አቡጊዳ – ህወሓት ፀረ ዴሞክራሲ (ፀረ የወላጆቻችን ትግል) መሆኑ በተግባር አስመስክሯል አሉ አቶ አብርሃ ደስታ

አረና በሁመራ ለማድረግ ያቀደው ህዝባዊ ስብስበ በአዲግራት እንደተደረገው ሁሉ በሕወሃት አምባገነንነት ሳይሳካ ቀርቷል። የአረና አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ በፌስቡክ ብሎጋቸው :

«ዓረና መድረክ በሑመራ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ለዓርብ ጥር ሰለሳ ቀጠሮ ይዞ፣ አስተዳዳሪዎችን አሳውቆ፣ የማዘጋጃቤት አዳራሽ ተፈቅዶለት ያለ ምንም የፀጥታ ችግር የተሳካ ቅስቀሳ ቢያደርግም የሑመራ (እንዲሁም የወልቃይት) ህዝብ ጥሩ አቀባበል ያስደነገጣቸው የከተማው አስተዳዳሪዎች ቃላቸው በማጠፍ የጠራነው ስብሰባ ሕገ ወጥ መሆኑና ማካሄድ እንደማንችል ዛሬ ሐሙስ ጥር ሃያ ዘጠኝ ትእዛዝ ሰጥተውናል። ለስብሰባው የሁለት ቀናት ሙሉ ቅስቀሳ ተደርጓል። ከ አስር ሺ በላይ በራሪ የጥሪ ወረቀት በሑመራና ሌሎች ስምንት የአከባቢው ከተሞች ታድሏል። ስልሳ አራት የፓርቲው አባላት በቅስቀሳው ተሳትፈዋል። ሁለት የድምፅ ማጉልያ በመጠቀም አውጀናል። ህዝቡ በስብሰባው ለመሳተፍ ያሳየው ተነሳሽነት በመገንዘብ ካድሬዎቹ ስብሰባው አግደውታል። ማስፈራርያም ተሰጥቷል» ሲሉ የነበርየወልቃይት ሑመራ ህዝብ ላደረገልን መልካም አቀባበል እናመሰግናለን»

ሲሉ፣ የነበረዉን ሁኔታ ያብራሩ አብራርተዋል። የወልቃይጥ ጠገዴ ሕዝብም ላደረገላቸው ትብብርና ድጋፍ ምስጋናቸዉንም አቅርበዋል።

የትግራይ ህዝብ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ የከፈለው ትልቅ ዋጋ ሃይጃክ እንደተደረገ ያስረዱት አቶ አብርሃ፣ የሕወሃት፣ ሕዝብን የማፈን ተግባራትን፣ የጭካኔ ተገባራት ብልዉታል።

«ህወሓት በትክክል ጨካኝ ነው። “ጨካኝ” የሚል ቃልም አይገልፀውም። ትናንት ማታ ካድሬዎች በሑመራ ከተማ አልጋ እንዳናገኝ ባለ ሆቴሎችን ያስፈራሩ ነበር (አልጋ እንዳያካራዩን)። እራት ለመብላት ስንንቀሳቀስ እየተከታተሉ የምግብቤት ባለቤቶችን እራት እንዳያቀርቡልን ያስጠነቅቁ ነበር። እራት ካቀረቡልን ግን (ነገ ጠዋት) የንግድ ፍቃዳቸው እንደሚሰረዝ ይነግሯቸው ነበር። ይህ የተደረገው ሐሙስ ማታ ነበር። ከሐሙስ በፊት ግን አስተዳዳሪዎቹን ሳይቀሩ ጥሩ አቀባበል አድርገውልን ነበር። ህወሓቶች ግን ለቂም በቀል ባትጋብዙን ምን አለበት? ለምን ህዝብ ፊት በሐሳብ ተከራክረን አሸናፊው በህዝብ ድምፅ አይለይም? ለነፃነትና ዴሞክራሲ ብለው ህይወታቸው የሰዉ ወላጆቻችንን አሳዘኑኝ። የወላጆቻችን ትግል ዉጤቱ እንዲህ ዓፈና ከሆኑ አባቶቻችን ባደረጉት ትግል ከስረዋል ማለት ነው። ምክንያቱም እነሱ የህይወት መስዋእት ቢከፍሉም የታለመው የልጆቻቸው ነፃነትና ዴሞክራሲ ግን ከሽፏል። እኛ ልጆቻቸው እንደገና መስዋእት ልንከፍል ነው። ወላጆቻችን ጭቆናን መታገል እንጂ መቀበል አላስተማሩንም። ስለዚህ ወላጆቻችን የጀመሩት የነፃነት ትግል እንጨርሰዋለን። ዴሞክራሲ በተግባር እስኪረጋገጥ ድረስ እንታገላለን። ህወሓት ፀረ ዴሞክራሲ (ፀረ የወላጆቻችን ትግል) መሆኑ በተግባር አስመስክሯል። በጨቋኞች አንምበረከክም። ከባርነት ነፃነት ይሻላል። ወላጆቻችን ለስልጣን አልታገሉም። ህወሓት ግን የወላጆቻችን ትግል የስልጣን ኮረቻ ለመጨበጥ ተጠቀመበት። የነፃነት መንገድ ትግል ነው» ሲሉም ትግላቸዉን በምንም ሁኔታ እንደማያቋርጡም አረጋግጠዋል።

በሁመራ ስለነበረዉ ሁኔታ ሲዘረዝሩ «የዓረና ፓርቲ የድርጅቶች ጉዳዮች ሐላፊ አቶ ስልጣኑ ሕሸና የፓርቲው አመራር አባል የሆነው አቶ ሃይለኪሮስ ታፈረ ትናንት ምሽት በሑመራ ከተማ በፖሊስ ታስረዋል። ዛሬ ዓርብ ተለቀዋል። በስብሰባው ለመሳተፍ የመጣ ህዝብ በአስተዳዳሪዎች ተበትኗል። ዛሬ በሑመራ ከተማ ከ አምስት ሰው በላይ ተሰባስቦ መንቀሳቀስ ወይ መቀጠም ወይ ሻይ መጠጣት አይፈቀድም ነበር። የፀጥታ ሃይሎች እየተዘዋወሩ ይበትኑም ያስሩም ነበር። ባጠቃላይ ዛሬ በሑመራ ከተማ ‘State of Emergency’ ታውጆ ነበር። ከአባሎቻችን ጋርም መሰብሰብ አልቻልንም። ህወሓት የሰለማዊ ትግል በር እያጨለመው ይገኛል። የወልቃይት ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ስርዓቱ ለመቀየር ከሚታገል ማንኛውም ሃይል ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑ አረጋግጦልናል» ነበር ያሉት።