ቤተ መንግሥቱን የከበበው መስቀል የሃይማኖት መሪዎቹን አነጋገረ

  • ‹‹አገር የጋራ ነው ከተባለ በኋላ የጎደለ ነገር አለ››/ሼኽ ኪያር ሙሐመድ አማን/
  • ‹‹በታሪካዊነቱ ተከብሮ ተጠብቆ መኖር አለበት›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፴፭፤ ቅዳሜ፤ የካቲት ፰ ቀን ፳፻፮)

Lion of Juda, Imperial Symbol የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና መኖርያ ቤት በሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት አጥር – ዙሪያ ገባው ላይ የሚገኘው የመስቀል ቅርጽ የእስልምናና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖቶች መሪዎችን አነጋገረ፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሑድ በሐዋሳ ባካሔደው የምክክር መድረክ ላይ ‹‹አገሪቱና መንግሥቱ የእኩልነትና የዜጎች መንግሥት ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ሙሐመድ አማን÷ ከቀድሞው ሥርዐት ይልቅ አንጻር አኹን የሚያበረታቱ ነገሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ይኹንና በሴኩላሪዝምም ቢኾን ፍጹምነት ባለመኖሩ ‹‹አገር የጋራ ነው ከተባለ በኋላ የጎደለ ነገር አለ፤›› በሚል አዘውትረው ጥያቄ የሚያቀርቡላቸው ሰዎች መኖራቸውን ሸኽ ኪያር ጠቅሰዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይቀርቡልኛል ካሏቸው ጥያቄዎች መካከል ‹‹ለምሳሌ፡- ታላቁ ቤተ መንግሥት በመስቀል ነው የተከበበው፤ ይህ መጥፎ ነገር ሊያመለክት ይችላል፤›› የሚሏቸው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ታላቁ ቤተ መንግሥትን የከበበውን መስቀል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት እንደ ቆመው የደርግ ሐውልት ያህል እንዲታይ በሚል ለጥያቄው መልስ እንደሚሰጡ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ‹‹በአክሱም ግን አንዲት ጎጆ መስጊድ እንኳ ለመገንባት እንዴት አልቻልንም?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹የዚኽን ያህል የቀልድ መልስ ለመስጠት እንኳ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገሮችን ለማከም መቅደድ አለብን›› የሚል የዐረብኛ ብሂል እንዳለ በመጥቀስም ኹልጊዜ ጥላሸት መስለው ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ለመፍታትና መልስ ለመስጠት ይቻላል ወይስ አይቻልም ሲሉ በፈገግታ የታጀበ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

በጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ጥያቄ ላይ ፈጥነው አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሸኽ ኤልያስ ያቀረቧቸው ነገሮች ሌሎች ስለጠየቋቸው እንጂ ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ አምነውበት እንዳልኾነ ከንግግራቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

tsion_axumበጥያቄው ስለ መስቀልም ስለ አክሱምም መነሣቱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ሁለቱም የቆዩ ናቸው እንጂ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ‹‹በዚህ ግቢ (ስብሰባው በተካሔደበት ሌዊ ሪዞርት ማለታቸው ነው) ያየናቸው ዋርካዎች ድሮ የነበሩ ናቸው፤ አሁንም ይጠቅማሉ፤ ከቆረጥናቸው ጉዳት ነው፤ ከኖሩ ይጠቅሙናል፤›› በማለት የቆየው ታሪክ መጠበቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ቅርጽ የቆየ ታሪክ ነው፤ በታሪካዊነቱ ተከብሮ ተጠብቆ መኖር አለበት፤ በአክሱም ስላለው ነገር ከተነሣም የእኛም ጥያቄ ወደ ረጅምና ዝርዝር ነገር ይሔዳል፤›› በማለት የኹሉም ታሪክ በየራሱ መታወቅና መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መከባበርም  መቻቻልም እጅግ የሚፈለግ መኾኑን ፓትርያርኩ ገልጸው፣ አገሩ የኹላችንም ነው፤ የነበረው ታሪክ ደግሞ በታሪካዊነቱ ተከብሮ መኖር አለበት በሚል ለጠያቂዎቹ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል በፈገግታ የታጀበ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የውይይቱ ተሳታፊ ከኾኑ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም ይኹን የምክክር መድረኩን ከመሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ኹለቱ የሃይማኖት መሪዎች በተለዋወጡት ሐሳብ ላይ የተሰጠ ምላሽና አስተያየት አልነበረም፡፡MOURNERS GATHER OUTSIDE HOLY TRINITY CATHEDRAL FOR REBURIAL OF HAILE SELASSIE

የመስቀልና ዘውድ አምሳል በተቀረጹባቸው አጥሮች እንደተከበበ የተገለጸው ታላቁ ቤተ መንግሥት የምኒልክ ቤተ መንግሥት በሚለው መጠሪያው የሚታወቅ ሲኾን ንጉሡ በ1878 ዓ.ም ያሠሩት መንበረ መንግሥታቸው ነበር፡፡ የተለያዩ መኖርያ ቤቶችን፣ የግብር ቤቶችንና እልፍኞችን እንዲኹም ቤተ ጸሎቶችን ያካተተው ቤተ መንግሥቱ÷ የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም፣ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንና የሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ይዋሰኑታል፡፡800px-Menelik_II_Mausoleum

በተለይ የዘውድ አምሳል በጉልላቱ ላይ ያነበረው የበኣታ ለማርያም ገዳም የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣ የንግሥታቱ እቴጌ ጣዪቱና ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲኹም የልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴና የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ዘግብጽ ዐፅሞች ያረፉበት ሲኾን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና መኖርያ የኾነው ከደርግ መንግሥት ጀምሮ ነው፡፡

ለሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች መነጋገርያ የኾነው ጉዳይ መነሻ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖሊቲካ ሳይንስ የግጭትና ሰላም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር በኾኑት ዶክተር ታረቀኝ አዴቦ ‹‹በአገራችን የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች በሰላም አብሮ የመኖር ወርቃማ ተሞክሮና የማስቀጠል ፋይዳው›› በሚል ርእስ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ነው፡፡

የአገራችን ሕዝቦች ‹‹እንኳን በብርሃን ዘመን በጨለማው ዘመንም ጭምር›› የሃይማኖት ብዝሐነትን በመሠረቱ ያለመግባባትና የግጭት መነሻ ሳያደርጉ በሰላም አብረው እንደኖሩ የሚያትተው ጽሑፉ፣ በሰላም አብሮ መኖር÷ ብዝሐነትን እንደ ነባራዊ ኹኔታ የመቀበል፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልት የመከተል፣ የብዝሐነቶች ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት አስተሳሰቦች ጥምረት መኾኑን ይገልጻል፡፡

የሃይማኖት መሪዎች በሰላም አብሮ የመኖር አርኣያ በመኾን ከቅድመ አያቶች ጀምሮ ለዘመናት የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴት በውስጣቸውም ይኹን በመካከላቸው አስተሳሰቡንና ተግባሩን በማስፈን ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራና የዜግነት ግዴታ እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፣ ያለፈውን ታሪካዊ እውነታ ተቀብሎና ዕውቅና ሰጥቶ፣ የወቅቱን ነባራዊ ኹኔታ መሠረት አድርጎ ወደፊት በመቃኘት በአገራችን ብዝሐነትን ተቀብሎ በተገቢው ኹኔታ ለማስተናገድ አቅጣጫ ያስቀመጠ ብቸኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው የሚሉት ሌሎች የጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች÷ መንግሥታዊ ሃይማኖትን ከሠየመው የንጉሣዊው ሥርዐት ሕገ መንግሥትና ፀረ ኹሉ ነበረ ከሚሉት የወታደራዊ ሥርዐት ሕገ መንግሥት በመለየት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ያስቀመጣቸውን መርሖዎችና ድንጋጌዎች ዘርዝረዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ለተከታዮቻቸው የማስተማር ሓላፊነታቸውን በተጠናከረ መልኩ መወጣት ይኖርባቸዋል ያሉት ጽሑፍ አቅራቢዎቹ፣ የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና ሠራተኞችም ሴኩላሪዝምንና ሃይማኖት ነክ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በጥብቅ በመተግበር መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መኾናቸውን ያረጋገጠውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡