የወያኔ ባለስልጣናት ከሕንድ ኢንቨስተሮች ጋር በመተባበር የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ተሰማርተዋል::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) – ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ እንደሚባለው ዜጎቹን የሚያስከብር መንግስት እና ሕግ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመት ስም እየተጠሩ ገንዘብ በብድር ተመድቦላቸው የሚመጡ የውጪ ሃገር ካምፓኒዎች ለወያኔ የፖለቲካ ፍጆታ ከመዋል በላይ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ብዝበዛ ሲያደርጉ መመልከት ያማል::በተለይ በሕጻናት ላይ የሚድረገው ብዝበዛ ቀኑን ጠብቆ ለዘገባ መብቃቱ እንዲሁም በሕገወጥ መልኩ የሚደረጉ የኢንቭስትመት ስራዎች በአገሪቱ ውስጥ ምን እየተደረገ እንዳለ በገሃድ ያሳያሉ::

ከሕንድ በኢንቨስትመት ስም ገብቶ በወያኔ ባለስልጣናት ድጋፍ እና አይዞህ ባይነት በጋምቤላ የሚገኘው የሕንድ ኩባንያ ቬርዳንታ ሐርቨስት ቀጥሮ ጉልበታቸውን ሲበዘብዝ ነበር የተባሉት አብዛኞቹ ሕፃናት ከሰባት ዓመት በታች እንደሆኑ፣ የተወሰኑት ደግሞ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 250 ሕፃናትን በመቅጠር ሲያሠራ መገኘቱን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡የአከባቢው ባለስልጣናት ቬርዳንታ ሐርቨስት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሕፃናቱን ጉልበት ሲበዘብዝ ቆይቷል ቢሉም ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት ግን መረጃው የለንም በሚል የድርጅቱን ሕገወጥ ስራ ለመሸፋፈን በመሞከር ላይ ናቸው::ቬርዳንታ ሐርቨስት ሕፃናቱ ከአቅማቸው በላይ የእርሻ ሥራዎችን፣ የምንጣሮ፣ የቁፋሮ፣ የቦይ ቀዳዳ ሲያሠራ መቆየቱ ታውቋል፡፡ይህም አልበቃ ብሎት ሕጻናቱን ክፍያ በመከልከል ባዶ እጃቸውን ይሸኛቸው ነበር::

ይኸው ድርጅት በጋምቤላ ሻይ ቅጠል ለማልማት ቢመጣም ከባለስልጣናት ጋር በመተባበር በደን ጭፍጨፋ ላይ ተሰማርቶ ጣውላዎችን ሲያመርት የነበር ቢሆንም በዚህ ወንጀሉ ሳይጠየቅ በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ በድጋሚ ቢገኝም ባለስልጣናት ከድርጅቱ ጎን ቆመው እየተከራከሩነት ይገኛሉ::የይህ ኩባንያ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጉማሬ ወረዳ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ 3,012 ሔክታር መሬት ለሻይ ቅጠል ልማት ቢሰጠውም ይህ ቦታ መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑ ተጠቅሶ መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢ ጉዳይ ተሟጋቾች ቅሬታ ቢያቀርቡም፣ መሬቱን የሰጠው ግብርና ሚኒስቴር ቦታው ላይ ያሉት ዛፎች ትልልቅ ሳይሆኑ ቁጥቋጦ ናቸው በማለት ሲቀርብ የነበረውን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ኩባንያው ጣውላ በሕገወጥ መንገድ ሲያመርት በመገኘቱ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ቢውሉም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ተለቀዋል::ከሦስት ዓመታት በኋላ ቬርዳንታ ሐርቨስት በዓለም አቀፍ ሕግጋትም በፅኑ የተከለከለውን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ማካሄዱ እና የወያኔ ባለስልጣንት ከጎኑ መቆማቸው በአካባቢው ቁጣ ቀስቅሷል::