የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በ28 የመነጋገርያ አጀንዳዎች ውይይቱን ቀጥሏል
- የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በአጀንዳነት ተይዟል፤ ዐሥር አህጉረ ስብከት ተለይተዋል፡፡
- በተጭበረበረ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃና የዶክትሬት መመረቂያ ጥናትን አስመስሎ መቅዳት/plagiarism/ ክሥና ወቀሳ እየቀረበባቸው የሚገኙት፣ ሓላፊነትን በተገቢው ኹኔታ ባለመወጣትና በትጋት ባለመሥራት የተገመገሙት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በከባድ እምነት ማጉደል በተቀሰቀሰባቸው የካህናትና ምእመናን ተቃውሞ ከቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪነት የሚነሡት አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንንና የመሰሏቸው ቆሞሳት ከታሳቢ ዕጩዎች መካከል መገኘታቸው በምርጫው አግባብነት ላይ ጥያቄ አስነሥቷል፡፡
- ‹‹የምንሾማቸው ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይኾኑ የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራ ለመቀበል የተዘጋጁ ሊኾኑ ይገባል›› ከሚለው የፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ጋራ በቀጥታ የሚጣረስ አይደለምን? የቤተ ክርስቲያንንስ አመራር ከወቀሳ ያድናል?
- የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናትና የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ተግዳሮቶች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደራዊ ችግርና የሊቀ ጳጳሱ ዕጣ ፈንታ እንዲሁም በሊቃነ ጳጳሳቱ ዝርዝር እይታ ላይ የሚገኘው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ምልአተ ጉባኤውን በስፋት እንደሚያነጋግሩ ተጠቁሟል፡፡
- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንፃን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ያስተዳድራል፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ልዩ ልዩ ገቢዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ተካተው በሚመደብላቸው በጀት ብቻ ይሠራሉ፡፡
- በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከኦዲት ምርመራ ጋራ በተያያዘ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቀረበውን ግለሰባዊ ትችት ምልአተ ጉባኤው በከፍተኛ ድምፅ ውድቅ በማድረግ የዘገየው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ተጠናቆ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
- ሊቃነ ጳጳሳቱ በ‹‹መቻቻል›› ላይ የሰነዘሩት ትችት መንግሥትን አሳስቧል፤ የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋራ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፤ በደኅንነት ስም በየሊቃነ ጳጳሳቱ ቤት የሚዘዋወሩ ግለሰቦች ዝርዝር ለመንግሥት ይቀርባል፡፡
