በዚህ ‹‹ክፉ ቀን›› ታሪክ ራሱን በመድገም የደርግን ዘመን አስታወሰኝ

በደርግ ‹‹ክፉ ቀን›› ለሰብዐዊ ዕርዳታ የሚውል እህል አሜሪካና ራሺያ ይልኩልን ነበር፡፡ በኢቲቪ፣ በሬዲዮና አዲስ ዘመን… መጠኑ የሚነገረን የአሜሪካው በሜትሪክ ቶን ሲሆን የራሺያው በኩንታል ነበር፡፡የአሜሪካውን አሳንሶ፣ የራሺያውን አብዝቶ የማሳየት ፕሮፖጋንዳ፡፡አሁንም ከሰሞኑ ከቻይና 163 ሚሊዮን ብር ፣ ከአሜሪካ 97 ሚሊዮን ዶላር፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት/ተመድ/ 17 ሚሊዮን ዶላር በረሃብ ለተጎዱት ዕርዳታ ተሰጠ የሚል አነበብኩ፡፡

አንድም የሁሉንም በአንድ ዓይነት መለኪያ ይንገሩን፤ በተሰጠው ካሬንሲ በዶላር ((8.15 ሚሊዮን ዶላር ከቻይና፣ 97 ሚሊዮን ዶላር ከአሜሪካ፣ 17 ሚሊዮን ዶላር ከተመድ) ያሊያም የሁሉንም መንዝረው በብር (ከቻይና 163 ሚሊዮን ብር ፣ከአሜሪካ 1.94 ቢሊዮን ብር፣ከተመድ 340 ሚሊዮን ብር) ይንገሩን፡፡ ያለበለዚያ ደግመን እንደ ደርግ ጊዜ አንሸወድም- በዚሁ መሰረት አሜሪካ የሰጠቺን የቻይናን 12 እጥፍ ሲሆን ፣የተመድም ቢሆን የቻይናን እጥፍ መሆኑ አይጠፋንም ፡፡

ለመጠርጠር ያህል ግን የቻይና በብር መገለጹ ቻይና ከዚሁ ከሰበሰበቺው ብር ነው መልሳ በብር የሰጠቺን ብለን ተነስተን፣ ‹‹የስጦታ ፈረስ ጥርስ ማየት›› እንዳይሆንብን ‹‹እጃቸውን ለዘረጉት›› ሁሉ ምስጋናችን ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ እንዲያው ለማስታወስ ያህል – በችግራቸው ወቅት ስንዴ የላክንላቸው እነ ጃፓን፣ ግብጽ… ምነው ድምጻቸው ጠፋሳ? ጨክነው ወይስ ለእኛ ባለስልጣናት ያልሰራነውን ለ‹‹ወያኔ ባለሥልጣናት›› የተንጣለለ ህንጻ ግንባታ መዋጮ አይመለከተንም ብለው?

ለማንኛውም ማመኑ ባይከፋም ልቤ ትንሽ ጠርጥር እንዲሉ ሆኖ እንጂ እነርሱ/ጃፓን፣ ግብጽ…/ ቢሰጡ እንኳ ስንዴው ይቅርና መያዣው/ማዳበሪያው/ ህንጻው ግንባታ አጠገብ እንዳይደርስ መከታተል ይችላሉ (ለጥበቃው የሰው ኃይል ከተፈለገ ይነገረን እንጂ ህንጻው ስር እያደርንም ቀን ከሌት እንጠብቀዋለን)፣ እናም አንጀታቸው እንዲራራ ሱባኤ መግባት ያስፈልግ ይሆን-እንደቅጠል ለሚረግፈው ወገን ምንም የመሆን ጊዜ ላይ በመሆናችን ፡፡ በመጨረሻም በእኛም ላይ ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ከ‹‹ክሽፈት›› ወጥተን ከእርጥባን መቀበል/ ተረጂነት ወደ ቀድሞው ‹‹የመስጠት/መለገስ›› የክብር ቦታችን ይመልሰን ዘንድ ለዚህም የበኩላችን ለማድረግ አብረን በኅብረት እንድንቆም ማስተዋሉን ይስጠን ፡