እኔ……….ወያኔ ነኝ (ሪያድ ኢብራሂም)
ሪያድ ኢብራሂም ከኖርዌይ
ለምታዉቁኝ በሙሉ
እኔ ወያኔ ነኝ ። በጡንቻየ የማስብ ፣በአግባቡ ህዝብን ከማስተዳደር ይልቅ በቆሎ መስፈሪያ እየሰፈርኩ በየወህኒው የማጉር ፣ ብእርን ከጦር መሳሪያ መለየት የተሳነኝ ብሎም ይህን እና ያሃን ጻፋችሁ ብዬ ብእረኞችን በሽብርተኛ ሂሳብ ወህኒ የማወራርድ ። ሲወርድ ሲዋረድ ከአያቱና ከቅመ አያቱ መሬቱን በውርስ ተረክቦ የእለት ተእለት ህይወቱን በግብርና የመሰረተውን መላውን የሀገሩን ገበሬ ከመሬቱ አፈናቅዬ ለባእዳን ባለሃብቶች የማከፋፍል … ያላሀፍረትም ከእንጀራው ያፈናቀልኩትን ህዝብ እድገቴን እይልኝ ስማልኝ ብዬ ቁምስቅል የማሳይ ። ‘’ያንተን ነገር አያሳየኝ ! ‘’ ያለኝን እግር ተወርች የምጠፍር ። ወጣቱን ሁሉ በሀገሩ ተስፋ እንዳይኖረው አድርጌ ፣ ግዛቴንም ስፋ አድርጌ በመያዝ መፈናፈኛ እያሳጣሁ ፣ ህዝቤን ሻሞ ብዬ ለባእድ ሃገራት የበተንኩ ፣ በትኜም ዜጋህ እንዲህ ሆነ ተብሎ አቤቱታ ሲቀርብብኝ በፍጹም የእኔ ሰው አይደለም ብዬ የምክድ ። መቼም ዘንግቶአቸው ይሆናል እንደማትሉ እገምታለሁ ! ሰው ሻሞ ብሎ በእጁ የበተነውን አይረሳምና ! ። ግን ! አለ…. አይደል ? የስሜ ነገር ያሳስበኛል ! ። ሱፍና ክራቫቴን ዥቅ አድርጌ ፣ ስብሰባ በየተጠራሁበት ቱልቱላየን መንፋቱ አልሆን ቢለኝ ፣ መጠቋቆሚያ መሆኑንስ በምን አቅሜ ?! ……ታድያ መካድ ይነሰኝ ? በወዲህ ደግሞ ሀገሬን አለቅም ፣ እምየን ለማንም ጅብ ትቼ አልሄድም ፣ ተጨንቄ በሀገሬ ልፈንዳ ያለውን አፍኜ ሌት ተቀን አለንጋ የምቀልብ ።
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ከሰውነቴ ይልቅ ጎጤን ያፈቀርኩ ። ለዘመናት በአንድ ስም ፣ በአንድ ማንነት ሲጠራ የነበረውን ህዝብ 80 ቦታ ለመክፈል የሞከርኩ ፣ ይህ አልበቃ ብሎኝ በጎጥ አባልቼ ቆሪጤን በደም ግብር እጅ ልነሳ እንቅልፍ ያጣሁ ። ህዝቡ አንድነቱን አፍቅሮ በጀ አልል ቢለኝ የደም ግብሩ ግድ ነውና ገሚሱን በጥይት ፣ ገሚሱን በወፌ ላላ ፣ ገሚሱን በረሃብ ፣ ገሚሱን በሰራሁት ተስፋ አስቆራጭ የኢኮኖሚ ድቀት በቁሙ እራሱን እንዲያቃጥል ፣ እንዲሰቅል የፈረድኩበት ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እኔ በተዋበ ቪላ ቁጭ ብዬ ጮማየን እየቆረጥኩ ፣ ውስኪየን በመለኪያ በቄንጥ ይዤ እየጨለጥኩ ፤ ፍርፋሪ የምወረውርላቸው ወሬ ነጋሪዎቼ ‘’ እንትን የተባለ አካባቢ እንቶኔ የተባለ ግለሰብ ኑሮ መሮት እራሱን ሰቀለ ፣ አቃጠለ ፤ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ በስደት ላይ ሳለ ባህር ዋጠው ‘’ ተብሎ ሲነገረኝ በክራንቻ ጥርሴ ከትትት ብየ እየሳቅኩ ጥጋብ እኮ ነው በማለት የምፈርድ ።
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ማስመሰልን ሙያዬ ያደረግሁ ። በተንጣለለ ቪላ በቴ ሆኜ በህዝብ ስቃይ ጮቤ እንዳልረገጥኩ …መቸም ለቀጪም ተቆጪ አለውና አንዱ የምእራቡ አለም መሪ ግዛቴን ሊጎበኝ ሲመጣ ህዝቤን በአንድ አዳር ባለመካከለኛ ገቢ አስመስዬ የምናገር ።አለፍ ሲልም በጎጥ ተደራጅቸ ያቆምኩትን የራሴን ፎቅ ፣ የሰራሁትን ፋብሪካ ወዘተ የማሳይ ፣ ውይይይ … የለየልኝ አስመሳይ እኮ ነኝ ! ህዝብህ ተርቧል የሚል ኣቤቱታ ሲቀርብብኝ አደራጅቸ ፍርፋሪ የማቃምሳቸውን (ቅንጥብጣቢ ወዝ ያላቸውን ) ካድሬዎቸን ከካሜራ ፊት የማቆም ።አቤት ስለ ፍትህና ደሞክራሲ ሲወራማ አይጣል ነው ! ድምጽ ማጉያው እስኪሰነጠቅ ማውራት ደስ ይለኛል ። የኋላ …ኋላ ‘’ የታለ?’’ ስባል ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ በት እወስደውና ድራማውን በመድረክ መሪነት ማሾሩን እቀጥላለሁ ።ከዚህ ወዲያ ዲሞክራሲ ከወደ የት?
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ለዘረፋዬ እውቅና የሰጠሁ ። አንዳንድ ሽብርተኞች በ5 ሺህ ብር የወር ደሞዝህ በምን ስሌት ይህን የሚያህል ህንጻ እና ፋብሪካ ልታቆም ቻልክ ብለው ብእራቸውን ሲያሾሉ እኔስ ምኔ ሞኝ ነው? ሁለተኛ እንዳይለመድ አድርጌ ከብረት ፍርግርጉ ጀርባ አስገብቼ አገላብጣቸዋለሁ ።ያኔ ፋታ ኣገኛለሁ :: ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዙ ብዬ ወደ ግል ኪሴ መክተቱንስ ማን አህሎኝ ? እንደውም አንዳንድ ጸረ ልማቶች እንደሚሉት… እንደ የቀድሞው ባለ 5 ሺህ ብር ደሞዝተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አይነት ልጅ በስሟ አንደተቀመጠላት ፤ በውጭ ባንኮች ያስቀመጥነውን ለመቁጠር የሚያስፈራ ገንዘብ ከቁጥር አስገብተውት ነው መሰል …. «እሱ ገንዘብ እኮ ወደ ሃገር ቢገባ ሰባት የህዳሴውን ግድብ አሰርቶ በቀሪው እነ መልካ ዋቀናን ፣ እነ ግልገል ጊቤን ወዘተ ገድቦ ውሃውን መፈናፈኛ ያሳጣው ነበር » በማለት ሃሜቱን እያጧጧፉት መሆኑን ስሰማ እነቅ… እነቅ ፣ ግደል…ግደል ፣ እሰር… እሰር የሚል አንዳች ስሜት ይወረኛል ።አንድም ከዚህ ወዲያ ጸረ ልማትነት ባለመኖሩ …. ሲቀጥል ህዝብን እና ገንዘብን ማፈን እንጂ ውሃን ማፈን የግልብ መሪ ወጉ ስላልሆነ ! ።
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ቀለም ያልዘለቀኝ ። «ህዝብ አልተማራችሁም ይለናል» ። ቆይ ትምህርት ማለት ከእስክርቢቶ ፣ ከወረቀትና ቱባ ከሆኑ መጻህፍት ጋር መዋል ብቻ ነው እንዴ ? እኔ እኮ በየበረሃ እና በየጫካው መሳሪያ ወልውሎ የመተኮስ የ40 አመት እውቀት አለኝ ፣ ተምሬም አላሳፈርኩ እስካሁን አንድ ተኩሼ የሳትኩት የለም ? ይህን ለመቁጠር እንደማትሰንፉ ስለማውቅ ግዳየን ማስቆጠር አይጠበቅብኝም ። ሀገር ደግሞ በመሳሪያ ስትመራ እንጂ በብእር ስትመራ ልፍስፍስ ትሆናለች ። ወኔ አይኖራትም ፣ ስልጣንም አይበረክትም ።
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ስልጣን የማልጠረቃ ። ምቀኞች ዙፋኑ ላይ ከተዘፈዘፍክ 25 አመት ሆነህ ይሉኛል ። አንድየን እላችኋለው ! 25 ቀንም የተቀመጥኩኝ አልመሰለኝ ። አቤትትትትት… ጊዜው ግን አንዴት ይበራል :: እንደቀልድ እኮ 25 ሆነኝ ስል ። ምቀኞች አፋቸውን አሹለው «ላንተ ነው እንደቀልድ ለኛ ግን እንደተራራ አልገፋ ብሎናል» ይሉኛል። ድሮም እኮ « የኛ ሰው ወርቅ ቢያነጥፉለት ፋንድያ ነው ይላል » ያሉት ኮሎነሉ ወደው አይደለም ። እስቲ ፍረዱኝ ? አጋድሜ ቀለሃ በቀለብኩ ፣ ብርድ እንዳይነካቸው ቃሊቲ ፣ ቂሊንጦና ዝዋይ በሰበሰብኩ ? …..?
አዎ ! እኔ ወያኔ ነኝ ። ያለ ትግል ከሞቀ ቪላየ የማልነቃነቅ። የህዝብ ብሶት ሰምቶ ማላገጥ እጅግ የሚያዝናናኝ ፣ ብሶት ወልዶት ጫካ ሊገባ ነው ስባል ብቻ ፣ ጆሮዬ እና ምላሴ የሚቆም ….. ብቻቻቻ… ምን አለፋችሁ ያለ ብረት አንዳች የማይገባኝ ። ይህን ያህል ስለራሴ ከነገርኳችሁ ይበቃል የተቀረውን በቅርቡ ከተጀመረው ከብረት አረሩ ምልልስ በህውላ ጭሱ ወደ መራኝ ሄጄ ፣ ካለሁበት ፤ ያለሁበትን ሁኔታ አወጋችኋለሁ ። እስከዛው ……… የ አመታት አስጨናቂ ቅዠታችሁ ከአራት ኪሎ ።[email protected]
The post እኔ……….ወያኔ ነኝ (ሪያድ ኢብራሂም) appeared first on ሳተናው (Satenaw)-Latest Ethiopian News & Breaking News.