ጉራማይሌ ፖለቲካ ክፍል 2 ዛሬም መሬት ማስወሰዱ ቀጥሏልን? – ተመስገን ደሳለኝ
ከእነዚህ ክስተቶች በተጨማሪ በአካባቢው የተመለከትኩት ከባድ ውጥረት አለ፤ ይኸውም ‹ለሱዳን ሊሰጥ ነው› እየተባለ የሚነገርለት የመሬት ጉዳይ ካመጣው ጣጣ ጋር የሚጋመድ ነው፤ በርግጥ በአንዳንዶች ዘንድ መሬቱ ወደ ውስጥ ስልሳ (60)፣ ወደ ጎን ደግሞ አንድ ሺህ (1000) ኪሎ ሜትር ድረስ እንደተሰጠ ይታመናል፡፡ ይሁንና በግሌ ይህ ክስ ማረጋገጫ የሚቀርብበት ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
በጉዳዩ ላይ ምክንያታዊ ለመሆንም በዚህ በተጠቀሰው የመሬት ስፋት ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ከተሞችን መመልከቱ የተሻለ በመሆኑ፣ በቀጥታ ከሱዳን ጋር ከሚዋሰኑ ሁለት ከተሞች አንስተን እናስላው፤ እናም ከመተማ ከተነሳን ሸህዲን፣ ወህኒ፣ ነጋዴ ባሕር እያልን ጭልጋን እናገኛለን፡፡ መነሻችን ከሌላኛው የወሰን ከተማ ተሂ ከሆነ ደግሞ ምንጁግጁግ፣ ወዲ በርዚን፣ ኩሊት፣ ሸንፋ፣ ማሕበረ-ስላሴ ገዳምን አልፈን ደንገል እንደርሳለን፡፡ እንግዲህ የሰማነው ወሬ እውነት ከሆነ እነዚህ መሬቶች ሁሉ ለሱዳን ተሰጥተዋል ማለት ነው፡፡ ግን ለምን? ኢህአዴግ እንዲህ ሙጭጭ ብሎ የያዘውን ሥልጣን ሊያሳጣው የሚችል ውሳኔ ላይ ለመድረስ (ከተሞቹን ለሱዳን ለመስጠት) የተገደደበት ምን ምክንያት አለ? በነገራችን ላይ ይህ አስተያየት ስርዓቱ ለሀገር ጥቅም ይቆረቆራል እንደማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሆነ ክፉ ቀን ሥልጣኑን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ሁኔታ ከገጠመው ሀገር ከመበታተንና ከማፈራረስ የሚመለስ አለመሆኑን የቀድሞው ተሞክሮዎቹ ይነግሩናል፡፡
የሆነው ሆኖ ሊተኮርበት የሚገባው ኢህአዴግ እስከአሁን በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሳይሰጥ ያደፈጠበት አንዳች የሸሸገው ሚስጥር ቢኖር ነው የሚለው ይመስለኛል፤ የዚህ መነሻ ምክንያታችን ደግሞ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በድብቅ ለሱዳን የሰጣቸው (ዛሬ ተወሰዱ ከሚባሉት ውስጥ የማይካተቱ) መሬቶች የመኖራቸው እውነታ ነው፤ ይኸውም ብአዴን የመሰረተው ‹‹ዘለቀ እርሻ›› የተሰኘው ድርጅት በአንድ ወቅት ያስተዳድራቸው የነበሩት አብደረግ እና ደሎል (ሽመል ጋራ እና ምዕራብ አርማጭሆ) ውስጥ በቁጥር ከአንድ እስከ ስምንት የተሰየሙ ግዙፍ የእርሻ መሬቶች ነበሩ፤ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከቁጥር ሁለት እስከ ስምንት ያሉትን (በድምሩ ወደ ሁለት መቶ ሺህ ሄክታር የሚደርሱ) መሬቶችን አሳልፎ ሰጥቷል፤ ይህንንም ተከትሎ ‹‹ዘለቀ እርሻ›› እንቅስቃሴ አልባ ሆኗል፡፡ በርግጥ ‹ቆራጦቹ› የብአዴን አመራሮችም ቢሆኑ እንዲህ አይነቱን ጥሬ ሀቅ አይክዱም፤ ይልቁንም ‹ቀድሞውንም ግማሹ ይዞታ የእነርሱ ነበር› ብለው ያስተባብላሉ እንጂ፡፡ …ግና! ማን ነበር ‹‹ከሱዳን ነጥቀን የወሰድነው መሬት አለ!›› ያለው? መለስ ዜናዊ ይሆን?
እንዲሁም ‹‹ስናር›› የተባለው ከፊል ቦታ ለሱዳኖች መሰጠቱን ከታማኝ ምንጭ ሰምቻለሁ፤ ርግጥ ስናርን ሱዳኖች እንዲቆጣጠሩት በር የተከፈተላቸው የደርግ መንግስት በወደቀበት ማግስት (በ1983 ዓ.ም መጨረሻ) ነው፤ የዚህ ስጦታ መግፍኤ በትግሉ ዘመን ሱዳን ኢህአዴግን ‹አቅፋና ደግፋ› ለድል እንዲበቃ ያበረከተችው ውለታን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ይነገራል፡፡ እናም ሱዳኖች እንደ መና የወረደላቸውን ያልታሰበ ገፀ-በረከት ለመጠበቅ ወደ አስራ ሁለት ገደማ የሚደርሱ ወታደራዊ ካምፖችን መስርተው እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ የምድሪቱን በረከት ሲቀራመቱ መቆየታቸው እውነት ነው፡፡ ይሁንና በ1988 ዓ.ም በወቅቱ የሱዳን መንግስት አፈ-ጉባኤ የነበረው ሃሰን አል-ቱራቢ እጅ እንዳለበት የተጠረጠረውን በአዲስ አበባ በቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንነት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ኢትዮጵያና ሱዳን (በተለይም ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠትና ባለመስጠት ጉዳይ) ግጭት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህን ጊዜም ኢህአዴግ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ‹‹መሬታችሁን አስመልሱ›› በሚል ቀስቅሶ በሱዳናውያን ላይ ያዘምታቸውና ድል ያደርጋሉ፤ ስናርም ተመልሳ በኢትዮጵያውያን ይዞታ ለመጠቃለል በቃች፡፡ ግና! አሁንም እንቆቅልሽ በሆነ ሁኔታ (ከ1999 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ) እንደገና ወደ ሱዳን ተላልፋ ተሰጠች፤ በነገራችን ላይ ስናር በሃያ ስድስት ‹‹ኮርድኔት›› የተከፋፈለች ስትሆን፣ ዛሬ የኢትዮጵያውያን ይዞታ ሊባል የሚችለው ‹‹ኮርድኔት 24›› በተሰኘው ውስጥ ባለፈው ዓመት ህይወታቸው ያለፈውና በርካታ ታጣቂዎችን ማስከተሉ የሰመረላቸው ባሻ ጥበቡ እና አስመሮም መኮንን የተባሉ ግለሰቦች ለሱዳናውያን ሳያስረክቡ፣ በራሳቸው ኃይል ተገዳድረው ያቆዩት መሬት ነው፡፡ በተቀረ በአካባቢው የምናገኛቸው ኢትዮጵያውያን ከሱዳናውያን ላይ በአረብኛና እንግሊዘኛ በተፃፈ ውል በተከራዩት መሬት ላይ ብቻ ነው፡፡
በአናቱም በአሁኑ ወቅት ለሱዳን ሊሰጡ ነው እየተባለ የሚነገረው እንደ መተማ-ዮሀንስ፣ ዳፋ፣ ሽመል ጋራ፣ ፎርኹመር፣ አብዱራፊ፣ ነፍስ ገብያ፣ አለቃሽ (በረሃማ አካባቢ ነው)… የመሳሰሉ ከተሞች ስማቸው ተደጋግሞ በመነሳቱ፣ አካባቢውን ውጥረት ውስጥ ከትቶታል፡፡ በርግጥም ከአገዛዙ ያደረ ታሪክ አኳያ መሬቶቹን አይሰጥም ተብሎ አይታሰብም፤ በተለይም ጉዳዩን ለጥጠን የሰሜን አፍሪካ አብዮት በፈጠረበት ስጋት፣ በድንገቴ ውሳኔ እየገነባ ካለው የ‹‹ህዳሴ ግድብ›› ጋር አነፃፅረን ካየነው፣ የሱዳንን ድጋፍ ለማግኘት መሬቶቹን አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል ወደሚል ጠርዝ እንገፋለን፡፡ …ግና! ይህ አይነቱ ኢህአዲጋዊ ድፍረት ‹‹አባትየው ቢሞት የለም ወይ ልጅየው?›› በሚል ሕዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ዛሬ ‹‹ተሰጡ›› ወይም ‹‹ሊሰጡ›› ነው ብለን የምንጫጫባቸው መሬቶች‹‹የይገባኛል›› ጥያቄ ያልቀረበባቸው በመሆኑ፣ ኦቦ ሌንጮ ለታ ‹በባሌ ሲጠብቁን፣ በቦሌ ገባን› እንዲል፣ ስርዓቱ ሆነ ብሎ ከእውነታውአርቆ ለማደናገር የሚጠቀምባቸው አጀንዳዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መጠርጠሩ አስተዋይነት ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ጉራማይሌ ፖለቲካ ማለት ይህ ነው፡፡
ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ኢህአዴግ በእነዚህ አካባቢዎች እያደረገ ያለው የሚከተለው መሆኑ ነው፡- ከኩሊት እስከ ቋራ ድንበር ድረስ ከወሎ፣ ከጎጃም እና ከጎንደር ነዋሪዎች አሰባስቦ የመልሶ ማስፈር ስራ ሰርቷል፤ የሰፈራው ዋነኛ አላማም ለም መሬት ይዘው እያረሱ ቤተሰብ መስርተው እንዲቀመጡ ያማቻቸላቸውን ሰፋሪዎች መሳሪያ በማስታጠቅ በአካባቢው በኩል ሊመጡ የሚችሉ የኃይል አማራጭን የሚከተሉ ተቃዋሚዎችን እንዲከላከሉ እና ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ደግሞ አስቀድመው መሬት ለሰጣቸው መንግስት እንዲያሳውቁ ማድረግን ያሰላ ነው፡፡ በዚህም ለሥልጣኑ አስጊ የሆነውን ቀዳዳ ለመድፈን እየሞከረ እንደሆነ መረዳት ይቻላል (በነገራችን ላይ ከጎንደር ተቆርሶ ለትግራይ መሬት ተሰጥቷል የሚል አደገኛ ቅስቀሳም እየተካሄደ ነው፤ በግሌ ይህ ጉዳይ የሚያወዛግብ አይመስለኝም፤ ስርዓቱ ያነበረውን ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም የማንደግፈው እስከሆነ ድረስ መሬቱ ወደ የትኛውም የሀገሪቱ ክልል ቢሄድ ለውጥ አይኖረውም፤ ምክንያቱም በኢህአዴግ ግብዓተ-መሬት ላይ የሚያብበው መልከዓ-ምድራዊ ፌደራሊዝም (Geographical Federalism) እነዚህን አጨቃጫቂ መሬቶች ለአስተዳደር አመች በሆነ መልኩ ማዋቀሩ አይቀሬ ነውና)