የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ርክክብ ዛሬ ይካሔዳል

  • የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ደግሞ በነገው ዕለት ለቋሚ ሲኖዶሱ ያስረክባል
A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የተቋማዊ ለውጥ አመራር ሲያጠና የቆየው የባለሞያ ቡድን በዛሬው ዕለት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱን ለሀ/ስብከቱ በይፋ ያስረክባል፡፡

ዛሬ፣ የካቲት ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በሚካሔደው የርክክብ እና ምስጋና መርሐ ግብር፣ 15 አባላት ያሉት የባለሞያ ቡድኑ ከአንድ ሺሕ በላይ አጠቃላይ ገጾች ያሏቸውን 12 ሰነዶች በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳትና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ነው የሚያስረክበው፡፡

ከረፋዱ 4፡00 – 6፡00 በሚዘልቀው በዚኹ የርክክብና የምስጋና መርሐ ግብር፣ የሀ/ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የብዙኃን መገናኛ ዘጋቢዎች እንደሚታደሙ የተመለከተ ሲኾን የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ለመርሐ ግብሩ ክንውን ድጋፍ ማድረጉ ተገልጦአል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ የቅርብ ክትትል የሀ/ስብከቱን የመዋቅር አደረጃጀትና አሠራር ጥናት ያከናወነው የባለሞያ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ለሀ/ስብከቱ በይፋ የሚያስረክበው ሰነድ÷ በሀ/ስብከቱ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ሓላፊዎች፣ በ169 ገዳማትና አድባራት የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና የምእመናን ተወካዮች ውይይት የተደረገበትና ከውይይቱ በተሰበሰቡ ግብዓቶች የዳበረና የተስተካከለ ነው፡፡

ከውይይት መድረኩ የተገኘውን የተሳታፊዎች ትችትና አስተያየት በከፍተኛ ጥንቃቄ መለየቱንና ማደራጀቱ የተገለጸው የባለሞያ ቡድኑ በተለይም÷ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለውን የአደረጃጀት መዋቅር፣ የገዳማትና አድባራት ደረጃ መስፈርትንና የሰው ኃይል ትመናውን እንዲሁም የፋይናንስ ፖሊሲውንና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያውን መሠረታዊ ማስተካከያ በማድረግ ጭምር ለማደራጀት ሌት ተቀን ሲሠራ መሰንበቱ ተዘግቧል፡፡