ገዳማትና አድባራት በአገልግሎት ስፋታቸውና በልማት አቅማቸው በደረጃ የሚመደቡበትና በቀጣይነት የሚያድጉበት መስፈርት ሊወጣ ነው
- በደረጃ ምደባው በአጥቢያዎች የተከማቸውን ከፍተኛ የአገልጋዮችና የሠራተኛ ቁጥር በማሠልጠንና ማብቃት ማደላደልና ማሸጋሸግ እንጂ ማፈናቀል አይኖርም ተብሏል
- ገዳማትና አድባራት በፋይናንስ ፖሊሲው መሠረት ከዓመታዊ በጀታቸው ቀሪ ከሚኾነው ገንዘባቸው 60 በመቶውን ለልማት ተቋማት ማቋቋሚያና ማስፋፊያ (የልማት ፈንድ) ይመድባሉ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናት ያሉበትን ኹኔታ ተገንዝበው አገልግሎታቸውን የበለጠ በማስፋፋት ወደተሻለ የአገልግሎት ዕድገት የሚሄዱበትን አቅጣጫ ያመላክታል የተባለ የደረጃ መስፈርት ጥናት ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ መስፈርት ሰነዱ÷ በሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ሥር የሰደደውን የመልካም አስተዳደር፣ የፋይናንስ አያያዝና የሰው ኃይል አመዳደብ ችግሮች በወሳኝ መልኩ ለመቅረፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያዎች የተካሄደው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት አካል መኾኑ ተገልጧል፡፡
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋራ በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በሞያና ልምድ የተመጣጠነ የሰው ኃይል ቁጥር የማስገኘት፣ ከአገልግሎቱ ጋራ የተመጣጠነ የአገልጋዮች ክፍያ ሥርዐት የመዘርጋት፣ ከምእመኑ ፍላጎት ጋራ የተመጣጠነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልት የመቀየስና በአጠቃላይም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋናና መሠረታዊ ተልእኮ ከኾነው የስብከተ ወንጌልና ክህነታዊ ተግባራት አንጻር አገልግሎቷን የመምራትና ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የደረጃ መስፈርቱ÷ ተዋረዳዊና ጎንዮሻዊ የሞያ ልህቀት ፍኖት/ሰዋስው (career path) ባለውና ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ሀ/ስብከት በሚዘልቀው መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሥራ መደብና የሥራ መዘርዝር መሠረት ራሳቸውን በመንፈሳዊ ቅንዓትና በፍትሐዊነት ላይ በተመረኮዘ የመወዳደር ብቃት የሚያሻሽሉበት ኹኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተዘግቧል፡፡
የምዘና መስፈርትና ደረጃ ጥናት ረቂቁ ገዳማቱን፣ አድባራቱንና አብያተ ክርስቲያናቱን በአምስት ደረጃዎች የከፋፈለ ሲኾን አራት ዐበይትና ከሠላሳ በላይ ንኡሳን የምዘና መስፈርቶች ተለይተውበታል፡፡ በዋናነት ለተቀመጡት መስፈርቶች የተሰጣቸው አጠቃላይ ክብደት በሥራቸው ለተካተቱት ንኡሳን መስፈርቶች ተከፋፍሎ በመጨረሻ ከመቶ የሚገኘው ጠቅላላ ድምር ውጤት የአብያተ ክርስቲያናቱን ደረጃ እንደሚወስን ተመልክቷል፡፡
በዚህም መሠረት በቤተ ክርስቲያኒቱ÷ ቅዳሴ፣ ሰዓታትና ጸሎት በዘወትር፣ በሳምንትና በበዓላት የሚፈጸምበት ጊዜ፣ የአብነት ትምህርት ጉባኤያትና የተማሪዎች ብዛት፣ ስብከተ ወንጌል የሚሰጥበት ጊዜ፣ የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ኹኔታ፣ በሙዝየም፣ በጠበልና በቀብር አገልግሎት እየሰጠች ያለችው መንፈሳዊ አገልግሎት 30 ነጥብ ተሰጥቶታል፡፡
ከሙዳየ ምጽዋት፣ ከልማትና ከአገልግሎት የሚገኘው የገቢ ኹኔታ 27 ነጥብ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሙዓለ ሕፃናት፣ በጤናና በአረጋውያን መጦርያ የልማት ተቋማትና የምግባረ ሠናይ ሥራዎች 23 ነጥብ፣ በአጥቢያው በሰበካ ጉባኤ የተመዘገቡ ምእመናንን ብዛት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ ሕጋዊነት፣ ስፋትና የምሥረታ ዘመን ያካተተው ሌሎች ሀብታትና ታሪክ መስፈርት 20 ነጥብ ክብደት እንደተሰጣቸው በጥናቱ ተብራርቷል፡፡
በዚህም መሠረት ከ85 – 100 ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ አንድ፣ ከ70 – 84.99 ያሉት ደረጃ ሁለት፣ ከ55 – 69.99 ያሉት ደረጃ ሦስት፣ ከ40 – 54.99 ያሉት ደረጃ አራት ሲባሉ ከተተከሉ እስከ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የኾኑ አዲስ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ለብቻቸው በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተለይተዋል፡፡
በየደረጃ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የተለያየ መዋቅር፣ የተለያየ የሰው ኃይል ምደባ/በቁጥርና በሞያ/ እንዲሁም የደመወዝ ስኬል የሚኖራቸው ሲኾን ይህም በየሁለት ዓመቱ በሚካሄድ ክለሳና አብያተ ክርስቲያናቱ ዐቅደው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ዕድገታቸው በቀጣይ የምዘና መስፈርት እየተረጋገጠ እንደሚሻሻል ከቀረበው ጥናት ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንደየሥራው ስፋት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ተፈላጊውን የትምህርት፣ የሥራ ልምድና የክሂሎት ዝግጅት ባገናዘበ አኳኋን ለየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በሚሠራው የሰው ኃይል ትመና ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚያስችላቸው የክፍያ ሥርዐት ተዘርግቷል፡፡ በተለይም ደግሞ በሀ/ስብከቱ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት አግኝተው ተተኪዎችን ማፍራት ይችሉ ዘንድ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በቢሮው ውስጥ ከሚሠራው ሥራ በበለጠ የካህናት ኑሮ የሚሻሻልበትን ኹኔታ ለመቅረፅ የቤተ መቅደሱ የውስጥ ክህነታዊ አገልግሎትም ቀዳሚ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡
በሰው ኃይል ትመናው ገዳማቱና አድባራቱ ካላቸው መንፈሳዊ አገልግሎትና የልማት እንቅስቃሴ አንጻር የሚበቃቸው ያህል አገልጋይ ያገኛሉ፡፡ ቀሪው የሰው ኃይል በፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው እንዲሁም በልማት ሥራዎችና ምግባረ ሠናይ ተግባራት ፖሊሲና መመሪያው መሠረት÷ አብያተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በጀታቸውን ከመጠባበቂያቸው ጋራ ከያዙ በኋላ ቀሪ ከኾነው ገንዘብ ከሚመድቡት 60 በመቶ የልማት ፈንድ በሚከፍቷቸው የልማት ተቋማት የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚሠማራበት ሥርዐት እንደሚኖር ታውቋል፡፡
ከዚህም አኳያ ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት በየአጥቢያው መኖሩ እሙን ቢኾንም አጥቢያዎች በልማት በየጊዜው ከሚፈጥሩት አቅምና በዚህም በሚስፋፉት የአገልግሎትና ምርት ተቋማት በሒደት የሚደላደል እንጂ የሚፈናቀል አገልጋይ እንደማይኖር ተገልጦአል፡፡
