የመሪዎቻችንን ንጽህና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው! ድምጻችን ይሰማ!

እሁድ ታህሳስ 13/2006

በግፍ እስር ላይ የሚገኙትን ጀግኖቻችንን ንጽህና ለመመስከርና የህዝበ ሙስሊሙ ድምጽ መሆናቸውን በህግ ፊት በተጨባጭ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በጀግኖቻችን ጠበቆች አማካኝነት እየተደረገ ያለው ይኸው ጥረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን ኮሚቴዎቻችን መንግስት ከለጠፈባቸው የሀሰት ውንጀላ ፍጹም የጸዱ መሆናቸውን በፍርድ ቤት ቀርበው የሚመሰክሩ ሰዎችን የማሰባሰቡ ሂደትም የፍቃደኝነት ፎርም በማስሞላት መልክ የተጀመረ መሆኑ ታውቋል፡፡

መሪዎቻችን በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ላይ ህዝበ ሙስሊሙን በሰላማዊ አካሄድ ላይ አደራ ያሉባቸው በርካታ ንግግሮቻቸው በማስረጃነት እንዲውሉ ለማድረግ እንዲሰባሰቡ እየተደረገ ሲሆን በተለይ በመጀመሪያዎቹ የአወሊያ ፕሮግራሞች እና በኋላም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተደረጉት የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራሞች ላይ የተቀዱት የድምጽና የምስል ማስረጃዎች መሰባሰባቸው በዚህ ረገድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ታውቋል፡፡

መሪዎቻችን በመሳጂዶች ላይ ከተደረጉት ፕሮግራሞች በተጨማሪ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ሲያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮችና የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊና ግልጽ ጥያቄዎች ለማብራራት ቃለ መጠይቅ የሰጡባቸው የራዲዮ ፕሮግራሞች፣ ጋዜጦች፣ መጽሄቶችና ሌሎችም የሚዲያ ውጤቶች በጠበቆች አማካኝነት እየተሰባሰቡ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ለህዝብ ድምጽ በመሆናቸው ብቻ መንግስታዊ የሀሰት ፍረጃ ሰለባ የሆኑትን መሪዎቹን ንጽህና ለማረጋገጥ እስከጥግ ድረስ መልፋት ያለበት ሲሆን በመንግስታዊ ተጽእኖ ስር በወደቀው የፍርድ ሂደትም ውስጥ ቢሆን የመሪዎቻችንን ንጽህና ለመመስከር ከምንጊዜውም በላይ ቆርጦ በመዘጋጀት የሚከፈለውን ሁሉ መስዋእትነት መክፈልም በትከሻው ላይ ያረፈ ሀላፊነት መሆኑ እሙን ነው!

ድምጻችን ይሰማ!