አማኑኤል ዘሰላም – «ታላቁ መሪያችን» የመዘበሩት ቢመለስ በርካታ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወጪ ይዘጋ ነበር
አቶ ወልደስላሴ በሕወሃት ተመድበው የጉምሩክ ምክትል ሃላፊ ነበሩ። ስራ ሲጀምሩ ደሞዛቸው 1600 ብር ነበር። በእድገት ደሞዛቸው ወደ 6000 ብር ይወጣል። እንዴት እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ ባለ 4 ፎቅ ህንጻ ባለቤት ሆነዋል። ወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ወልደስላሴ፣ ደሞዛቸው 532 ብር ነበር። ነገር ግን በግል የባንክ አካዉንታቸው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል። በአፋር ክልል ከ 1 ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ በር በላይ በሆነ ወጭ የእርሻ ኢንቨስትመንትም አላቸው። ይሄ ሁሉ ሃብት ከየት ተገኘ ? አጭር መልስ ሌብነትና ሙስና !!!!

አቶ ወልደስላሴ የጸረ-ሙስና ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል በቁጥጠር ስር አዉሏቸዋል። ይህ አይነቱን በስልጣን የመባለግና ሃብትን በማጭበርበር የማከማቸት እኩይ ተግባራት ላይ፣ የመንግስት የሕግ አካላት ሲነሱ ማየት በጣም የሚያስደስትና ጥሩ ጅማሬ ቢሆንም ዘልቆ ግን ሊሄድ አልቻለም። አቶ ወልደስላሴ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የመዘበሩት ግን ሌሎች ከፍተኛ የአገዝዙ ባለስልጣናት ጋር ሲወዳደር፣ እዚህ ግባ የማይባል ነዉ።እንግዲህ ሙስናን ከተዋጉ አይቀርም በአፍና ትናንሽ ጥንቸሎች ላይ ብቻ በመዝመት ሳይሆን ቱባ ቱባ መዝባሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋል አለባቸው። በሕይወትም ከሌሎች በሕግ ከሕዝብ የሰረቁት ገንዘብ እንዲመለስ መድረግ አለበት።
አንድ ምሳሌ ላቀርብ። አንድ ገለልተኛ፣ «ዘ ሪቸስት» የሚባል፣ በአለም ያሉ ሃብታሞችን የሚዘረዝር ድርጅት አለ። ይህ ድርጅት በድህረ ገጹ ላይ፣ በሁሉ መስክ ያሉ የተላያዩ ሃብታሞችን ስም ፣ ምን ያህል የገንዘብ ሃብት እንዳላቸው ያስቀመጣል። በነገራችን ላይ ይህ ድህረ ገጽ ከኢትዮጵያዉያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው፣ ከፖለቲክ ነጻ የሆነ ድርጅት ነዉ።
ያዉ እንደ ሚታወቀ ቢል ጌት አንደኛ ነዉ። 77.1 ቢሊዮን ዶላር አለው። በሁለተኛነት አምባገነኑ ቭላዲሚር ፑቲን ተቀምጧል (77 ቢሊዮን ዶላር)። ያዉ ስልጣኑን ተጥቅሞ ዘርፎ እንደሆነ ይታወቃል። የቀድሞ የኒዉዮርኩ ከንቲባ፣ ማይክል ብሉምበርግ 21ኛ ናቸው ( 31.2 ቢሊዮን) ። የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች 76ኛ ነዉ ( 13.6 ቢሊዮን)። የኛዉ ግማሽ ወሎዬው ሼክ ሞሃመድ አላ አሙዲ 85ኛነዉ። ( 12.5 ቢሊዮን)። የኤሲ ሚላን እግር ኳስ ክለብ ባለቤትና የቀድሞ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሲልቪዮ ቤሎርስኮኒ 195ኛ ናቸው። ( 6.2 ቢሊዮን) ። እንግዲህ የሃባታሞቹ ዝርዝር እንዲህ እያለ ይወርዳል።
የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዘዳነት ቢል ክሊንተር ፣ 80 ሚሊዮን (አስቡት ቢሊዮን አይደለም) ፣ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቶኒ ብሌር 30 ሚሊዮን ፣ የአሁኑ የእንግሊዘ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሮን 6 ሚሊዮን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአዉስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት ጁሊያ ጂላርድ 2 ሚሊዮን ፣ የካናዳዉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስቲቭን ሃርፐር 2 ሚሊዮን ፣ ዝነኛዉ የእግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሶሲ 115 ሚሊዮን እና የራሷ የቴሌቭዥን ጣቢያ በአሜሪካ ያላት ኦፕራ ዊንፍሪ ደግሞ 2.9 ቢሊዮን የሚጠጋ ሃብት አላቸው።
የኛው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ከ1995 እስከ 2010 ያገኙት ደሞዝ 220 ዶላር በአመት፣ በጥቅሉ $2640 መሆኑን «ዘ ሪቸስት» በድህረ ገጹ ቢገልጽም፣ የአቶ መለስ ዜናዊ ሃብት ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ግን ያስቀምጣል። የሃብታቸውም ምንጭ ሲገልጽ «ፖለቲካ»፡ እንደሆነ ይነግረናል።
ቁጭ ብዬ አስብኩ። ከቢል ክሊንተን፣ ቶኒ ብሌር፣ ዴቪድ ካሜሮን ፣ ጁሊያ ጂላርድ የመሳሰሉ የታላላቅ መንግስታት መሪዎች ከሰሩት የተለየ ፣ የፖለቲክ ቢዝነስ ምን ሊኖር ይችላል፣ አቶ መለስን እንደዚህ ቱጃር ያደረጋቸው ?
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፣ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ለምን ቴሌኮሚኒኬሽንን ለግል ኩባንያዎች እንደማይሰጡ ሲገልጹ፣ «የባቡር ግንባታዉን እያደረግን ያለነው ከቴሌ በሚገኘው ገንዘብ ስለሆነ ፣ ቴሌን መልቀቀ አንፈልግም» የሚል እድምታ ያለው አስተያየት ነበር ያቀረቡት።
በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው የመለስተኛ ባቡር ፕሮጀክት አጣቃላይ ወጭዉ 475 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነዉ። ከሰበታ -አዲስ አበባ – አዳማ የሚደርሰው ፣ ወደ መቶ ኪሎሜትር የሚሆን ድርብ የባቡር መስመር (ደብል ትራክ) ለመገንባት ፣ ከዚያም አዋሽን አልፎ እስከ ሚየሶ የሚደርሰዉን የባቡር መስመር በኤሌትሪክ እንዲሰራ ተደርጎ ለማደስ የሚያሰፍልገው ወጭ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ነዉ። ከመዪሶ ፣ ድሬደዋን አልፎ ጅቡቲ ጠረፍ የሚደርሰዉን መስመር ለማደስ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ለነዚህ ሶስት ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገዉን ወጭዎች ብንደምራቸው፣ ሶስት ቢሊዮን ሰባ አምስት ሺህ ዶላር ይደርሳል።
«ታላቁ መሪያችን» አቶ መለስ ዜናዊ ከሕዝብ የዘረፉት ገንዘን ምንም አይነት ብድር ሳንወስድን እነዚህን ሶስት የባቡር ሃዲዶች ይገነባልን ነበር።
አቶ ኃይልማሪያም ደሳለኝ ፣ ባቡር ለመስራት በሚል ቴሌን ከሚገድሉ ፣ «ታላቁ መሪያችን» ሶስ ቢሊዮን የሚጠጋ ሃብት እንዴት እንዳገኙ ቢጠይቁ ጥሩ ሊሆን ይችል ነበር። እርሳቸው በየስብሰባዉና ቃለ መጠይቁ የሚክቧቸው አቶ መለስ፣ ላይበሉት፣ ከድሃዉ ሕዝብ የሰረቁት ገንዘብ እንደሆነ ይረዱ ነበር። ከሕዝብ የተመዘበረዉን ገንዘብ የማስመለስ ሥራ ቢሰሩ ለአገር የሚጠቅም ሥራ የሰሩ ነበር። «ታላቁ መሪያችን» አቶ መለስ ዜናዊ ከሕዝብ የዘረፉት ገንዘን ምንም አይነት ብድር ሳንወስድን እነዚህን ሶስት የባቡር ሃዲዶች ይገነባልን ነበር።
http://www.therichest.com/celebnetworth/politician/minister/meles-zenawi-net-worth/
http://www.railwaygazette.com/news/infrastructure/single-view/view/contract-awarded-for-ethiopian-electric-railway.html