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ አጠገብ በቆርቆሮ የታጠረ አንድ ግቢ አለ፡፡ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ ዳዋ የለበሰ ግቢና በጭቃና ቆርቆሮ የተሠሩ ሦስት አነስተኛ ክፍሎችን ታገኛላችሁ፡፡
እኔ በጥግ ወዳለው ክፍል ዘለቅኩ፡፡ አንድ ዓይነ ሥውር አረጋዊ አባት አልጋ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ቤቷ ጠባብና በዕቃዎች የተሞላች ናት፡፡ የመጽሐፈ መነኮሳቱ መምህር መጋቤ ምሥጢር ተሾመ ታደሰ ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ መጀመሪያ ረዳት መምህር ሆነው ከ1987 ዓም ጀምሮ አገልግለዋል፡፡ በ1991 ዓም ደግሞ ሙሉ መምህር ሆነው ጉባኤ ቤቱን ተረክበዋል፡፡
የ66 ዓመቱ መምህር የሚያስጨንቃቸው የሚበሉት ምግብና የደመወዛቸው ሁኔታ አይደለም፡፡ የመጽሐፈ መነኮሳቱ ጉባኤ ቤት እየጠፋ መምጣት ነው፡፡ በሀገራችን በመጥፋት ላይ ከሚገኙት ጥንታውያን ትምህርቶች አንዱ የመጽሐፈ መነኮሳት የትርጓሜ ትምህርት ነው፡፡ በዋናነት መነኮሳት እንዲመከሩበት የተጻፈውና የተተረጎመው፣ በሦስት ክፍል (ማር ይስሐቅ፣ አረጋዊ መንፈሳዊና ፊልክስዩስ) ይህ መጽሐፍ በጉባኤ ቤት የሚማረው እየጠፋ መጥቷል፡፡ በሀገራችን ለምንኩስና ሥነ ምግባር መበላሸት አንዱ ምክንያትም ይህንን የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥነ ምግባርና የእምነት መጽሐፍ ያልተማሩ፣ የስም መነኮሳት መብዛት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡
ይህን ትምህርት ቤት ታላቁ ሊቅ አለቃ አየለ (ዶክተር) በ1948 ዓም እንደገና እንዲያንሠራራ አድርገውት ለብዙ ዘመናት ቆይቶ ነበር፡፡ ቦታውን በተመለከተ የአካባቢው መስተዳድርና መምህራኑ እየተወዛገቡበት፣ ጉባኤው ግን ሳይታጠፍ ኖሯል፡፡ በ1988 ዓም ኅዳር 30 ቀን የአካባቢው መስተዳድር ቦታውን ለትምህርት ቤቱ ሰጠ፡፡ መምህሩና ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሲደሰቱ ግን ጉባኤ ቤቱ በ2004 ዓም የካቲት 7 ቀን በተነሣ እሳት ወደመ፡፡ በዚህ ቃጠሎ በ1714 ዓም የተጻፈ መጽሐፈ መነኮሳትን ጨምሮ አያሌ ቅርሶችና መጻሕፍት ወድመዋል፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ ችግር ላይ ወደቀ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በጭቃ እና በቆርቆሮ እነዚህን ሦስት ክፍሎች ሠሩ፡፡ ግቢውንም ዳዋ ዋጠው፡፡ ተማሪዎቹም ከምግብና ልብስ ችግራቸው ላይ የመጠለያ እጦትም ተጨመረበት፡፡ ውኃውን የማራኪ ግቢ ጉባኤ ልጆች አስገብተውላቸዋል፡፡ መብራት ግን የለም፡፡ አሁን አሥር ተማሪዎች ዳዋ ተንተርሰው እየኖሩ ጉባኤው እንዳይታጠፍ ይተጋሉ፡፡
መምህሩም እንዲህ አሉኝ ‹‹እኔ እንግዲህ የሚቻለኝን ደክሜያለሁ፤ ከዚህ በላይ ለማድረግ ዐቅሙም ዕውቀቱም የለኝም፡፡ ይህን ጉባኤ ቤት ደርቡሽ ፈተነው፣ መንግሥት ፈተነው፣ እሳት ፈተነው፣ ረሃብ ፈተነው፤ ይህንን ሁሉ ተቋቋመ፡፡ አሁን ግን እኔም አልፋለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱም ይዘጋል፡፡ ሁላችንም ታሪክ ሆነን እንቀራለን››
እንዲህ ያሉት ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ብዙ ሀገራዊ ጉዳት አላቸው፡፡ ከዘመን ዘመን የተጠራቀመ ዕውቀት፣ ታሪክ፣ ትውፊትና መረጃ ይጠፋል፡፡ ከሀገራዊ ማዕድ ውስጥም አንድ ዓይነት ይጎድላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የምንኩስና ሕይወትም ያለ ዕውቀት ይቀራል፡፡ የኔ ቢጤው ደግሞ በሰማይም በምድርም አይተህና ሰምተህ ታድያ ምን አደረግክ? ተብሎ ይወቀሳል፡፡
ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቢፈርስ ያመኑና ያወቁ አበውና ምእመናን ተባብረው አስበልጠው ያሠሩታል፡፡ ትምህርት ቤት ፈርሶ ትምህርቱና ሊቃውንቱ ከጠፉ ግን እንደገና መመለስ ከባድ ነው፡፡ እስኪ በየቦታው የተመሠረታችሁ በጎ አድራጊ ማኅበራትና ግለሰቦች የልባችሁ አጀንዳ አድርጉት፡፡