ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን ተሾመ
- ተሿሚው ዋና ዲን አሜሪካዊው ቀሲስ ኸርበርት ጎርደን (ቄስ ሰይፈ ወልደ ገብርኤል)÷ ከሕንዳዊው ቀሲስ ዶ/ር ቪ.ሲ. ሳሙኤል (1960-1968 ዓ.ም.) እና ግብጻዊው ዶ/ር እንጦንስ ያዕቆብ (1991-1993 ዓ.ም.) ቀጥሎ የተሾሙ ሦስተኛው የውጭ ዜጋ ናቸው፡፡
- በኮሌጁ ቦርድ ቀርበው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተሾሙት ዋና ዲኑ÷ የኮሌጁን አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ አደረጃጀትና አሠራር በሞያዊ አመራር በማጠናከር ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚያድግበትን ተቋማዊ አቅምና ጥራት ያጎለብታሉ፡፡
- በኮሌጁ ደንብ መሠረት÷ የመምህራንና ተማሪዎችን ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ እየተመካከሩ በአግባቡና በወቅቱ በመመለስ የመማርና ማስተማሩን ጤናማነት ይጠብቃሉ፡፡
- ኮሌጁ÷ በሃይማኖታዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካዳሚያዊ ዕውቀታቸውና ሕይወታቸው ምሳሌ የኾኑ ኦርቶዶክሳውያን ደቀ መዛሙርትን በጥብቅ ዲስፕሊን እየመለመለ የሚያሠለጥንበትን የቅበላ ሥርዐት ያጠናክራሉ፡፡
- ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚበቁ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትና ምሁራን በዘመናዊ ሥርዐተ ትምህርት ታንፀው የሚፈልቁበት መካነ ጥበብ መኾኑን ያረጋግጣሉ፡፡
- ‹‹የኮሌጁ አስተዳደር በባለሞያ ተጠናክሮ ቢመራና ደቀ መዛሙርቱ በጥራት እየተመለመሉ እንዲገቡ ቢደረግ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን በብቃት የሚያገልግል፣ በዕውቀትም በመንፈሳዊ ሕይወትም ምሳሌ ሊኾኑ የሚገባቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ጠባቂዎች ደቀ መዛሙርት መፍለቂያ ኮሌጅ ይኾናል፡፡›› /መምህራን/
- ‹‹…የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም ተማሪውን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር ማስተካከልና ማብቃት አለብን፡፡ እነዚኽ የትምህርት ተቋማት ሰባክያንና መምህራን የሚፈልቁባቸው የሃይማኖታችን ምንጮች ናቸው፡፡ ምንጩ ደፍርስ ከኾነ የተጠማው መንገደኛ ውኃ ለመጠጣት ይቸገራል፤ ጥሩ ምንጭ ከኾነ ግን የጠማው ብቻ ሳይኾን ያልጠማው መንገደኛም ቢኾን በውኃው ጥራት ከመጎምጀቱ የተነሣ ሳይቀምሰው አያልፍም፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
ተጨማሪ መረጃዎችን ይከታተሉ
