ዶር ነጋሶ ጊዳዳ የአክሱም ሃዉልት ያለበት ስጦታ ተበረከተላቸው

Millions of voices for freedom – UDJ

ዶር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው አኩሪና ዉጤታማ በሆነ መንገድ ካገለገለኡ በኋላ ሃላፊነታቸው ለተተኪዉ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አስረክበዋል።

በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የተዘጋጀ፣ ዶር ነጋሶ ለአመታት ለአገራቸው ኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጾ የሚያሳይ የቪዲዮ ቅንብር ለጠቅላላ ጉባኤዉ የቀረበ ሲሆን፣ የክልሉ የአንድነት አባላትን ወክለው የተገኙ፣ የጠቅላላ ጉባኤዉ አባላት፣ ለዶር ነጋሶ ያላቸውን ፍቅር፣ አክብሮትና አድናቆት በከፍተኛ ጭብጨባና ስሜት ገልጸዋል። ይህ ጠቅላላ ጉባኤ እኝህ ታልቅ ኢትዮጵያዊ አባት ምን ያህል በጣም የተወደዱ መሆናቸውን በግልጽ ያረጋገጠ ነዉ።

ከትግራይ ክልል የመጡ የአንድነት አባል፣ ለዶር ነጋሶ ያላቸውን አድናቆት የገለጹት የአክሱም ሃዉልትን የሚያሳይ ስጦታ በማበርከት ነበር። የቀድሞ የገዢ ፓርቲ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ «የአክሱም ሃዉልት ለትግሬው እንጂ ለሌላዉ ምንድን ነዉ ? » ያሉትን ከፋፋይና ዘረኛ አባባል በማስታወስ፣ የአክሱም ሃዉልት በአክሱምና በትግራይ ብቻ ለሚኖረዉ ሳይሆን የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ቅርስ እንደሆነም በመናገርና የኢትዮጶያዊነትን እና የአንድነት ድምጽን በማስተጋባት፣ ስጦታውን በአክብሮት ለዶር ነጋሶ ያበረከቱት።

ገዚዉ ፓርቲ በስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ እንዲያስችለው ዋናዉን ቁልፉ መሳሪያ ዜጎችን በዘርና በሃይማኖት መከፋፈል፣ አንድ የሚያደርጋቸውን እና የሚያስተሳስራቸዉን ሳይሆን፣ የሚለያቸውን ማጉላት፣ እንዳይተማመኑና እንዳይቀባበሉ ማድረግ መሆኑ ይታውቃል።

ነገር ግን በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ሲንጸባረቅ የታየው መንፈስ ፣ በኢሕአዴግ ዘንድ ካለው የተለየ ፣ የመከፋፈል ሳይሆን የአንድነት፣ ጾታ፣ ዘር፣ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ ስብእናና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረ ነዉ። እንግዲህ ምርጫዉና ልዩነቱ በገሃድ ጎልቶ ወጧል። በዘር መከፋፈሉ እንዲቀጥል፣ ልዩነቶችና ጥላቻዎች እንዲበዙ፣ የኢትዮጵያዊያን መሰባሰብ እንዳይኖር፣ የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ እየወደቀ የክልልና የጎጣ አስተሳሰብ እንዲያድግ ፍላጎት ያለው ካለ፣ ብዙ መጨነቅ አይኖርበትም። ሕወሃት/ኢሕአዴግ አለለት።

ነገር ግን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዘሩ ሳይሆን በስራዉ እንዲመዘዘን፣ ሁሉም ዜጋ በዘሩ፣ በጾታዉ ፣ በሃይማኖቱ ልዮነቶች ሳይደረግበት እኩል እንዲታይ፣ በሁሉም የአገሪቷ ወረዳዎች በነጻነት መስራት፣ መኖር.፣ መነገድ፣ መማር፣ መዉጣት ፣ መግባት ፣ መምረጥ፣ መመረጥ የሚችልበት፣ አንዲት የበለጸገች፣ ለሁሉም እኩል የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያዉን ለመመስረት የሚፈልግ ሁሉ ግን ፣ ይኸው ከሕወሃት/ኢሕአዴግ የተለየ ፣ ሰላማዊ አማራጭ ቀርቦለታል።

የአንድነት ፖለቲካ፣ ለቀደምት ታጋዮች ክብርን የሚሰጥ፣ የኢትዮጵያዊነትን እና የሰለጠነ ፖለቲካ ነዉ። ይህ ፖለቲካ በአገራችን እንዲሰፍን የሚፈልግ ሁሉ የአንድነት ፓርቲን ይቀላቀል። በገንዘቡ፣ በሃሳብ፣ በጸሎት…. በሚችለው ሁሉ አቅሙ እንደፈቀደ ይደግፍ።