አዲሱ ነጠላ ዜማ፣ ድርድር ክንፉ አሰፋ

በሳውዲ የተነሳው የወገን ሰቆቃ ገና አልበረደም። ስቃዩ የበለጠ ሲከፋ እንጂ ሲቀንስ አላየንም። ለውጭ ምንዛሪ ማግኛ ሲባል ልክ እንደ ባርያ ንግድ በቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ በኩል የተላኩት ምስኪን ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በገዥው ፓርቲ እንደታሰበው አልሆነም። እንዲያውም ሌሎች መዘዞችን አስከትሎ መጥቷል። ዲያስፖራው እንደገና ተነሳ። ለቦንድ ግዢና ለግንቦት ሃያ በዓላት የሚሰባሰቡትም ጭምር ገዢው ፓርቲን ማውገዝ ጀመሩ። የስደተኛው ጎርፍም እንደሱናሚ ማእበል ያንን ጎራ ማጨናነቁ ግልጽ ነው። ወቅት እየጠበቀ የሚነሳው የክረምቱ ነቀርሳ አሁን በነበረከት ስምዖን ላይ ጠና ያለ ይመስላል። ይህ ህመም ማስታገሻ ያስፈልገዋል። ዘላቂ ሳይሆን ግዚያዊ ማስታገሻ። መቼም ለነቀርሳ ዘላቂ መፍትሄ የለውም። ለግዜው ግን እድሜ ማራዘሚያ … የድርድር ጥያቄ።

ጣላንያዊው የተንኮል ፖለቲካ ፈላስፋ ኒኮሎ ማኬቬሊ፣ (In Politics Timing is Everything) በፖለቲካ ታይሚንግ ኢዝ ኤቭሪቲንግ ነበር ያለው። ባላንጣን ለማጥቃት ወቅትን በተገቢው መጠቀም በፖለቲካ ትልቁን ስፍራ መያዙን ማኬቬሊ ዘ-ፕሪንስ በሚለው መድበሉ ይነግረናል።

በዚህ ፈላስፋ ጽንሰ-ሃሳብ የተካኑት ሰዎቻችን ታዲያ ወቅት እየጠበቁ ነጠላ ዜማ ይለቁልናል። አላማው በሚለቀቀው ነጠላ ዜማ እንድንዝናና ሳይሆን እንድንዘናጋ፤ ትኩረታችንን ከአንድ አቅጣጫ ነቅለን፤ ሃሳባችንን ሁሉ እነሱ በሚቆፍሩት ቦይ እንድንወስደው ለማድረግ ነው። በተለይ ደግሞ የዲያስፖራውን ስነ-ልቦና በደንብ አድርገው ስለበሉት አንዴ ሰበር ዜና ሌላ ግዜ ደግሞ ሰባራ ዜና እየላኩ ይቀልዱብናል። እኛም የነሱ መስመር ውስጥ ገብተን በሰበሩ ዜና ስንዘናጋ፣ በሳባራው ዜና ደግሞ ስንቆጭ ይሀው ሃያ አመት አስቆጠርናቸው።

የድርድሩ ጥያቄ ግን ትንሽ አስቆኛል። እንዲያውም እንድ ቀልድ አስታወሰኝ። ጸጋዬ ገብረመድን አርአያ በአንድ ወቅት በጦብያ መጽሄት ላይ አስፍሮት የነበረው ቀልድ ነው። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም በድንገት ተረበሹና የመንፈስ ጭንቀት ያዛቸው። ይህንን ያዩ ወዳጆቻቸው በመደናገጥ መፍትሄ መፈላለግ ያዙ። በመጨረሻም አንድ ሃሳብ መጣላቸው። በሰራዊቱ ውስጥ ሰዎችን በማዝናናት እና በቀልደኝነቱ የሚታውቅ አንድ አስር አለቃ መጥቶ ጓድ መንግስቱን በቀልድ እንዲያዝናናቸው ተወሰነ።

ወታደሩ ተጠርቶ ቤተመንግስት እንደገባ አይቶ የማያውቀውን ነገር በማየቱ ተደናገጠ። እየፈራም ወለሉ ላይ ቁጭ አለ። በዚህን ግዜ ኮ/ል መንግስቱ አዩትና “አይዞህ፤ አትፍራ። ከወለሉ ላይ ተነስና ሶፋው ላይ ቁጭ በል.. ቤቱ እንደሆነ የናንተው ነው። ይህ ቤተ መንግስት እኮ የህዝብ ቤት ነው።” አሉት።

በዚህ ግዜ ወታደሩ ከተቀመጠበት መሬት ላይ ብድግ አለና ሆዱን ይዞ መሳቅ ጀመረ። በወታደሩ ሁኔታ የተበሳጩት አንድ ሚኒስትር ቆጣ ብለው “ወንድም ጊዜ የለንም። ሳቁን አቁምና ቀልድህን ቀጥል!” ይሉታል። ወታደሩም መልሶ፣ “ጌታዬ እኔ ምኑን ቀለድኩት። እሳቸው ከኔ ባላይ ይቀልዱ የለም እንዴ?” አላቸው።

እርግጥ ነው። ሰዎች ስልጣን ላይ ሲቀመጡ ቀልድ ይጠፋባቸዋል። እናም በቁምነገር ላይ ይቀልዳሉ። ቀልዱ ከቁምነገሩ ተምታቶባቸው እንዳልሆነ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ድርድር፤ ለዚያውም የፖለቲካ ድርድር ምን እንደሆነ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። በእውነተኛ ድርድር እና በምርጫ ያለጥርጥር እንደሚሸነፉ ልቦናቸው ያውቀዋል። 17 አመታት ሙሉ በበረሃ የፈረስ ሽንት እየጠጣን የያዝነውን ስልጣን በሰላም አናስረክብም ብለው ከአንዴም አስር ግዜ ሊነግሩን ሞክረዋል።

የድርድር ፎርሙላ ቀላል ነው። ሰጥቶ መቀበል። በቃ!

ይህንን የድርድር ዜና የሰማ ወዳጄ ስልክ ደውሎ አንድ ቀልድ ነገረኝ። እኩለ ሌሊት ላይ ነው። አንድ ወንደላጤ አስተማሪ እቤቱ ውስጥ የሚንጓጓ ነገር ይሰማና ከእንቅልፉ ይነቃል። ከአልጋው ቀና ሲልም ሁለት ሌቦች ቤቱን ሲፈትሹ አያቸው። አስተማሪው ከአልጋው ተነሳና ባትሪ ይዞ ወደሌቦቹ ተጠጋ። ከዚያም ብርበራውን ያግዛቸው ጀመር። በሁኔታው የተገረመው አንደኛው ሌባ “ምን እያደረግክ ነው?” ሲል ጠየቀው። አስተማሪውም መልሶ “በቤቴ ምንም ነገር ስለሌለ አሳፍሮኝ ነው። ባይሆን ላግዛችሁና ከተገኘ ለሶስት እንካፈላለን።” አላቸው።

በእርግጥ በዚህ ነገር አይቀለድም። ቀልዱን እነሱ ከጀመሩት እኛም እንቀልድ ለማለት እንጂ። ድርድር እኮ አርቀው ከሚያስቡ መሪዎች የሚመነጭ ሃሳብ ነው። ሌላውን ሁሉ እንተወውና የሳውዲን መንግስት በመቃወም የወጡ ወገኖቻችን ላይ ባደረሱት ቅጥቀጣ ያፈሰሱት ደም እንኳን ገና አልደረቀም።
ድርድር አንድ ነገር ነው። በድርድሩ የበላይነትን ቦታ መያዝ ሌላ ነገር። እዚያ ላይ ነው ሰጥቶ መቀበል ጨዋታ የሚመጣው። መስጠት የሚችለው የጫወታውን ህግ ይወስናል። የፖለቲካ ድርድር እንደቤተሰብ ጸብ ይቅር ለእግዜር የሚባል ነገር አይደለም። እንደመንፈሳዊ እርቅ ለጽድቅ የሚደረግ ነገርም አይደለም። ምንም ሳይይዙ ለፖለቲካ ድርድር የሚቀርቡ – ይህንንም የሚያስቡ ካሉ የዋሆች ናቸው።
የሰጥቶ መቀበልን ነገር ካነሳን የሚታወሰን እ.ኤ.አ. በ1973 የቬትናም እና የአሜሪካን ጦርነት ያበቃው የፓሪስ ስምምነት፤ እንዲሁም በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ያለው የመሬት-ለሰላም ስምምነቶች ናቸው። የቬትናም ጦርነት የሰላም ውል ከመፈረሙ በፊት አንድ አወዛጋቢ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ቬትናሞች ከአሜሪካ ጋር ከመደራደራችን በፊት የምንቀመጥበት ጠረፔዛ ቅርጽ ማወቅ አለብን አሉ። አደራዳሪዎቹ ያቀረቡትን ባለ አራት ማእዘን ጠረፔዛ እንደማይቀበሉትም ቁርጡን ነገሯቸው። ቬትናሞች በክብ ጠረፔዛ ካልሆነ ከአሜሪካ ጋር ውይይት እንደማይደረግ አቛማቸው ግልጽ ነበር። ከወራት ድርድር በኋላ በክብ ጠረፔዛ ለመደራደር ተስማሙ። ያቺ ደቃቅ ሃገር ከሃያል ሃገር ጋር እኩል ለመደራደር ያስደፈራት ምክንያቱ፣ የምትሰጠው ነገር በመኖሩ ነው።
ቬትናም ምንም ነገር ሳትይዝ ለድርድር ብትቀርብ ውይይቱ የሚሆነው እንደ ዴቭድ ሌተርማን ሌት ናይት ሾው ነበር። እሱ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ እንግዳውን በአግዳሚ በማስቀመጥ፣ ከላይ ወደታች እያየና እየቀለደበት … አይነት ውይይት ነገር።

ለሃያልዋ እስራኤልም የፍልስጤምን ሰጥቶ መቀበል ጥያቄ መቀበል እንደትልቅ ሞት ነው። ሌላ አማራጭ ግን የለም። ሰላምን ለመቀበል መሬት መስጠት የግድ ነው። ይህ እንዲሆን ከእስራኤል ጎን የተሰለፉ ሃያላን መንግስታት የእስራኤልን እጅ መጠምዘዝ አያስፈልጋቸውም። ጥምዘዛውን ያካሄዱት ራሳቸው ፍልስጤማውያን የሚያካሂዱት እረፍት የሚነሳ፣ ሰላም የሚያውክ አመጽ እንጂ።
ደርግ ከህወሃት ጋር ለመደራደር አስቦትም አያውቅም ነበር። ህወሃቶች ጎንደርና ጎጃምን አልፈው ጅሩና ክምር ድንጋይ ሲደርሱ መንግስቱ መባነን ጀመረ። ‘ቆራጡ’ መሪ ወያኔዎቹ የያዙትን ሁሉ ይዘው ጉያው እስኪደርሱም የድርድር ጥሪ አላቀረበም ነበር። ሶስተኛ አካልን የድርድር ጥሪ ግን እንቢ ለማለት የማይችልበት ሁኔታ ተከሰተ። ምንም እንኳን ፈታኝ ሁኔታ ቢገጥመውም ለመደራደር የኽርማን ኮህን አማራጭ መቀበል ግድ ሆነበት። ደርግ በወቅቱ የድርድሩን የበላይነት ስፍራ ለቛል። በእርግጥም የሚቀበለው እንጂ የሚሰጠው ነገር አልነበረውም። እናም ጉልበቱ ተፈታ።…
የበሰሉ ሰዎች ችግርን ለመፍታትና ባላንጣን ለማሸነፍ ከሃይል(The hard way) ይልቅ ጥበብን (The smart way) ይመርጣሉ። በጥበብ የሚያምን አእምሮውን ያሰራል። አስቀከድሞ ጥቅምና ጉዳቱን ያስባል፣ ያመዛዝናል፣ ያገናዝብማል። ጉልበት ስላለው ብቻ አሸንፋለሁ ብሎ የሚያምነውን ደግሞ በመጨረሻ ሲወድቅ እናየዋለን።

የወያኔን ስርዓት በሃይል ለማስወገድ አስመራ የመሸጉ ሃይሎች ብዙ ናቸው። የአንዳንዶቹ ተቃውሚዎች አስመራ የገቡት የዛሬ 20 አመት ገደማ መሆኑ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ የአፍሪካን ሲንጋፖር ሊፈጥሩ ቃል በገቡበት ወቅት። ኤርትራ ሲንጋፖር ከሆነች እኛ ማሌዥያን አናጣትም ያሉ ነጻ አውጪዎችም አልጠፉም። እነሆ የተባለው ተዓምር ሳይፈጸም ሁለት አሰርት አመታት አለፉ። ኤርትራም ሲንጋፖር አልሆነች፣ የተቃዋሚ መሪዎቹም ከአስመራ ቪላ ቤታቸው ፈቀቅ አላሉም።

እንዲያው ለነገሩ እንጂ የአስመራውን ትግልና ታጋዮች ጉዳይ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሲሳይ አጌና ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ግልጽ አድርጎ ነግሮናል። “ከሌሎቹ ሲነጻጸር…” አለ አንዳርጋቸው “ከሌሎቹ ሲነጻጸር የአስመራው ትግል ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ጋር የሚወዳደር ነው።” በአስመራ ያሉ እነ ጀነራል እና ኮሎኔል እገሌ አምስት ኮከብን የት ሊያገኙዋት ይችላሉ? አዲስ አበባም ቢሆን በሙስና ካልሆነ እንዲሁ ሊያገኙዋት እንደማይችሉ ያውቃሉ። በምርጫና በህዝብ ይሁንታ ሳይሆን በመሳርያ ሃይል ስልጣን ይዘው ሚኒሊክ ቤተ-መንግስት ቢገቡም የቤተመንግስት እስረኛ ነው የሚሆኑት። እዚያው እያሉ አንድ ትውልድ አለፈ። ወይ የአስመራው አምስት ኮከብ ህይወት ተመችቷቸዋል፤ አልያም ኢሳያስ አፈወርቂ በረጅም ገመድ አስሮ ለቋቸዋል።

ህወሃት ለድርድር ሲጠራ የራሱ መለኪያ አለው። የበላይ ሆኖ ለመደራደር መስፈርቱን የሚያሟሉትን ከጠራ ግን በእርግጥም ተቀይሯል ያሰኛል። ህወሃት ሊቀየር ይችላል። ያንን መልካም ፈቃድ ለማስረገጥ ግን መጀመሪያ በእስር ላይ ያሉትን የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ይፍታ። በአዋጅ ያሰራቸው ጋዜጠኞች ነጻ ይሁኑ። በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወገኖች ይለቀቁ። አላማው የሰላም እና እርቅ ከሆነ ደግሞ፤ ጥሪው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁንና ብሄራዊ እርቅ ይፈጠር።