የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናታዊ ውይይት የመጨረሻ ዙር ተሳታፊዎች የሚኾኑት የቦሌ፣ ልደታ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ለተቋማዊ ለውጡ ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ነው፤ ለውጡ ‹‹ተረፈ ደርግና አሸባሪ የኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የዘረጋው አሠራር ነው›› የሚሉ ‹ተቃዋሚዎች› ጥናቱ ጸድቆ የሚተገበር ከኾነ ‹‹ፐርሰንት አንከፍልም፤ ተገንጥለን በቦርድ እንተዳደራለን›› በማለት በረዳት ሊቀ ጳጳሱ ቀጣይነት ላይ እያደሙ ነው

A.A.D Parish churches discussion on change mgt.

የየካ ክፍለ ከተማ ገዳማትና አድባራት ጥናታዊ ውይይት (ፎቶ: የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ድረ ገጽ)

  • ዛሬ ዐርብ ታኅሣሥ ፲፩ – ፲፪ የሚካሄደውን የልደታ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ልኡካን የሚሳተፉበትን ጥናታዊ ውይይት መስተንግዶ የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል እና የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ከታኅሣሥ ፲፫ – ፲፬ የሚካሄደውንና የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን የሚሳተፉበትን ጥናታዊ ውይይት ደግሞ የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ስፖንሰር ለማድረግ በየሰበካ ጉባኤያቸው ማስወሰናቸውንና የሀ/ስብከቱን ወጪ መጋራታቸውን ገልጸዋል፡፡
  • ታኅሣሥ ፮ እና ፯ በኮልፌ ቀራንዮ፤ ታኅሣሥ ፬ እና ፭ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን እንደ ቅደም ተከተላቸው የተካሄደው ጥናታዊ ውይይት÷ ከአሉባልታዎች ይልቅ ከቀረበው የጥናት ረቂቅ ይዘት ጋራ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው፣ ለሰነዱ መዳበር ብቻ ሳይኾን የይዘት መስተካከልም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ገንቢና ሞያዊ እንደነበር ባለሞያዎቹ፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ እና አዘጋጅ ኮሚቴው ጥናታዊ ውይይቶቹ በተካሄዱባቸው ዕለታት በመደበኛነት ያደረጓቸው የውሎ ምዘናዎች/ግምገማዎች በጉልሕ ያመለክታሉ፡፡
  • በክፍላተ ከተማው ልኡካን ከተነሡት ነጥቦች መካከል በሀ/ስብከቱ አድባራት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት የደረጃ መስፈርት ጥናት÷ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋራ የተመጣጠነ የሰው ኃይል /በቁጥር፣ በክህሎት፣ በሞያና ልምድ/ እንዲያገኙ የሚጠቁመው ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ ሐሳቡ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያላቸውን ሀብት፣ ታሪክ፣ ንብረት፣ ገንዘብ በተሻለ ደረጃ ለመጠቀም የሚችሉበትን ኹኔታ ለማመላከትና መንፈሳዊ ቅናትን በመፍጠር የአገልግሎት አሰጣጥ ተነሣሽነትን በአገልጋዮች መካከል ማስፈን መኾኑ ተገልጧል፡፡
  • በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ገዳማትና አድባራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ክምችት እንደያዙ የታመነበት በመኾኑ በጥናቱ መሠረት ገዳማቱና አድባራቱ ካሉበት ደረጃ ጋራ ተመጣጣኝ የኾነ የአገልጋይ ቁጥር በመደበኛነት ከያዙ በኋላ ቀሪዎቹ ሳይፈናቀሉ ለማስተዳደር የሚችሉባቸው አግባቦች/አማራጮች በጥናቱ ተቀምጠዋል፡፡ ከአግባቦቹ አንዱ፣ ከመደበኛው (ስታንዳርድ) የአገልጋይ ቁጥር የቀረውን አገልጋይ ጊዜያዊ ምደባ ሰጥቶ ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅማቸው ሳይነካ የሰው ኃይል ወደሚፈልግባቸው አጥቢያዎች የሚንሸራሽበት ሥርዐት ነው፡፡
  • ሌላው አማራጭ፣ አጥቢያዎች በራሳቸው አልያም በልማት ተቋማት ማስፋፊያ ፖሊሲው መሠረት በሚከፈቱ የልማት ተቋማት አንጻር ተገቢውን የክህሎት/ሞያዊ ሥልጠና በመስጠት ማሰማራት ነው፡፡ ከመደበኛ ቁጥር ውጭ የኾነው አገልጋይ በትርፍነት የሚቆየው ለረጅም ጊዜ ከኾነ ደግሞ ሲያገኘው የቆየው ደመወዝና ጥቅማጥቅም እንደተጠበቀለት በአዲስ አበባ ዙሪያ ይኹን በአህጉረ ስብከት የካህናት እጥረት ባለባቸው አብያተ ክርስቲያን አበል እየታሰበለት ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡ የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን ከማገልገልና የቅጥር ውጭን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ትርጉም ያለውን ይህን ሐሳብ የጥናታዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች በሙሉ ልብ የደገፉ ሲኾን አፈጻጸሙ በአገልጋዩ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንዲኾን በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡
  • ‹ቅሬታ› አቅራቢ ነን ባይ ተቃዋሚዎቹ ግን አሁን በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት መኖሩ ችግር መኾኑን እያወቁ፣ ከዚህ አንጻር የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብም በገጠርም በከተማም ያለችውን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለማገልግል የሚያስችል እንደኾነ ሳይሰወራቸው መረጃው አይኖረውም ብለው የሚያስቡትን ብዙኃኑን ካህን ‹‹በየአጥቢያው ኻያ ኻያ ካህን ብቻ ነው የሚያስፈልገው ተብሏል፤ መፈናቀላችኹ ነው፤ ወደ ጋምቤላ መበተናችኹ ነው፤›› እያሉ ሰፊ ውዥንብር መፍጠራቸው የ‹ቅሬታቸውን› አግባብነትና ቅንነት አጠያያቂ የሚያደርገው ነው፡፡
  • የለውጡ ተቃዋሚዎች ኅቡእ ስብሰባ እንደተካሄደበት የተዘገበው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ÷ የኅቡእ ስብሰባውን መካሔድ በማስተባበልና የኅቡእ ስብሰባውን ዓላማ በጽኑ በመቃወም ለለውጡ ተግባራዊነት ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እና ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ጽፈዋል፡፡

*                                 *                                *

  • በቀንደኛ የሀገረ ስብከቱ ሙሰኛ የአድባራት አለቆች፡- መልአከ ገነት ኃይሌ ኣብርሃ (ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስ (ኮተቤ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል)፣ መልአከ ብሥራት መልአክ አበባው (አፍሪቃ ኅብረት ቅዱስ ሚካኤል) እና ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ (የካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል) የሚመሩ ‹ተቃዋሚዎች›÷ ፓትርያርኩ ጥያቄዎቻቸውን የማይቀበሏቸው ከኾነ ‹‹የ[አቡነ] መርቆሬዎስ ደጋፊዎች ነን ብለን ሰልፍ እንወጣለን፤ መግለጫ እንሰጣለን›› እያሉ በፓትርያርኩ ላይ ሲዝቱ ውለዋል፤ ‹‹በቅዱስነትዎ ዘመን ደም እንዲፈስ ይፈልጋሉ ወይ? ይህ ጥናት የማይቆም ከኾነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እናሳውቃለን፤ ፐርሰንት አንከፍልም፤ ለሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች አስተዋፅኦ አናወጣም፤ የአባ እስጢፋኖስን ስም አንጠራም፤ ተገንጥለን በቦርድ እንተዳደራለን፤›› በማለትም የለውጥ ትግበራ ሂደቱን ለእነርሱ ብቻ በሚታያቸው ብጥብጥ የማወክና የማምመከን ዝንባሌና ውጥን እንዳላቸው ገልጠዋል፡፡
  • በፓትርያርኩ ጽ/ቤት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች፣ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ከሚገኙ ግለሰቦች ጋራ የጥቅምና ዓላማ ግንኙነት መፍጠራቸው የሚነገርላቸው ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ÷ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለጥናቱ አጸዳደቅ የሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ እንዲፈጸም መስማማታቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ‹‹ጥናቱን ይቃወማሉ›› በሚል ከፓትርያርኩና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋራ ለማጋጨት፣ በዚህም የተቋማዊ ለውጥ ሒደቱ ርስ በርሱ ተጠላልፎ የሚወድቅበትን ውጥን መዘርጋታቸው ተጠቁሟል፡፡ የመካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ የኾነው ሊቀ ትጉሃን ደነቀ ተሾመ በዋናነት የሚያስፈጽመው ነው የተባለው ይኸው ሊቃነ ጳጳሳቱን የመከፋፈል ውጥናቸውም፣ የውሳኔውን አፈጻጸም በመረጃ ደረጃ እየተከታተሉ የማያቋርጥ ምክር በመለገሥ ላይ የሚገኙትን እንደ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ያሉ የተቋማዊ ለውጥ ጠበቆችን ማስቆጣቱ ነው የተሰማው፡፡
  • ‹ቅሬታ› አቅራቢ የተቋማዊ ለውጥ ተቃዋሚዎቹ ከትላንት በስቲያው ምክራቸው በኋላ ለፓትርያርኩ አቀረቡት በተባለው አቤቱታ ‹‹ሙሉ የጥናት ሰነዱ›› እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህን እነርሱ ባይሉትም በየደረጃውና በየሞያ ዘርፉ በተለየ ኹኔታ በሚዘረጋው የሥልጠና መርሐ ግብር መሠረት ለየአብያተ ክርስቲያናቱ የሥራ ክፍሎች 13ቱም ጥራዞች እንደሚደርሱ በጥናታዊ ውይይቱ ላይ በተደጋጋሚ በመገለጽ ላይ ያለ ነው፡፡ ሊተኮርበት የሚገባው ግን፣ የጥናት ረቂቅ ሰነዱን በጋራ ውይይትና ግንዛቤ ለማዳበር የተዘረጋላቸውን መድረክ በአካል እየተገኙና አግባቡ እየተሳተፉ አስተዋፅኦ ባላደረጉበት፣ አንዳንዶቹም በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ተራቸው ደርሶ ባልተወያዩበትና ባልተሳተፉበት ኹኔታ ይህን ጥያቄ የማቅረባቸው መግፍኤ ነው፡፡
  • ከዚህ አኳያ በተወካዮቻቸው በእነ መልአከ ገነት ኃይሌና ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ አማካይነት በፓትርያርኩ፣ በረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና በቋሚ ሲኖዶስ አባላት ፊት ያቀረቡትን ‹ቅሬታ› በጥሞና ያዳመጡት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ‹‹ከዚህ የሚያደርሳችኹ ነገር አልነበረም፤ እዚህ ከመምጣታችኹ በፊት ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋራ መነጋገር ነበረባችኹ›› ሲሉ የሰጧቸው ምላሽ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ውሏቸውን በቅርበት የተከታተሉ ምንጮች እንደተናገሩት ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ፣ ‹‹ሙሉ ሰነዱን እንመረምራለን›› በሚል ዐቢይ ኮሚቴና ንኡሳን ኮሚቴዎችንም አዋቅረዋል፡፡

*              *             *

  • ‹‹በየሬስቶራንቱና በየሆቴሉ ከምትሰበሰቡ›› በሚል በተፈቀደላቸው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከትላንት በስቲያ፣ ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀትር ጀምሮ ሲመክሩ የዋሉት ከ60 የማይበልጡ ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በጦር ሜዳ የተሸነፈው የደርግ ርዝራዥ ነው፤ በጦር ሜዳ ገጥሞ ያልቻለውን ሥርዐት በሃይማኖት ገብቶ ሊጥለው ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አሠራር በጥናት ስም እየዘረጋ ነው፤ አሸባሪ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ባወጣው ደንብ አንመራም፤›› በማለት ከመሠረተ ቢስ ውንጀላ፣ ከጭፍን ጥላቻ እና ሕገ ወጥ ጥቅምን አስጠብቆ ለመኖር ከመፈለግ በቀር ለውጡን በግልጽ መድረክ በምክንያት ተደግፎ በሚቀርብ የአማራጭ ሐሳቦች ግብግብ የሚሟገቱበት መሬት የረገጠ መከራከርያ እንደሌላቸው አረጋግጠዋል፡፡
  • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና የባለሞያ ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ታደሰ አሰፋ÷ በጥናት ሰነድ ረቂቅ ዝግጅቱ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተቋም ያደረገው ተሳትፎ እንደሌለ በየጥናታዊ ውይይቶች ላይ ከባለሞያዎቹ ዝርዝር ማንነትና ስብጥር ጋራ ተደጋጋሚ መረጃዎች በመስጠት ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡
  • ከባለሞያ ቡድኑ መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መኖራቸው ርግጥ ቢኾንም ሀ/ስብከቱ የተጠቀመው ግለሰባዊ ዕውቀታቸውን/ሞያቸውን እንጂ የማኅበራቸውን መዋቅር እንዳልኾነ ለተወያዮች በተደጋጋሚ ሲገልጹ የቆዩት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ሰነዱን ማን አዘጋጀው ትታችኹ መሬት ወድቆ ብታገኙት አትጠቀሙበትም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ባለሞያዎቹ በመደበኛ ሥራቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚከፈላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች መኾናቸውን የጠቀሱት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጥናቱ የቤተ ክህነታችንን ችግር በቅርበትና በጥልቀት በማወቅ ላይ ተመሥርቶ በአጭር ጊዜ መከናወኑ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ከመኾኑም በላይ ከባለሞያ ክፍያ አንጻር ብቻ ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ወጭ የዳነበት መኾኑን አስረድተዋቸውም ነበር!!
  • በዚህ ረገድ የባለሞያ ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ታደሰ አሰፋ ከሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ተቃውሞ አይሉት ጥያቄ ጋራ ያደረጉት ምልልስ በተሳታፊዎች ዘንድ የጥቅስ ያህል የተያዘ ነው፡፡ የቤት እና የንግድ መኪኖች፣ ከአንድ በላይ መኖርያ ቤቶች ባለቤትነታቸው ብቻ ሳይኾን ከሽጉጥ ታጣቂነታቸው ጋራ በቁጣቸውና ለመነኮስ ከሚገባ አኗኗር መራቃቸው የሚታወቅላቸው የየካ ደብረ ሣህል ቅ/ሚካኤል አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በውይይቱ ወቅት ርስ በርሱ በሚምታታው አነጋገራቸው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሙስና ሙስና ትላላችኹ፤ ሙስና የለም! በልጆቻችን እንድንሠለጥን ያደርጉናል ወይ? ሕግ አያስፈልግም! ማንነታችኹ አይታወቅም፤ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አይደላችኹም፤ ልጅና ጎረቤት እኮ ልዩነት አለው፡፡››
  • አቶ ታደሰ ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በሰጡት አስተያየት፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በ፵ እና በ፹ ቀን በተፈጸመልን ጥምቀተ ክርስትና ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ልጅነት እኩል ነን እንጂ ልጅና ጎረቤት የለም፡፡ በዘመናችን የእግዚአብሔር የለሽ ፍልስፍና ስንቶች ፀረ ቤተ ክርስቲያን ኾነው ወጥተዋል፡፡ እኛ የሥላሴ ልጅነት ካገኘንባት ቤተ ክርስቲያን ሳንወጣ እዚህ በመገኘታችን መሰደብ አለብን?
  • እግዚአብሔር በሰጠን ዕውቀትና ሞያ ለቤተ ክርስቲያናችን መታዘዝ እንዳለብን እናምናለን፡፡ በግላችን ተጠርተንና ሞያችንን ዐሥራት አድርገን የሠራነው ጥናት የልጅነት ድርሻችንን የተወጣንበት የመታዘዝ ፍሬ ነው፡፡ እነሊቀ ሊቃውንት ደግሞ የጠመመውን ማቅናት፣ የጎደለውን መሙላት ይጠበቅባችኋል፡፡ ካልፈለጋችኹት ጋርቤጅ ውስጥ ጣሉት፤ ይጠቅማል ካላችኹ አሻሽሉት፡፡
  • ሊቀ ሊቃውንት እንደተናገሩት፣ በቤት ልጅና ጎረቤት ዘይቤ ከቀጠልን ግን ወደ 43.7% የወረደውና በዐሥር ሚልዮኖች ያጣነው የምእመናን ቁጥር ከ20% ወርዶም እናገኛዋለን፡፡ ሊዘነጉት የማይገባው ቁም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የሊቃውንትም የምእመናንም መኾኗን ነው!!››

Holy Synod direction on the A.A Change mgt.01Holy Synod direction on the A.A Change mgt.02