አሳድ ህዝባቸውን በአንድ ጊዜ አስጨረሱት የኛዎቹ ግን ቀስ በቀስ! (የትነበርክ ታደለ)

የህዝብ የለውጥ መሻት እ.ኤ.አ. 2011 በሲሪያ ከገባ ጀምሮ ሚሊየኖች ሞቱ፣ ሚሊየኖች አካላቸው ጎደለ፣ ሚሊየኖች ሀገር ጥለው ተሰደዱ። የሀገሪቱ መሪ ጓድ አሳድ ግን ዛሬም ለዚህ እልቂት ምላሻቸው አንድና አንድ ብቻ ነው “እኔና እኔ ብቻ!” ዛሬ አለም የሲሪያውያንን እልቂት በየደቂቃው ይሰማል። መፍትሄ አልባው ጦርነትም እንዲሁ በዚህም በዝያም እየተደገፈ ቀጥሏል።

በተመሳሳይ ደግሞ የብዙ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች በስራአጥነት እና በነጻነት እጦት ሳቢያ በየጊዜው የመኖርያ ቄሄያቸውን እየለቀቁ ወደ ተለያዩ ሀገራት ይሰደዳሉ። ለዚህ ደግሞ የኛዋ ሀገር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት።

“አድገናል” እየተባለ ቀንና ማታ ዲስኩር ከሚደሰኮርባት ሀገራችን ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወጣቶች የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ መደጎም ተስኗቸው በየአቅጣጫው ይሰደዳሉ። ፊቱን ከቴሌቪዥን መስኮት ዞር የማያደርግ ተመልካች ወይም ጊዜውን በኢንተርኔት ድረ ገጾች ላይ የሚያሳልፍ ማንኛውም ሰው የሀገሩ ሰው ወንድ ሆነ ሴት በበረሀ ወይም በባህር የሚደርስባቸውን አሰቃቂ አደጋ በየቀኑ ማየት የተለመደ ነው።

እስከ ትናንትናው የዴይሊ ሜይል ዘገባ ድረስ ማንኛውም የቁሳቁስ ማመላለሻ ኮንቴነር ውስጥ ሰው ተያዘ ከተባለ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እየታዘብን ነው። በብዙ የአፍሪካ ሀገራት እስር ቤቶች ውስጥም ቢሆን ዜጎቻችንን በእስር ሲማቅቁ ማግኘት አስደናቂ ጉዳይ መሆኑ ቀርቷል። ~ ህገ ወጥ ስደተኞች ~ ኢትዮጵያውያን!

ለወገኖቻችን የስደት መንሰኤ ድህነት ብቻም አይደለም። 547 የፓርላማ ወንበር አንድ ፓርቲ ብቻውን በተቆጣጠረበትና *ዲሞክራሲያዊ መንግስት* የሚል ቅጥያ በተሰጠው አስተዳደር ውስጥ ዜጎች የመናገር ነጻነት የላቸውም። ጎረቤት ጎረቤቱን በሚሰልልባት ሀገራችን መንግስትን መጠየቅ፣ መንግስትን መሞገት፣ መንግስትን ልክ አይደለህም….ማለት ነውር ሳይሆን ወንጀል ነው።

ይህቺን የኔን ተራ ጽሁፍ እንኳ በዚህ ፌስ ቡክ ላይ ለመጻፍ የዘርአይ ደረስንና የአብረሀም ደቦጭን አይነት ጀግንነት ይጠይቃል። መጻፉ ይቅርና ይህን መሰል ጽሁፍ አንብቦ “ላይክ” ማድረግ በራሱ ታላቅ ወንጀል እንደሰሩ ለሊት ያስበረግጋል። ~ “ማን አይቶኝ ይሆን?”

እናም ህዝቦች ያለነጻነት መኖር ይጨንቃቸዋል። ለዚህም እግራቸውን ስበው የትውልድ ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። በዚህም ቁጥራቸው ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታ በየበረሀውና በየባህሩ ወድቀው ይቀራሉ፣ አካላቸው ይጎድላል፣ ኩላሊታቸው ተቆርጦ ይሸጣል…… ይህን የሚያይ የሚሰማ መንግስታችንም ያንኑ የተለመደ “በሀገራችሁ ሰርታችሁ ኑሩ!” የሚል “በራስ ንብረት ግብዣ” ከማቅረብ ውጪ “ለስደት ሁነኛው መፍትሄ ምንድነው?” የሚል መፍትሄ ለማምጣት ምንም ጥረት ሲያደርግ አናይም።

ለዚህም የሲሪያን ያህል አለም አያስተውለው እንጂ የኛም ወገኖች እልቂት ከዝያ የሚተናነስ አይደለም~~ ግን ቀስ በቀስ!!!