ኤርትራ፣ አርበኞች ግንባር፣ ግንቦት ሰባት
ከአለቃ ተክሌ
የዛሬው ንባባችን ትንሽ መንገጫገጭ ሊበዛበት ስለሚችል ቀበቷችሁን አጥብቁ። ግንቦት ሰባት የምወደውና የምሳሳለት ድርጅት ነው። ለግንቦት ሰባት መቆም የገንዘብና የሀሳብ ካስማና ምሰሶ ካቀበሉት ሰዎች አንዱ ነኝ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ ክፍያ የፈጸምኩባቸውን ደረሰኞች ላሳይ እችላለሁ። በዚህ ዘመን በኛ እድሜ በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአመጽ ለውጥ መምጣት ካለበት፤ ቢከፋም ቢለማም ያንን የማሳካት አቅም ያለው ግንቦት ሰባት ብቻ ነው ባይ ነኝ። ያ እንዲሆን ስለምመኝም ነው ዛሬም በግንቦት ሰባት ላይ የተነሳሁበት። የተነሳሁለት። ሌላ አንድ በግንቦት ሰባት አመራር ዘንድ የሚዘወተር የማይገባኝ ነገር ተመልክቻለሁ። “እኛ በኢትዮጵያ ስም አንደራደርም” የሚባል ነገር። ይሄ የፍራቻ ምልክት የልበ ሙሉነት እጥረት ነው ባይ ነኝ። አንድ ድርጅት ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ይጠቅማል ካለ፤ በኢትዮጵያ ስምም የማይደራደርበት ምክንያት አይታየኝም። ማንም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሕዝብ ውክልና የተደራደረና የተዋዋለ መንግስትና ድርጅት የለም። ዋናው ነገር በርግጥም ውሉና ድርድሩ ለህዝቡ እንደሚጠቅም ማረጋገጡና ማድረጉ ላይ ነው።
አንዱ ይሄ አንደራደርበትም የሚባለው ነገር የኤርትራ ነገር ነው። ከኤርትራ ውጪ መዳን በማንም የለም ብዬ ከዚህ ቀደም ጽፌ ነበር። አሁንም እላለሁ፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ መጥፊያ ነች፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ መዳኛም ነች። ግንቦት ሰባት በግልጽ ባደባባይ ከኤርትራ መንግስት ጋር መነጋገርና መስራት ካልጀመረ፡ ሌሎች የስራ መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋልና ትግላችን እዚያው ባሉበት መርገጥ ነው ባይ ነኝ። በዚህ ጽሁፌ በዋንናነት የማብራራው ይሄንን ይሆናል። እግረ መንገድም ግን አንድ ስለአርበኞች ግንባር የተጻፈን ጽሁፍ በጨረፍታ እነካለሁ። በጸረ ወያኔ ትግሉ ውስጥ የጎረቤት መንግስት እገዛ ካስፈለገን፡ ያለችን ብቸኛ አጋር ኤርትራ ብቻ ነች። የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለማውጣት በሚደረግ ትግል ውስጥ ግንቦት ሰባትም ይሁኑ ሌሎች ሀይሎች ከኤርትራ ጋር በኢትዮጵያ ስምም ቢዋዋሉ፡ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው እስካልሰጡ ድረስ ምንም ጥፋትም ክፋትም የለውም ነው። ባህሩንም የባህሩንም በር አሳልፎ የሰጠ መንግስት አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ የለም እኛ በኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ላይ ከሌሎች ሀይላት ጋር አንዋዋልም፡ ሌላ ሽሽት ነው። መንገዳችን ኤርትራ ብቻ ነች። እነሆ ምክንያቶቼ።
ሕዝብ ምን አገባው?
አንደኛ ነገር ብርቱካንም ይሁኑ መለስ ለትግል ሲነሱ ሕዝቡ ታገሉልኝ ብሎ ፈቃድ ሰጥቷቸው አይደለም። የትግራይ ህዝብ ድንጋይ ተሸክሞ መለስንና ስዩምን እባካቸእሁ ነጻ አውጡኝ ብሎ የለመነበት ጊዜ አልተጻፈም። ራሴንም ህዝቡንም ነጻ ለማውጣት ስታገል ህዝቡ ተክሌ ሆይ እባክህን ጠብመንጃ ይዘህማ ይሁን ባፍህ ስለኔ ታገል ያለበት ቀን ትዝ አይለኝም (በነገራችን ላይ ስታገል ስል በሀሳብ ደረጃ ማለቴ ነው እንጂ አሁን ትግል ላይ ነኝ ማለቴ አይደለም)። እንዲያውም ትዝ የሚለኝ ቤተሰቦቼም ይሁን ዘመዶቻችን እንዲሁም ጎረቤቶቻቸን “ባክህ አርፈህ ኑር” እያሉ ሲያስፈራሩኝ ነው። አባቴም እናቴም ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መፈትፈቴን የደገፉበት ቀን የለም። ስለዚህ ግንቦት ሰባትም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ሲታገል በራሳቸው አነሳሽነት በተሰባሰቡ የበጎ ፈቃድ ታጋዮች እንጂ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን አድርግ ብሎ በቀባቸው ሰዎች አይደለም። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንፈልገውን ነጻነት ለማምጣት ከረዳ ከኤርትራ መንግስት ጋር ለመስራትም ይሁን ለመደራደር የኛ የራሳችን እምነት እንጂ የሕዝብ ውክልና አያስፈልገንም።
ይሄንን ሀሳብ ትንሽ ላጠንክረው። ልድገመውም። ከዚህ ቀደም እንደነገርኳችሁ አሁንም እንዳዝማች እንደምደግመው፡ ራሱን ጠላትን ብንወስደው የትግራይ ህዝብም ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም ቢሆን “ነጻ ታወጣን ዘንድ ይሁን” ብለው ፈቃድ አልሰጡትም። ሕወሀቶችም ይሁኑ ሻእቢያዎች በራሳቸው አነሳሽነት የተሰባሰቡ ሰዎችና ቡድኖች ናቸው። የኢትዮጵያንም ህዝብ ይሁን የትግራይን ህዝብ ሳያማክሩ ነው የራስን እድል በራስ መወሰን፡ በብሄር ብሄረሰቦች ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም፡ አዲስ ህገመንግስት፡ አዲስ መንግስት፡ አዲስ የመሬት ህግ፡ አዲስ አስተዳደር የመሰረቱት። በአባይም ይሁን በቀይ ባህር ሲደራደሩና ሲሰጡ በድብቅ ሳይሆን ባደባባይ፤ በአዋጅ ነው። ቀድሞም ይሁን ሲያደርጉት የኢትዮጵያ ህዝብ ደግፎላቸው አይደለም። እነሱም የኢትዮጵያ ህዝብ ደግፎናል አላሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍም አላስፈለጋቸውም። እኛ እናውቅላችኋለን ብለው ነው ያደረጉት። በትእቢትና በእብሪትም ባይሆን እንደዚያ ያለ ታጋይ ነው የሚያስፈልገን።
በጎ በሆነ መልኩ ግንቦት ሰባትና ሌሎች ድርጅቶችም (ያው በዚህ ዘመን ነፍስ ያለው ድርጅት ግንቦት ሰባት ነው) ማድረግ ያለባቸው ይሄንኑ ነው። በተወሰነ መልኩ እንደውም ግንቦት ሰባት ከሻእቢያና ከሕወሀት ይልቅ የሕዝብ ውክልና ያላቸው ወይንም የነበራቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው። ስለዚህ ለህዝብ ይበጃል ያሉትን ለማድረግ ምንም መጠራጠር አያስፈልግም። ምክንያቱም የምንታገለውም እኮ፡ ትግል ካልነው፡ ህዝቡ ሀሳቡ ይከበር በለን ነው፤ እንጂ የህዝቡን ሀሳብ አውቀነው አይደለም። ሕዝብ ሀሳቡ ቢከበርለት ደስ ይለዋል ብለን አምነን እንጂ፡ ሕዝብ ሀሳቡ ቢከበርለት እንደሚመርጥ ነግሮንና አሳውቆን አይደለም። ሌሎች ጉዳዮች ላይም፡ እኛን ከመሰለንና ለህዝቡ ይበጀዋል ብለን ካመንን፡ ህዝቡ ቢበጀውም ባይበጀውም ያንን የሚናገርበት እድል ሲያገኝ እኛ ይበጅሀል ያልነውን ማጽደቅ ወይንም መሻር ይችላል። እስከዚያው ግን እኛ ነን ይበጀዋል ወይንም አይበጀውም ማለት የምንችለው። እነጂ ሌላ የህዝብን ስሜት ማወቂያ መንገድ የለም።
ለነገሩ፡ ሕዝብ የሚበጀውን ያውቃል እንዴ?
ሌላው ነገር፡ ከፖለቲካ አንጻር ሕዝብ ብዙውን ግዜ የሚያስፈልገውን የሚያውቅም አይመስለኝም። ሀሳቡን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ምሁራን ወይንም ልሂቃን ካላብራሩለትና ካልተናገሩለት በስተቀር ተራው ህዝብ እንደው ያገር ፍቅር በሚለው ጥቅል ሀሳብ እንደሆነ እንጂ፡ “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ድረስ፣ የኦሮሞ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፣ ኢትዮጵያ የብሄሮች እስር ቤት ናት፣ ብሄር መሰረት ያደረገ ፌደሬሽን” ምናምን የሚሉትን ሀሳቦች ጠንቅቆና ተንትኖ ያውቃል ለማለት ይከብደኛል። አሁን ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንገት ነበረች ተቆርጣ ሄደች፣ ጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች ኢትዮጵያን ያለባህር በር አስቀሯት ከሚለው ድፍን ነገር ውጪ ከዚህ በኋላ የኤርትራና ኢትዮጵያ ግንኙነት እንዴት ነው መቀጠል ያለበት፤ ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚ ድርጅቶችስ ከኤርትራ ጋር ቢሰሩ ምን ጠቀሜታ አለው የሚለውን ጥያቄ ግራ ቀኙን አይቶ እንዲመልስ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ድርጅቶች ቀድመው ገብተውበት ካላገዙት በስተቀር ሕዝብ ቢጠቅመውም እንኩዋን “ምን ሲደረግ ከገንጣዮች ጋር” ሊል ይችላል።
የሆነ ሆኖ በጫካ እያሉ አንድኛው ሰላሳ፣ አንድኛው 17 አመታት፤ በስልጣንም 19 አመታት ይሄንን የመገንጠልና የነጻነት ጥያቄ ያነገቡ ሀይሎች ህዝቡን ስላሸነፉት፤ ህዝብ አሸናፊና መሪው እንዳረገው ነው የሚኖረውና ኖረ እንጂ፡ ሕዝብ ቢጠቅመውም መጠቀሙን ላያውቅ ይችላል። ስለዚህ ህዝብ ሀሳቡን ቢቃወምም እንኩዋን እንኳን፡ እንደ ግንቦት ሰባት ያለ ድርጅት አቋም ይዞ ይመራል እንጂ፡ ህዝብ ስላልወከለኝ በዚህ ነገር ላይ አቋም አልይዝም ማለት ጥርጣሬና ፍራቻ ይመስላል። ይሄንን ብል ይሄን ይሉኛል ይሄንን ብል ደግሞ ይሄን ይሉኛል አይነት ነገር። ስለዚህ በዚህ በኤርትራና በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ፡ እንዲሁም በባሀር በር ባለቤትነትና በወደብ አጠቃቀም ላይ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ነው የሚለውን በግልጽና በድፍረት አስቀምጦ ወደፊት መጓዝ ነው እንጂ፡ ህዝብ ይወስን ብሎ መተው የፖለቲካ ሽሽት ነው። የፖለቲካ ሽሽት እንደ ፖለቲካ ፍትወት አደገኛ ነው።
የጎረቤት እርዳታ፡ አንዳንድ መርሆች
መቼም የሚሰማኝ አጣሁ እንጂ ከዚህ በፊትም ቸክችሄያለሁ። ማንም የሌላን አገር መንግስት ተቃዋሚዎች የሚያስጠጋ መንግስትና አገር ያንን የሚያደርገው ለነፍሱ ብሎ ወይንም ሊጸድቅበት ብሎ አይደለም። ሱዳንና ሶማሊ ትናንት የኤርትራና የትግራይን ተቃዋሚዎች ቢያስጠጉ ለኢትዮጵያ ብለው አይደለም። ኢትዮጵያም ትናንት የሶማሊያና የሱዳንን ተቃዋሚዎች ብታስጠጋ ለነፍሷ ብላ አይደለም። እንዲያውም በዚህ ረገድ ደርግ ትንሽ ወደነፍሱ የተጠጋ ነበር። አንድ የሱዳን ነጻ አውጪ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ሟቹ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ግንባር መሪ ዮሃንስ ጋራንግ ከመገንጠል ይልቅ ከሱዳን ጋር መብታቸው የተጠበቀበትን አንድነት ይደግፍ ነበር ለተባለው ሀሳብ የተቃውሞ መልስ ሲሰጡ ዮሀንስ ጋራንግ ያንን ያደረገው የመገንጠልን ሀሳብ ሳይደግፍ ቀርቶ ሳይሆን የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ራሳቸው በወቅቱ የኤርትራን ተገንጣይ ሀይሎች ይዋጉ ስለነበር የሱዳንን መገነጣጠል አጥብቀው ይቃወሙ ነበር። ስለዚህ እነ ዮሀንስ ጋራንግ የመንግስቱን ድጋፍ ለማግኘት ሌላ ምርጫ ስላልነበራቸው ነው አንድነትን ይደግፉ የነበረው ብሏል።
ያም ሆነ ይህ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ራሱ የምንመለከተው፡ መንግስታት ለሌሎች አገራት ተቃዋሚዎች ርዳት ሲሰጡ የራሳቸውን ጥቅም ከግምት በማስገባት ነው እንጂ ለዛ አገር አስበውና ተቆርቁረው አይደለም። ስለዚህ ለአርበኞች ድርጅት መዳከም ወይንም ለአንድነት ድርጅቶች አለመጠንከር የኤርትራን መንግስት የሚከሱ ሀይሎች፡ አንዱ የተሳሳቱት የምለው ነገር፡ ኤርትራም ትሁን ሌሎች አገሮች ይሄንን ነገር ሲያደርጉ ለኢትዮጵያ ብለው አስበው እንደሚያደርጉ መገመታቸው ነው። ስህተት ነው። ኤርትራ ያንን የምታደርገው የራሷ ፍላጎት ስላላት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ኤርትራ በምትፈልገው መልኩ መስመር እንዲይዝ ማድረግ የኤርትራ ብሄራዊ ጥቅም ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎችን ስታስጠጋ፡ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም እስካልተጋፋ ድረስ ነው። ያንን ሳናውቅ ኤርትራ ከገባን፡ ያ የኛ ችግር ነው።
ሁለተኛ ነገር ማንም አገር የሌሎች አገር ተቃዋሚዎችን ወይንም ሽምቅ ተዋጊዎችን ሲያስጠጋ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ባስጠጋቸው ሀይሎች ላይ ቁጥጥር ማድረጉ አይቀርም። እኛም የሰው አገር ስንሄድ የዚያ አገር መንግስት እንግዶች ሆነን እንጂ ቱሪስቶች ሆነን አይደለም። መሳሪያን ያህል ነገር አስታጥቆ ሲልክ እነዚያ ሀይሎች የት ገቡ የት ደረሱ ብሎ መቆጣጠር የዚያ ሉአላዊ አገር መብትና ግዴታ ነው። እነዚያ በዚያ አገር የተወከሉ አገናኝ የጦር መኮንኖች የማሰኑና ምግባረ ብሉሹ ናቸው ብሎ መክሰስ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን በነዚያም ይሁን በራሳችን ምግባረ ብልሹ ሰዎች የተነሳ በሚመጣ ስህተትና ችግር የተነሳ ያን ያስጠቃ አገር መኮነንና ሆን ብሎ እንደሚፈጥረው አድርጎ መወንጀል አግባብ አይደለም። ኮሎኔል ፍጹም ወይንም ጄኔራል ስብሀት በሚፈጥረው የግል ብልሹ አሰራር የተነሳ ለዚያውም ከኛም በኩል ያሉ የተበላሹ ግለሰቦች አካሄድ ታክሎበት የዚያን አገር መንግስት በሙሉ መክሰስ ስህተት ነው። በተጨማሪም ነገር ያ አስጠጊ አገር፡ ለምሳሌ ኤርትራ የሚያስጠጋቸው ሀይሎች ጸረ-ኤርትራ አቋምና አጀንዳ እንዳይኖራቸው መቆጣጠር አለበት። ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር በተያያዘ አሁንም ቢሆን ወደ ኤርትራ የሚሄዱ ሀይሎች ባንድ በኩል የኤርትራን ሀብትና ቁስ እየተጠቀሙ በተቃራኒው ደግሞ ቀይ ባህርን እናስመልሳለን፤ ወይንም አሰብ የኛ ነው አይነት ዝማሬ የሚዘምሩ ከሆነ ያ መንግስት ከምንም በፊት የራሱን ህልውና መጠበቅና ማስጠበቅ አለበት። ቀላል ሎጂክ ነው። ያለበለዚያማ ያ መንግስት ቂል መንግስት ነው። ሻእቢያ ደግሞ ቂል አይደለም። አንዴ ተሸወደ። ሁለተኛ ግን አይሸወድም።
የኤርትራ ነገር፡ ያልተዘጋ መዝገብ
የኤርትራ መዝገብ እንዲህ በቀላሉ የሚዘጋ አይደለም። ንጉሱ አልዘጉትም። ደርግም አልዘጋውም። ሕወሀትም አልዘጋውም። እኛ ነን ልንዘጋው የሚገባው። ኤርትራ አትለቀንም። እኛም አንለቃትም። ይሄ ቀይ ባህር፣ የባህር በር፣ የባህር ወደብ፣ አሰብ፡ የአፋር ሕዝብ መብት፡ ገነመኔ የምንለውን ነገር ካላቆምንና እስከፈለጉት ድረስ ከነጻነታቸው ጋር በተያያዘ ግልጽ ማስተማመኛ እስካልሰጠናቸው ድረስ፡ በምንም መልኩ እነሱም በስጋት ውስጥ ከመኖር አይድኑም፤ እኛንም ማወካቸው አይቀርም። ለዚህ ነው ኢትዮጵያን ከሕወሀት አገዛዝ ነጻ አወጣለሁ ብሎ የሚታገል ድርጅትና መሪ በልበሙሉነት ሕዝብ ቢደግፈውም ባይደግፈውም የኤርትራን ነጻነት አውቆ፡ ይልቅስ እነሱም ነጻ ሆነው እኛም እንደሆነው ሆነን፡ ጎን ለጎን መኖር እንደምንችል መደራደር አለበት የምለው።
በዚህ ረገድ የአቶ አንዳርጋቸውንም፤ የዶ/ር ብርሀኑንንም “ግንቦት ሰባት የህዝብ ውክልና ስለሌለው በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ለመደራደርና የኢትዮጵያን ቋሚ ጥቅሞች የሚያስነካ ውል ለመዋዋል ምንም አይነት ሀሳብ የለውም” የሚሉትን ቃላቸውን አልወደድኩላቸውም (የጠቀስኩት ቃል በቃል አይደለም)። ግንቦት ሰባት ብቻ ሳይሆን ብዙ ግዜ ብዙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች አንዳንድ መሰራተዊ ብሄራዊ ጥያቄዎች ሲጠየቁ “እሱን ህዝብ ይወስን” የሚሉት ነገር አላቸው። ለምሳሌ መሬትን ውሰዱት። ወይንም የወደብን ጉዳይ። እንዴት ያበሽቁኛል መሰላችሁ። ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን የማያውቅ ድርጅት ሊያታግለኝ አይገባም። ቆይ ላሻሽለው። ቢያንስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይበጃል የሚለውን የማያውቅ ድርጅት ሊያታግለን አይገባም።
ወያኔዎቹ በዚህ ረገድ ይበልጡናል። ቢበጅም ባይበጅም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀው ይሄ ነው ብለው ይመራሉ። ዞሮ ዞሮ ወሳኙ ነገር አሸናፊነት ነው። አሸናፊ ሁሌም ቢሆን የሱ ሀሳብ ገዢ ነው። ሕወሀት፡ አይደለም ለኢትዮጵያ ህዝብ፡ ለትግራይም ሕዝብ የማይበጅና ቀደም ሲል የትግራይ ሕዝብ አጥብቆ የሚቃወመውን ዓላማና ፕሮግራም ይዞ ተንቀሳቀሰ። የህዝብ ድጋፍ ሳይሆን፡ ቁርጠኝነቱ ስለነበረ፡ አሸነፉ። የህዝብ ድጋፍ የግድ አይደለም። አንዳንዴ የሕዝብ ድጋፍ ኖሮም መሸነፍ አለ። ለምሳሌ የደርግ መንግስትን የኢትዮጵያን አንድነት አቋም አብላጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ይደግፈው ነበር። ያ ድጋፍ ግን ሕወሀትንና ሻእቢያን ከማሸነፍ አላቆማቸውም።
የኤርትራ ነገር፡ እኛም እነሱም
ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጋር በተያያዘ አቋሙን ግልጽና የጠራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ማሻሻልም አለበት። ዞሮ ዞሮ ማንም ድርጅት 80 ሚሊዮን ህዝብ ይደግፈኛል ይከተለኛልም ብሎ ለትግል አይነሳም። ስለዚህ የሚደግፈውም ደግፎት ቆርጦና አውቆት እንዲከተል፡ የሚቃወመውም የመሰለውን መንገድ እንዲቀይስ፡ ግንቦት ሰባት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀው፡ “የኤርትራን አገርነት አውቆ፣ የኤርትራን ሉአላዊነት አውቆ፣ በምንም መልኩ የወደብ አጠቃቀምን እንጂ የወደብ ባለቤትነትን ጥያቄ ሳያነሳ ከኤርትራ ጋር በሰላም በጎረቤትነት ለመኖር ወስኖ መኖር ነው ብሎ” መታገል አለበት። ኤርትራም ተመሳሳዩን ቃል ሰጥቶ “በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ላያደርግ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በጎረቤትነት በጋራ ትብብርና መከባበር እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ በምንም መልኩ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ላይገባ ተስማምቶ ለመስራት” ቃል ከሰጠ አለቀ። ወደፊት ማለት ነው።
ከዚህ በፊት በፖለቲካ ውስጥ መተማመን እንደሌለና እንደማይኖር ተናግሬያለሁ። ስለዚህ አንዱ ያንዱን ቃል ይመን ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ነገሩን እስኪ ዳር ይዛችሁ ተመልከቱት፤ ከዚያ ውጪ ምን ምርጫ አለ። ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ያለን ምርጫ፡ መተማመንና ነቅቶ መጠባበቅ ነው። የኢትዮጵያን ቋሚ ፍላጎትና ጥቅም የማያውቅ፡ እንዲህ መሆን ነው ያለበት ብሎ የማያምንና በዚያም የማያታግል ድርጅት ተጠራጣሪና ህዝቡ ስለሚፈልገው ነገር ርግጠኛ ያለሆነ ይመስላል። ስለዚህ ርገጠኛ ያለሆነ አታጋይ ድርጅት አያሸንፍም።
በድሮ በሬ ያረሰ የለም፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መፍረስ አታተርፍም
ከዚህ ቀደም ሻእቢያ ይታገልበት የነበረውን “ኢትዮጵያ ትጥፋ” መፈክርና ፕሮግራም ርሱት። እንኩዋን እኛ እነሱም ያንን ማንሳት ማስታወስ የሚፈልጉ አይመስለኝም። ካፈርኩ አይመልሰኝ እንጂ የኤርትራ ታጋዮችም ይሁኑ ኤርትራዊያን ራሳቸው ያሰቡትና የታገሉለት አሁን እየሆነ ካለው ጋር የሰማይና የምድር ያህል ሳይሆን የከርሰ ምድርና የሰማየ ሰማያትን ያህል የተራራቀ ነው። ኤርትራ ነጻ ወጥታ የአፍሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልእለ ሀያል መሆን ቀርቶ ልክ እንደኢትዮጵያ ራሷን መመገብ እንኩዋን የተቸገረችበት ደረጃ ላይ ነች። በነጻነታቸው ያገኙትን የመንፈስ ርካታ እንጃ እንጂ፤ በነጻነታቸው ያገኙት ቁሳዊ ርካታ ግን ከቶም እንደሌለ ራሳቸውም ሌሎችም ምስክሮች ይናገራሉ። አስራምናምን አመት ወጣቶችን ለሳዋ ማሰልጠኛ ማእከል እየገበሩ መኖርና ሁልግዜም ባሰቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ መኖር ምን አይነት ነጻነት ነው? ነገ ኤርትራ ልገባ ስለምችል ስለኤርትራ የነጻነት ተስፋና ቀቢጸ ተስፋ ብዙ ለማለት አልፈልግም። ደም ብቻ አይደለም ቂም ያቃባኛልና።
የሆነ ሆኖ እያመራሁ ያለሁት ባምናው ሳይሆን በዘንድሮው ስሌት ኤርትራዊያን ወይንም ሻእቢያ ከኢትዮጵያ መፍረስና መከፋፈል የሚያገኙት ምንም አይነት ቁሳዊ ጠቀሜታ የለም የሚል ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለሶስት ለአራት ተከፋፈለች፡ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራው፣ ምናምን እያለ ሄደ። ከዚያስ? እኔ ምንም አይታየኝም። ግድግዳ ብቻ እንጂ። እዚህ ካናዳ “ዴድ ኤንድ” የሚሉት አይነት ትራፊክ። አሜሪካም ሊሆን ይችላል። ኤርትራዊያን ይደሰቱ ይሆናል። ያ ግን ልክ እንደነጻነታቸው ባዶ ደስታ ነው። ስጋ የሌለው ባዶ ደስታ። አምባሻ የሌለው ደስታ። ስለዚህ ለኤርትራ የሚፈይደው ምንም አይነት ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ፋይዳ ስለሌለ፡ ሻእቢያ ይሄንን የኢትዮጵያን መገነጣጠል አይፈልገውም ባይ ነኝ። በርግጥም አንዳንድ ሰዎች ኤርትራን ጸረ-ኢትዮጵያ አድርገው ሲከሱ፡ ሻእቢያ ሰላሳ አመት ኢትዮጵያን ለማፍረስ መስራቱንና አሁንም አንዳንድ ጸረ-አንድነት ሀይሎችን በቤቱ ስለያዘ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ሻእቢያ ከኢትዮጵያ መፈራረስ ምን ያተርፋል ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አይሰጡም። ከዚህ ቀደም እንደጻፍኩት፡ በጅቡቲ ዞሮ፡ በአፋር ተሻግሮ፡ ትግሬውንና አማራውን ዘሎ፡ ከኦሮሞ ጋር ሊነግድ ነው? የማይመስል ነገር።
ኤርትራ የምትፈልጋት ኢትዮጵያ፡ አንድ ግን ደካማ
ከብዙ ኤርትራ ከርመው ከመጡ ጓደኞቼ ጋር ባደረግኩት ጨዋታ የተረዳሁት ሻእቢያ የሚፈልገው የኢትዮጵያን መፍረስ ሳይሆን፡ “ያለፈራረሰች ግን የደከመች፣ የማታሰጋ፣ እነሱ ኤርትራዊያን እየገቡ እየወጡ እየነገዱ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ነው”። ይህ እንዲሆን “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሰረተው መንግስት በተቻለ መጠን ርስ በርሱ የሚጠባበቅና የማይተማመን መንግስት እንዲሆን” ነው የሚፈልጉት። ለዚህም ይመስላል እስካሁንም ድረስ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ የትግራይ የምናምን አሁን በቅርቡ ደግሞ የአማራው ድርጅት ከቤታቸው አስቀምጠው የሚኖሩት። አኔ በዚያ ችግር የለብኝም። የተሻለ ምርጫ ስለሌለ ማለቴ ነው። ምክንያቱም እንደዚያ አይነት እንገነጠላለን የሚሉ ኢትዮጵያዊያን እስካሉ ድረስ ኤርትራዊያን እነሱን ቢያስተናግዷቸው ምን ያስደንቃል?
ለዚህ መድሀኒቱ ግልጽና አንድ ነው። ኤርትራን አስገድዶ ኢትዮጵያዊ ሀይሎችን አስገድዳ ባንድነት እንድታሰራ ለማድረግ ወይንም የማንፈልጋቸውን ጸረ-አንድነት ሀይሎች ገፍተን ለማስወጣት ወይንም ወደ ድርድር ለማምጣት፡ እኛ ራሳችን የአንድነት ሀይሎች የምንባለው ከኤርትራ ጋር ግልጽ፣ ያልተደበቀ፣ በከፍተኛ ልኡካን ደረጃ የተደራጀ፣ ያልተድበሰበሰ፣ ይሄ እንደ አርበኞች ግንባር የውጭ ኮሚቴ፡ የውስጥ ኮሚቴ ምናምን የሚባል ዝባዝንኬ የሌለበትና ሁሉም በእኩልነት የሚታገልበት ድርጅት መስርተን መግባት ነው። እንደው በዚህች ጽሁፍ ስንቱን ላንሳው እንጂ ያ ውሳኔያችን በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞን ቢያስነሳም፤ በተቃራኒው ግን በብዙዎችም ዘንድ “እነዚህ ሰዎች እውነትም ቆርጠዋል” ያሰኛልና ልንጋፈጠው ይገባል። ቢያንስ ተከታዮቻችንን ያበረታል። ድርጅቶች ደግሞ መጨነቅ ያለባቸው ስለተከታዮቻቸው ነው። የሚቃወምማ ሁልግዜም ለመቃወም እንዳሰፈሰፈ ነው። ተቃዋሚ እንደማር ነው። ቢመዝኑትም ሁሌ ያጎድላል፡ ቢጭኑትም ሁሌ ያጋድላል።
እኔ እንደዚያ ያለው ካርበኞች ግንባር ጋር በተያየዘ የተገለጸው አይነት ችግር እንዳይፈጠር ነው ከኤርትራ ጋር የሚደረግ ንግግር በግልጽና ባደባባይ በከፍተኛ ልኡካን ደረጃ ይሁን የምለው። እንደተባለው ወይ መታወቁ ላይቀር ምስጢር ሆኖ ላይዘልቅ ነገር አንዳርጋቸው ጽጌ የሙስሊሞች ቆብ እየደፋ በዚህ ገባ በዚህ ወጣ ከሚባል፡ ቀድሞውንም ያልኩት የግንቦት ሰባት ሰዎች በከፍተኛ ልኡክ ደረጃ ተሰባስበው ሄደው በግልጽ ከኤርትራ መንግስት ጋር ንግግር መጀመርና፡ መቀመጫቸውን ወደዚያ አዙረው ሌሎች ኢትዮጵያዊ ሀይሎችን አስተባብረው መንግስት መመስረት አለባቸው ነው። ከዚህ በፊት ያነሳሁትን ያየር ላይ ጥምረት ወደ ምድር ያውርዱት አይነት ለማለት ነው። ነገሮች ድብቅብቅ ሲደረጉና ምስጢር ሲሆኑ ነው ለአሉባልታ፣ ለሹክሹክታና ለተሳሳተ እንዲሁም ለተዛባ መረጃ መንገድ የሚከፍቱት። በግልጽና ባደባባይ ከተደረጉ ግን የሚቃወምም ይቃወማል የሚደግፍም ይደግፋል፡ ይቆርጥለታልም እንጂ ለሌላ አተካራና አሉባልታ መንገድ አይከፍትም። በቅርቡ ባርበኞች ግንባርና በግንቦት ሰባት እንዲሁም በሌሎች ኤርትራ ውስጥ ባሉ ሀይሎች ላይ የተጻፈው ጽሁፍ የሚያስተምረኝ ያንን የግልጽነትን አስፈላጊነት ነው።
ያርበኞች ግንባር ጉዳይና እኔ የጨመቅኩት ተሞክሮ
ስለአርበኞች ግንባር የተጻፈውን በቅጡ ቢቀናበር መጽሀፍ የሚወጣውን እውነት መሰልና የዋህ ጽሁፍ አነበብኩ።1 አብዛኛው ውስጥ ውስጡን እሰማው የነበረ ቢሆንም፡ በዚህ በተቀናበረ መልኩ ከውስጥ አዋቂ የተጻፈ ብዙ ገጽ መረጃ ሳይ የመጀመሪያዬ ነው። ከዚያ ሁሉ ጽሁፍ ውስጥ ጨምቄ ያወጣሁት ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ነው። አንደኛ የአርበኞች ግንባርና ሌሎች የአንድነት ሀይሎች አመራር አባላት፤ በተለይም ከውጭ አገር የሚመጡ የተልእኮ ታጋዮች ርስ በርሳቸው በሚፈጥሩት ሽኩቻና የስልጣን ግብግብ ምክንያት ትግሉ ተጎዳ ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር የተያያዘው ደግሞ የኤርትራ መንግስትን ወክለው የተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚያስተባብሩ ሰዎች በተንኮልና ሆን ብሎ ክፍፍልን በመፍጠር ትግሉ ወደፊት እንዳይራመድ አደረጉ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ኤርትራ ወያኔን ለማስፈራሪያነት ብቻ እንጂ በምንም መልኩ ኢትዮጵያዊ ሀይል ገፍቶና ጠንክሮ እንዲወጣ አይፈልግም የሚል ነው።
ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው ዝብዘባ ሁሉ ያስረዳኝ ይሄ ከላይ ያልኩትን ነው። እኔ ያ ስለአርበኞች ግንባር የተጻፈው ሁሉ እውነት ነው ወይስ ውሸት ብዬ አተካራና ምርምር ውስጥ አልገባም። ሁሉንም እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኩዋን ያ እውነት በምንም መልኩ ከኤርትራ መንግስት ጋር እንዳንሰራ አያደርግም። እንዲያውም ዋናው ችግር ያለው ከራሳችን በኩል እንደሆነ፣ ራሳችንን አጥርተን ብንቀርብ አሁንም ቢሆን ልንሰራ የምንችልበት እድል አለ የሚለውን ነው የሚያሳየኝ።
እንግዲህ እኔ ይሄ ነገር ያስረዳኝ የሚከተሉትን ነው። ስለመጀመሪያው ነጥብ። የቅርብ ጊዜ የራሳችንን የፖለቲካ ባህልና ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ፡ ሻእቢያ ወይንም እንደ ኮሎኔል ፍጹም ያሉ የሻእቢያ ተወካዮች ሳይኖሩና በነጻነት አገር እየኖርንም እኮ፡ ፖለቲከኞቻችን ርስ በርስ በመከፋፈልና በመሻኮት የተካኑ ናቸው። ለምሳሌ የቅንጅትን መከፋፈል ተመልከቱት። ወይንም የቅንጅት አለማቀፍን መከፋፈል። ያኔ ሻእቢያ ገብቶ አይደለም ያን ሁሉ የሰቀቀን ኑሮ የኖርነው። ወይንም መገናኘት ስላልተቻለ አይደለም ያ የሆነው። በስልክና ባካል እንዲሁም በኢሜል በደንብ መገናኘት እየቻልን ነው ርስ በርስ ስንሻኮት፡ ሲሻኮቱ የነበረው። ስለዚህ ፖለቲከኞቻችን በተለያየ ምክንያት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ርስ በርስ ሊሻኮቱ የሚችሉ ሴረኞች ስለሆኑ፡ የሻእቢያ ሰዎች መጨመር የሚያስፈልጋቸው አይደሉም።
በዚህ ነገር ውስጥ የኤርትራ ሰዎች እጅ የለበትም አልልም። ነገር ግን ያ ዋና ምክንያት ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ። አለበልና አንዳርጋቸው፤ መአዛውና ልኡል፤ መልኬና ዘውዳለም፤ ኤልያስና ግሩም፤ የሺና ስለሺ በርግጥም ጠንካሮች ከሆኑና የሚያስቀድሙት የግል የፖለቲካ ፍትወት ከሌለ በስተቀር የሻእቢያ ሰዎች ውስጣቸው መግባት ብዙ የሚያመጣው ለውጥ ሊኖር አይገባም ነበር። ባጠቃላይ ፖለቲከኞቻችን፡ የሻእቢያም ይሁን የሕወሀት ቅጥረኞች በሌሎበት ርስ በርስ መሻኮት ካላቆሙ፡ ሽኩቻውን በሻእቢያ ላይ ማላከክ አንድም የራስን ጥፋት ለመሸፈን ነው ሌላም ነጭ ውሸት ነው። ነጭ ውሸት እንዴት ያለ ነው ካላችሁ፡ እንደዚህ እንደላይኛው ያለ እላችኋለሁ። ያለሻእቢያም ጣልቃገብነት የምንራኮት ከሆነ ኤርትራ ምድር ላይ ሄደን ብንራኮት የግድ የመራኮታችን ምንጭ ሻእቢያ ነው ማለት አይደለም። የራሳችን ችግር በመጀመሪያ ራሳችን ነን። ቀጥሎ ሌሎች ናቸው። ወይንም ሊሆኑ ይችላሉ። ያጫሾችና የጠጪዎች ነገር ነው። መጀመሪያ አጪያሽ ነው ተጠያቂው። ከዚያ የሲጋራውን አምራቾች ይክሰስ።
እንደማጠቃለያ፡ ኤርትራ መንገዳችን
ባጠቃላይ ጥያቄው መሆን ያለበት፡ በእውኑ ከኤርትራ ተጠግተን ምን እናገኛለን ነው? እንዴትስ አድርገን የኤርትራን ስጋት እንቀንሰዋለን? ነው እንጂ፡ ሕወሀትን ለመውጋት ከኤርትራ ጋር መደራደር የሚለው ነገር ምንም ሀጢያትም ክፋትም የለበትም። እሱም ሁሉም ነገር አደጋ አለው። በካናዳ አውራ ጎዳናዎች መኪና ስናሽከረክርም ከአደጋ ነጻ ሆነን አይደለም። በመሰረቱ ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ከአደጋና ከተቃውሞ የጸዳ መንገድና መፍትሄ ያለው ካለ፡ እሱ ጻድቅ ነው። አንድ ነገር ግን ግልጽ ላድርግ፡ ከኤርትራ ጋር እንስራ ስል፡ እንደው የኢትዮጵያን ትግል ሁሉ ለኤርትራ አሳልፈን ሰጥተን፡ የዛሬ አስራ ዘጠኝ አመት እንደሆነው፡ አዲስ አበባ ድረስ በነሱ ድጋፍ እንግባ ማለቴ አይደለም። ያ አይሆንም። መሆንም የለበትም። ትግላችንን ባንድ ቅርጫት ውስጥ ብቻ አስቀምጠን ያ ቅርጫት ሲከሰከስ እኛም ሞራላችን ክሽክሽ የሚለው ነገር መቆም አለበት። የትግራይ ህዝብም በዚያ በኩል የሚያሳልፈን አይሆንም።
እኔ የምለው ከረጅም ግዜ ሀሳብና ማብሰልሰል፡ እንዲሁም አያሌ መላምቶችን ማገጣጠም በኋላ የደረስኩበት ስልት የሚከተለው ነው። በኤርትራ አጋዥነት፡ ህወሀትን ወደድርድር የሚያመጣና አገር ቤት ውስጥ ሰላማዊ ሽግግር እንዲፈጥር የሚያስገድድ ትግል መፍጠር እንችላለን ነው። ካለበለዚያ ግን፡ ሕወሀት እኛን በዝረራ እንዳሸነፈን፡ ሻእቢያንም በበቃኝ አሸንፎ፡ አንድ ያለችንን የኤርትራ አማራጭ ያጠፋብንና፡ መቼም ጭልምልም፡ ብሎብናል፡ ያው ጨርሶ ድፍንፍን ይልብናል። ይሄ ከየከተማው በምንለቃቅመው የሰቀቀን አስር ዶላር መዋጮ እንታገላለን የሚለው ነገር ብዙ አያራምደንም።
ብዙ የሚያወላዳ ባይሆንም፡ በኤርትራ በኩል መጓዙ፡ በወያኔ ላይ ግፊትና ጫና ከመፍጠር አንጻር፡ እውቅናና ዲፕሎማቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት፡ የምር ታጋዮች ለመምሰልና ወደ አገራችን የተጠጋን ለመሆን፡ ትግሉን የትርፍ ጊዜ ወይንም የቅንጦት ስራ ሳይሆን፡ የሙሉ ጊዜ ጉዳይ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የምንታገለው ሕወሀትም ይሁን የምንጠጋው ሻእቦያ፡ በአመታት የሙሉ ጊዜ ትግል የታወቁና የተሳካላቸው ናቸው። በኛ በኩል ደግሞ የጎደሉት ነገሮች እነዚያ ናቸው። የሙሉ ጊዜ ትግልና የሙሉ ጊዜ አጋር። ጎበዝ በዚያው በኤርትራ ገብተን ወይ እንግፋ ወይ እንጥፋ። ያለበለዚያ እኔ እየመረረኝ ነው። አሁንማ ትንሽ ወደኤምባሲው ቀረብ ብያለሁ፤ ያው ሶስት መቶ ካሬዬን ላፍ አድርጌ ወዲያውም እናቴንም አይቼ እመለሳለሁ። ቀልዴን ነው። ይህቺን የመጨረሻዋን እንኩዋን ያከልኳት፡ ወደ ሀሳብ ክርክር ሳይሆን ወደ ስብእና ዝንጠላ ለሚዘሉ ተሳዳቢዎች ስራ ለማቅለል ነው።
(ጨረስኩ)
አለቃ ተክሌ ነኝ። ቫንኩቨር/ኦታዋ፡ ካናዳ። መስከረም፡ 2003/2010