ሰበር ዜና – የአ/አ ገዳማትና አድባራት ሰበካ ጉባኤያት ሊቃነ መናብርት፣ ካህናት፣ ሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን የሀ/ስብከቱን የተቋማዊ ለውጥ ጥናት በመደገፍ ነገ እሑድ በ8፡00 ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በሺዎች ሊተሙ ነው፤ የአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ ጸድቆ እንዲተገበርና የሙሰኛ አስተዳዳሪዎችና ተቃዋሚ ነን ባዮች የሀብት ምንጭ እንዲመረመር ይጠይቃሉ

  • ‹‹ምእመናን የቤተ ክርስቲያን አባላት እንጂ አካላት አይደሉም›› ባዮቹና በተቃውሟቸው ‹‹መንግሥት እየደገፈን ነው›› ያሉት እነኃይሌ ኣብርሃ÷ ፓትርያርኩ ረዳታቸውን ‹‹እስከ ገና ድረስ ዘወር የማያደርጉ›› ከኾነ እንቅስቃሴያቸው ትጥቃዊ መልክ እንደሚኖረው በማስጠንቀቅ ዝተዋል – ‹‹ያኹኑ ሊቀ ጳጳስ የማን ረዳት ናቸው፤ የማኅበረ ቅዱሳን ናቸው ወይስ የቅዱስነትዎ? በሊቀ ጳጳሱ ፈረጅያ ሥር ተከተው ጀግና ሊቀ ጳጳስ በሠራው ሀ/ስብከት ቢሮ ተሰጥቷቸው እያረቀቁበት ስለኾነ እንዲወጡ ይደረግልን! ከአቅማችኹ በላይ ከኾነ አሳልፋችኹ ለመንግሥት ስጡ፤ ሄደን እኛ እናስለቅቀዋለን፤ ውጊያ ከመገባቱ በፊት ወረቀቱ ተቀዶ መመለስ አለበት፤ እነንቡረ እድ ኤልያስ እነአባ ሰረቀ ያርቅቁ፡፡ ታኅሣሥ ገና ላይ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ወደ ጅማቸው ብቻ ቢሄዱ፤ ይህን ከተማ አበጣብጠውታል፤ መንግሥትም ስለማይናገር ነው እንጂ እያዘነ ነው፤ ረዳትዎን ዘወር ያድርጉልን!››
  • በግፍና ነውር በተሞላው አስተዳደራቸው የተነሣ የወሊሶ ካህናትና ምእመናን ያባረሯቸው አቡነ ሳዊሮስ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ውሳኔ በመቃወም ከተቋማዊ ለውጥ ተቃዋሚዎች ጋራ መቆማቸውን በይፋ አረጋግጠዋል
  • ፓትርያርኩ ለአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ ክንውን ከሰጡት አባታዊ መመሪያ በተፃራሪ በእነ ኃይሌ ኣብርሃ ለሚመራው የተቃዋሚ ነኝ ባይ ወሮበላ ስብስብ ፊት በመስጠት የሚያሳዩት የመደራደር ዝንባሌ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና በተቋማዊ ለውጥ ኃይሎች ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል፤ ‹‹ተጠርቼ መጥቼ የእርስዎ ረዳት የኾንኩትና ደፋ ቀና የምለው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ውሳኔና የቅዱስነትዎን መመሪያ ለማስከበር ነው፤ አቋምዎን በግልጽ ያሳውቁኝ!›› /ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ/