ፓትርያርኩ የሀ/ስብከቱ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት ‹ተቃዋሚዎች› ንግግር ግብረ ገብነት የጎደለው ሕገ ወጥ እንደኾነና የለውጥ ሒደቱ መሥመሩን እንደማይለቅ አረጋገጡ

  • ‹‹በቤተ ክርስቲያን ልጅነት በግብረ ገብነት መነጋገር ነው እንጂ ሕገ ወጥ ንግግር ተቀባይነት የለውም፤ ይኼ የአሁኑ የእናንተ የረጋ አቀራረብ ነው፤ ያስመሰግናል፤ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት ነው የኹላችን ጥረት፤ ወደኋላ የምንመለስበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/
  • ‹‹የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያስጠናውን ተወያይተንበታል፤ የታሰበው የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ የሚያነቃቃ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር ለማስፈን በመነሣሣቷ ደስተኞች መኾናችን ዕወቁልን፤ እኛን እንደወከሉ መስለው እዚኽ የመጡት እኛን አይወክሉም፤ ጥናቱ በእኛ ዘመንና በቅዱስነትዎ ጊዜ መተግበር አለበት›› /የምእመናን ተወካይ የኾኑ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር/
  • ‹‹በመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቅ ላይ ውይይት ሲካሔድ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በዝቷል ያላችኹትን ቀንሱ፣ የጎደለበትን ጨምሩ ብለዋል፤ ሀ/ስብከቱ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቀና የዘመኑን ሥልጣኔ የዋጀ አደረጃጀትና አሠራር ለመዘርጋት መነሣቱ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስነቅፈውም፤ የበዛው ተቀንሶ፣ የጎደለው ተሟልቶ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሳችን መሪነት እንድንሠራበት ይደረግ››
  • ‹‹ከእኛ በላይ ያሉት አባቶች እየተሰደቡ እኛን የሚሰማን አይኖርም፤ የሥነ ምግባር ጉድለት ይስፋፋል፤ ሠርተው የሚያሠሩንን አባቶቻችንን አጥተን ሌላ አባት ልናገኝ አንችልም፤ የስም ማጥፋት ዘመቻውና ውንጀላው እንዲቆም ቅዱስነትዎ መመሪያ ቢሰጡልን፤ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚያልቅ ነገር ካለ ይለቅ፤ አስተዳዳሪዎች እየተለያየን ሳይኾን በአንድ ላይ ኾነን ፊት ለፊት እንነጋገር፤ የተነጋገርነውም እዚኹ ይቅር፤ በኢንተርኔት የመናፍቅ መጫወቻ አንኹን›› /የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተወካይ የኾኑ የጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ/