‹‹በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ተጀምሮ የቆመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሒሳብና የሥራው ሂደት በመንግሥት ባለሞያዎች እንዲመረመር ታዘዘ

Dire Dawa Saba Debre Hayel St. Gabriel Church

‹‹በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መገንባት›› በሚል በጥቅምት ወር ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ቢጀመርም ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በተዘፈቀበት ሙስና የተነሣ ሥራው ቆሞ የሚገኘው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

  • የሥራ ተቋራጩ በ2 ዓመት ጊዜና በ3 ሚልዮን ብር ወጪ ግንባታውን አጠናቅቆ ማስረከብ ነበረበት፤ ይኹንና የሥራው መጠን ከ65 በመቶ በላይ ባልተራመደበትና ከውለታ ጊዜው ውጭ ለ6 ዓመት በዘገየበት ኹኔታ አላግባብ በቀረበ የተቋራጩ የይገባኛል ጥያቄ ከብር 8 ሚልዮን በላይ ወጪ መከፈሉ ተጠቁሟል፡፡
  • ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት÷ በ3 ሚልዮን ብር በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ሕንፃ እስከ አሁን 8 ሚልዮን ብር ፈጀ መባሉ በርግጥም አጠራጣሪ ኾኖ ስለሚታይከጠቅላይ ቤተ ክህነት ታዛቢ ባለበት ከመንግሥት መ/ቤት ከሚገኙ ብቁ የሒሳብ ባለሞያዎች ወጪና ገቢው እንዲመረመርበሕንፃው ጥራት ላይም ባለሞያዎች ጭምር ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳላቸው የተገለጸ ስለኾነ ገለልተኛ በኾኑ የመንግሥት ሥራና ከተማ ልማት ባለሞያዎች የግንባታው ሂደት እንዲመረመር አዝዟል፡፡
  • ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በጥቅም የተሳሰረው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ እየጣሰ ለሰበካ ጉባኤው ባለመታዘዝ ከሚፈጽመው ምዝበራ ጋራ ተባብረዋል፤ በግንባታው ወጪና ገቢ፣ በሥራው ሂደትና ጥራት ላይ ጥያቄ የሚያነሡ የደብሩ አገልጋዮችን ደመወዝ በመቀነስ፣ ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግና በማዘዋወር ሲበደሉ፣ ምእመናኑ በፖሊቲከኝነትና በአሸባሪነት እየተወነጀሉ ሲሸማቀቁና አቤቱታቸው እንዳይሰማ ሲደረግ ሽፋን በመስጠት ችግሩን አባብሰዋል የተባሉት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ከሓላፊነታቸው ተነሥተዋል፡፡
Aba Aregawi Nemomesa

ከድሬዳዋ ሀ/ስብከት የሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነታቸው የተነሡት መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ

  • ለሁለት ዓመት ሀ/ስብከቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩት አባ አረጋዊ ነሞምሳ ወደ ሓላፊነት የመጡት፣ በታወቁት ሙሰኛ ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ ከሚመራው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ተለይተው የወጡ ተቆርቋሪዎች ያቋቋሙት ‹‹የምእመናን ተሟጋች ቡድን›› በሕንፃ ሥራው ሽፋን የሚካሄደውን ምዝበራና የተራቀቁ ወንጀሎች በማጋለጥ የፈጠረውን ንቅናቄ በመደገፍ የግንባታው ወጪና ገቢ በሀ/ስብከቱ ኦዲት እንዲደረግ ትእዛዝ የሰጡት የቀድሞው ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ናሁ ሠናይ በለጠ በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ አባ አረጋዊ ለሙሰኞች ሽፋን ከመስጠት ባሻገር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ከሀ/ስብከቱ በማፈናቀል በኑፋቄ የሚጠረጠሩና ግልጽ የምግባር ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች በመሰግሰግ በሀ/ስብከቱ አድባራት አስተዳደሮች ይተቻሉ፡፡
  • በዐሥር አባላት ተቋቁሞ የሀ/ስብከቱን የቀድሞ አስተዳደር ይኹንታ ያገኘው ‹‹የምእመናን ተሟጋች ቡድን›› ሥራ ከተጀመረበት ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. አንሥቶ ገቢና ወጪውን ኦዲት አድርጎ በ፳፻፬ ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ባቀረበው ሪፖርት ከውጭና ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበው አጠቃላይ ገንዘብ ብዛት ብር 11,388,096.23 በላይ መኾኑን አረጋግጧል፡፡ የሒሳብ ምርመራ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአሳማኝም ኾነ አሳማኝ ባልኾነ መንገድ በደረሰኝ የወጣው ወጪ 5 ሚልዮን ብር እንደኾነ ገልጾ ይህ ስሌት ከጠቅላላ ገቢው አንጻር ከ5 ሚልዮን ብር በላይ የገባበት እንደማይታወቅ አመልክቷል፡፡
  • በቋሚ ኮንስትራክሽን መተዳደርያ ደንብ መሠረት የዋጋ ግሽበት ጥያቄ ከሚመለከታቸው ሲሚንቶ፣ ብረትና ነዳጅ ካሉት ዋና ግብአቶች ውጭ አጠቃላይ የነጠላ ዋጋ ይሻሻልኝ ጥያቄ ከውለታ ጊዜው ውጭ ለዓመታት ለዘገየ የግንባታ ፕሮጀክት በማቅረብ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለሥራ ተቋራጭ እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ በዋናው ውል መሠረት የቅድሚያ ክፍያ የተከለከለ ቢኾንም የሥራ ተቋራጩ ምንም ዐይነት የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ሳያቀርብ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ከፍተኛ ገንዘብ በብድር ተሰጥቶታል፡፡ በተለይም ከነሐሴ ፳፻፪ ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ እጃቸውን ባስገቡት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ/አገልግሎት ሓላፊ አቶ ሰሎሞን ካሳዬና ከውድድር ውጭ በተቀጠረ ባለሞያ ሽፋን ሰጭነት ከፍተኛ ገንዘብ በቃል ትእዛዝ ተከፍሏል፡፡
  • ለግንባታው ያለክፍያ ሞያዊ አስተዋፅኦ የማበርከት ዕድል የተነፈጋቸው መሐንዲሶች የተካተቱበት ተሟጋች የምእመናን ቡድን ካካሄደው ምርመራ በመቀጠል በግንባታው ገቢና ወጪ ሁለተኛውን ኦዲት የሠራው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት ነበር፡፡ የአገልግሎቱ ባለሞያዎች ኦዲት ደግሞ በውጤቱ ለሥራ ተቋራጩ ከ1.8 ሚልዮን ብር በላይ ከውል ውጭ እንደተከፈላቸው ከማጋለጡም በላይ በጎ አድራጊዎች ለግንባታው በዐይነት የሚሰጣቸውና ማታ ታይተው ለጥዋት የማይገኙት ድንጋይ፣ አሸዋና ሲሚንቶ በገንዘብ ተተምነው እንደማይሰሉ አስረድቷል፡፡ ይኸው ጉድለት ከደንብና መመሪያ አንጻር ተገናዝቦ ማስተካከያ እንዲደረግበት ያሳሰቡት የወቅቱ የቁጥጥሩ አገልግሎት ሓላፊ በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ ከሓላፊነታቸው ከመነሣታቸው አልፎ ያለጊዜአቸውም በጡረታ እንዲገለሉ ተደርጓል፡፡
  • ለአሁኑ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ የኾነው ሦስተኛ ዙር ማጣራት በቀድሞው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት የተመራና አምስት አባላት ባሉት ልኡክ በኅዳር ወር ፳፻፭ ዓ.ም. የተካሄደ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች የቀረቡበት የማጣራት ሪፖርቱ÷ ከውለታ ጊዜው ውጭ አላግባብ በተፈጸሙ ክፍያዎች የተጋነነ ወጪ የወጣበት ግንባታ ሒሳብና የግንባታው ጥራት በገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር፣ ቃለ ዐዋዲውን ከማስከበር ይልቅ ለችግሩ መባባስ ተባብረዋል የተባሉትና በግንባታው ሽፋን ሕገ ወጥ መጠቃቀም እንደነበረ ለአጣሪው አካል ማመናቸው የተዘገበው ዋና ሥራ አስኪያጁ በሓላፊነታቸው መቀጠል እንደሌለባቸው፣ በቃለ ዐዋዲው ጥሰት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የደብሩ አስተዳዳሪ በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ የሚሉ የውሳኔ ሐሳቦች አቅርቧል፡፡
  • በሪፖርቱና የውሳኔ ሐሳቦቹ ላይ በስፋት መነጋገሩ የተገለጸው ቋሚ ሲኖዶስ÷ የግንባታው ወጪና ገቢ ከመንግሥት መ/ቤት ከሚገኙ ብቁ የሒሳብ ባለሞያዎች፣ በመስኩ ዐዋቂዎች ዘንድ ሳይቀር አጠራጣሪ የኾነው የሕንፃው ግንባታ ሂደትና ጥራት ደግሞ በሥራና ከተማ ልማት ባለሞያዎች እንዲመረምሩ፣ በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ ስለቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አጣርተው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡበት፣ የገለልተኛ ባለሞያዎች ምርመራ ተካሂዶ ውጤቱ እስኪታወቅ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በሀ/ስብከቱ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት አሳስቧል፡፡
  • የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስፈጸም በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በተጠራው የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ፣ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴና የተሟጋች ምእመናን ተወካዮች ምክክር፣ ‹‹ሰላም ፍጠሩ›› ብለው መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ውሳኔውን ማንም መሻርና ማስቀረት አይችልም፤›› ሲሉም ውሳኔው በተጨባጭ ርምጃ ሳይደገፍ እንደቀረው የቀደሙት ማጣራቶች እንደማይኾን ስጋታቸውን ላነሡት ተሟጋች ምእመናን አስታውቀዋል፡፡ የቤተ ክህነቱ ታዛቢዎችና የምእመናን ተወካዮች በታዛቢነት የሚገኙበትን የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋምም በዚሁ ሳምንት እንቅስቃሴ እንደሚጀመርና አስፈላጊው ወጪ በደብሩ እንደሚሸፈን ተገልጧል፡፡
  • በምክክሩ ላይ ‹‹ሲኖዶሱ ግራ ቀኙን ሳያይ በግብታዊነት ነው የወሰነው›› በማለት ትችት ለመሰንዘር የሞከሩት ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበርነታቸው የፈጽሟቸው የምዝበራና ተቆርቋሪዎችን በመሠረተ ቢስ ውንጀላዎች የማሸማቀቅ ተግባራት በግልጽ ተነሥተዋል፤ ተገሥጸዋልም፡፡ የሕግ ተጠያቂነታቸውስ?
  • የመንበረ ፓትርያርኩ የቁጥጥር አገልግሎት በአጣሪነት፣ በአንድ ሰው የሁሉንም የምሕንድስና ዘርፎች ዲዛየንና ቁጥጥር አደርጋለኹ የሚለው የምሕንድስና አገልግሎቱ በተቆጣጣሪነት የተከታተሉትና የተሳተፉበት የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የግንባታ ሒሳብ ምርመራና የግንባታ ሂደት ክትትል ሪፖርቶች ለቅ/ሲኖዶሱ የተሟላና ተአማኒ አለመኾናቸው መዋቅሮቹ ትክክለኛው አቅምና በቂ ቁጥር ባለው የሰው ኃይል እንዲጠናከ በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ዕቅድ ከዓመታዊ ሪፖርቶች ፍጆታ ባለፈ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡

Holy Synod decision on D.D St Gabriel bld01Holy Synod decision on D.D St. Gabriel church02