“በህልሜ ከሌላ ወንድ ጋር ስትተኚ አይቻለሁ” በሚል ነፍሰጡር ሚስቱን የገደለው ሞት ተፈረደበት

“በህልሜ ከሌላ ወንድ ጋር ስትተኚ አይቻለሁ” በሚል ነፍሰ ጡር ሚስቱን በብረት በመደብደብና የሰውነት ክፍሏን በእሣት በማቃጠል የገደለው ግለሰብ፤ ከትናንት በስቲያ ሞት ተፈረደበት፡፡ መሐመድ ሃሰን የተባለው ጐልማሳ፤ መጋቢት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ነፍሰጡር ሚስቱን፤ “በህልሜ ከሌላ ወንድ ጋር ስትተኚ አይቼሻለሁ፤ ይህም እውነት ነው” በማለት፣ እግርና እጇን በገመድ አስሮ፣ በብረት ከደበደባት በኋላ የሰውነቷን የተለያዩ ክፍሎች በእሣት በማቃጠል፣ ፍፁም ጭካኔ በተሞላበት አኳሃን ገድሏል – ይላል የክስ መዝገቡ፡፡

ድርጊቱንም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ በመቀጠል ሟችን ሲያሰቃያት እንደዋለ በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ተከሳሹ ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ ቢሆንም አቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦበታል፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 20ኛ የወንጀል ችሎትም፤ ከትናንት በስቲያ በግለሰቡ ላይ የሞት ፍርድ ውሣኔ አስተላልፏል፡፡ሟችና ገዳይ፤ እድሜው 5 አመት የሆነ የአብራካቸው ክፋይ እንዳላቸውም ተገጿል፡፡