የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ይሆናል

ከዓለምአቀፍ የሲቪልና ፖለቲካዊ ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ
በሕወሀት/ኢህአዴግ ወቅታዊና ስር የሰደደ ጭቆና ላይ የወጣ አስቸኳይ የጋራ መግለጫ

እሁድ፡ መስከረም 18፡ 2004

የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ይሆናል!!

በሰሜን አሜሪካ የምንኖር፡ በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገል፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪል ማህበራት አባላትና ድጋፍ ሰጪ ማህበራት፡ ሰሞኑን የሕወሀት/ኢህአዴግ አፋኝ አገዛዝ፡ በጋዜጠኞች፡ የፖለቲካ መሪዎች፡ የጥበብ ሰዎችና ጋዜጠኞች ላይ እየወሰደ ባለው የእመቃ እርምጃ፡ በ“በቃ ንቅናቄ” የተዘጋጀ ለሰዓታት የዘለቀ፡ አስቸኳይ የስልክ ስበስባ አድርገን፤

የህወሀት/ኢህአዴግ የአዲስ ዓመት አዲስ ዙር እስራትን ስረ-መሰረት ተረድተን፤ የአረቡ ዓለም አመጽ ወደአፍሪካና ኢትዮጵያ በሚያደርገው መስፋፋት መሸበሩንና፡ አዲስ የወጣው የ“ጸረ-ሽብር ህግም” ሽብርን ለመዋጋት ሳይሆን፡ ማናቸውንም የሀሳብ ልዩነት ለማጥፋትና የነጻነት ታጋዮችን ለመወንጀል እንደሆነ ተገንዝበን፤

አገዛዙ ከሚለፍፈው የድርብ ቁጥር የምጣኔ-ሀብት እድገት በተቃራኒ፤ በከፍተኛ ስራ-አጥነት፡ በትምህረት ጥራት ጉድለት፡ ስር በሰደደ የከተማና የገጠር ድህነት፡ በዋጋ ግሽበት፡ በንጹህ ውሀ እጦት፡ በሙስና መንሰራፋት፡ በዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት መሬት መፈናቀል፡ በረሀብና ድርቅ፡ እንዲሁም በጥቂቶች የስርአቱ ደጋፊዎች ብልጽግናና በብዙዎች መደህየት፡ ተቆርቁረን፡

ጎሳን መሰረት ያደረገው የሕወሀት/ኢህአዴግ ማፊያና ቅጥረኛ ቡድን፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፡ ገበሬዎችን ለዘመናት ከኖሩቤት መሬት እያፈነቀለ፡ የከተማ መሬቶችንም ለራሱ የቅርብ የድርጅት አባላት በሚያደርገው እደላ ተቆጭተን፤

ከሀያ አመታት አገዛዝ በኋላም፡ በኢትዮጵያ በሚታየው አስደንጋጭ ድርቅና ረሀብ አዝነን፡ በተቃራኒው የህወሀት አገዛዝ በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ያለውን መጠነ-ሰፊ ረሀብና ግጭት ለመሸሸግ በሚያደርገው ጥረት፡ ይባስ ብሎም አለምአቀፍና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳይታዘቡ፡ የአገር ውስጥም ውጭም ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡት በሚያደርገው መሟሟት፡ ይሄንን ለመዘገብ በተጓዙት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ ባደረሰው ጉዳትና እስራት ተቆጥተን፤

የሕወሀት/ኢህአዴግ ስርአት አያሌ የሰብአዊ መብት ጥሰትና መንግስታዊ ሽብርተኝነት እየፈጸመ፡ የውጭ እርዳታንም ለፖለቲካ ጭቆና እንደሚጠቀም የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ እያለ፤ አሜሪካንን ጨምሮ፡ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም ምእራባዊያን መንግስታት ይሄንን ማስረጃ ችላ ብለው፡ ለሕወሀት/ኢህአዴግ አገዛዝ በሚሰጡት የገንዘብ እርዳታ በማዘን፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በ2004 አዲስ አመት መልእክት፡ ህዝቡ ለትግል እንዲነሳና የተነጠቀውን ነጻነት እንዲያስመልስ ያቀረበው የትግል ጥሪ በዋነኛዎቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ተቀባይነት ማግኘቱን ተገንዝበን፤

በአዲስ አበባ ለመስከረም 21፡ 2004 የተጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ ወቅታዊነት አድንቀንና የሕወሀት አፋኝ አገዛዝም የሰልፍ ፈቃድ መከልከሉ፡ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አብዮት፡ ወደ ኢትዮጵያም እየተስፋፋ መሆኑን እንደሚጠቁም አጢነን፡

በቅርብ ጊዜ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር ጋር በተያያዘ የሚደረገውን እንካሰላንቲያ አላስፈላጊነትና ከደጃፋችን የደረሰውን አብዮት ለመጠበቅ እንደማይጠቅም አስተውለን፡ የሕወሀትን ጎሳ-ተኮር አምባገነን አገዛዝ ለመጣል ለሚደረገው ትግል፡ የሁሉንም የፖለቲካ፡ ሲቪልና ማህበራዊ ሀይሎች እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተን፡

የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፈናል፡

(1)- የአንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲ፡ በ2004 የአዲስ አመት መልእክቱ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ 1966ቱ አብዮት፡ የፖለቲካ ድርጅቶች እስኪቀሰቅሱት ሳይጠብቅ፡ የተነጠቀውን ነጻነት ለማስመለስ ባንድነት እንዲነሳ ያቀረበውን የትግል ጥሪ ሙሉ በሙሉ አጽድቀናል።1

(2)- በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ለመስከረም 21 የተጠራውንና ወደፊትም የሚጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ሙሉ በሙሉ ደግፈን፡ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባቸው ዋና ዋና የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ከተሞችም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ ወስነናል።

(3)- በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያሉ ኢትዮጵያዊያን፡ የህወሀት/ኢህአዴግን አመራርና ቅጥረኛ አባላት እንዲያገሉ ጥሪ እያቀረብን፡ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም፡ የህወሀት/ኢህአዴግ ኤምባሲን አገልግሎት እንዲተዉ፤ ከሕወሀት ጋር የተዛመዱ የንግድ ድርጅቶችን፡ የአምልኮ ቦታዎችን፡ ማህበራትና ተቋማት መገልገል እንዲያቆሙም ጥሪ እናቀርባለን።

(4) የአሜሪካና የካናዳ መንግስታት፡ ከህወሀት/ኢህአዴግ አምባገነንና ህገ-ወጥ አገዛዝ ጋር ያላቸውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲቀይሩና፤ የሕወሀት አገዛዝ ጋሻጃግሬዎች በሰሜን አሜሪካ ያላቸውን የህዝብን ነጻነት የሚያውክ እንቅስቃሴ እንዲገድቡ ጥሪ እያቀረብን፤ የህወሀት ዘረኛ አመራሮች፡ መለስ ዜናዊ፡ በረከት ስምኦን፡ ሽመልስ ከማል፡ ዲና ሙፍቲ፡ ሬድዋን ሁሴን፡ ሀይለማሪያም ደሳለኝ፡ ስዩም መስፍን፡ ሀዜብ መስፍን፡ ሳሞራ የኑስ፡ ጌታቸው አሰፋ፡ አዲሱ ለገሰ፡ ብርሀነ ገብረክርስቶስና፡ ስብሀት ነጋ፡ በዘር ማጥፋት ወንጀልና ሰቆቃ በመፈጸም፡ በአለምአቀፉ የወንጀል ፍርድቤት ሊያቆማቸው የሚችል ጠንካራ ማስረጃ ስላል፡ ማናቸውንም የቪዛና ኮንሱላር አግልግሎት እንዲከለክሉ እንጠይቃለን።

(5) የአቶ ኦልባና ሌሊሳ፡ በቀለ ገርባ፡ ደበበ እሸቱ፡ አንዱአለም አራጌ፡ ዘመኑ ሞላ፡ ናትናኤል መኮንን፡ እስክንድር ነጋ፡ ርእዮት አለሙ፡ ውብሸት ታዬ፡ ሌሎችም የሕወሀት/ኢህአዴግ እስር ቤቶችን ያጣበቡትን የፖለቲካ እስረኞች እስራት አጥብቀን እያወገዝን፤ እነዚህ የጥበብ፡ የፖለቲካና ሰላማዊ ሰዎች የታሰሩበት ምክንያት የሀሰት፤ የታሰሩበት ህግም ዴሞክራሲን ለማፈን የወጣ አሸባሪና አፋኝ ህግ ስለሆነ፡ ህዝቡ ይሄንን ሕግ እንዳይታዘዝ፡ እስረኞቹም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም እንጠይቃለን። አለምአቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶችም እስረኞቹ በእስር ባሉበት ወቅት ምንም አይነት ድብደባና ሰቆቃ እንዳይፈጸምባቸው እንዲጎበኟቸው ጥሪ እአቀረብን፤ እኛም የእስረኞቹን ቤተሰቦች በሞራልና በቁሳቁስ እንደምንረዳ ወስነናል።

(6) የሲቪልና የፖለቲካ ድርጅቶችም፡ የተጋረጠባቸውን መሰናክል አስተውለው፡ ባስቸኳይ፡ ሁሉን አቀፍና ሰፊ የኢትዮጵያን የነጻነት ትግል የሚያፋጥን፡ የነጻነት ትግሉን ከግብ የሚያደርስ፡ እንዲሁም አገሪቱን ለብሄራዊ እርቅና ለሰላም፡ ለነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የሚያሰናዳ፡ ህግና ስርአትን የሚያስጠብቅ፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና ግዛታዉ ሉአላዊነት ወደ ሚያስከብር የአደራ መንግስት የሚወስድ፡ ጊዜያዊ ብሄራዊ ምክር ቤት ወይንም ሸንጎ (National Council) እንዲያቋቁሙ ጥሪ እናቀርባለን።

(7) ባደረግነው ስብሰባም፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለነጻነት፡ ለፍትሀና ለሕግ የበላይነት ለሚደረገው ትግል የማያወላዳ እገዛ ለማድረግ ቁርጠኝተነታችንን አድሰን፤ ይሄንንም ከግብ ለማድረስ፡ በአንድነት፡ ዓለም-አቀፍና መጠነ-ሰፊ የዲፕሎማሲ፡ የቁሳቁስ፡ የሀሳብና የሞራል ዘመቻ ለማድረግ ወስነናል። የህወሀትን ዘረኛ አስተዳደር፡ ሰላምን፡ ብልጽግናንና ነጻነትንነ በሚያመጣ ዴሞክራሲአዊ መንግስት ለመተካት በሚደረገው ትግል ላይ፡ ሁሉም የዴሞክራሲ ሀይሎች እንዲተባበሩም፡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።