ህወሓቶች ያልተባለውን መጠምዘዝ ይወዳሉ…እናም ስም ማጥፋት ስራቸው ነው!
ህወሓቶች ያልሆነ ወሬ ሆን ብለው ለህዝብ ይበትናሉ። የተቃዋሚ መሪዎች ያልተናገሩት ነገር “እንዲህ ተናገሩ” እያሉ አሉባልታቸው ይነዛሉ፤ የፖለቲከኞች ስም ለማጥፋትና በህዝብ እንዲጠሉ ለማድረግ።
በ97ቱ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ፀረ ትግራይ ህዝብ” አስተያየት እንደሚሰጡ በካድሬዎች ይነገረን ነበር። “ፕሮፌሰር መስፍን መቐለ መጥተው ‘የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና ነው’ ብለው ሰደቡን” እያሉ የተሳሳተውን መረጃ በሰፊው ለህዝብ ተበተነ። ከምርጫው በኋላ ፕሮፌሰር መስፍን በትክክል የተናገሩትን ነገር እንዲነግረኝ ለአንድ ካድሬ ጓደኛዬ ጠየኩት። መጀመርያ ህወሓቶች ተዘጋጅተው፣ ተደራጅተው ቅንጅቶች የጠሩትን ስብሰባ ለመረበሽ ገቡ (የነገረኝ ካድሬ ከረብሻው አዘጋጆች አንዱ ነበር)። ስብሰባው ተረበሸ ::
በተደራጀ መልኩ ስብሰባ መረበሽ የህወሓቶች ስትራተጂ መሆኑ በደንብ አውቃለሁ። ምክንያቱም በነ ገብሩና አረጋሽም በ2002 ምርጫ ቅስቀሳ ቅንብሩ ተስርቷል። “ፕሮፌሰሩ ምን ነበር ያሉት?” ብዬ ደግሜ ጠየኩት። “ቃል በቃል አላስታውሰውም ግን ‘የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና አንድ ሊሆን አይችልም’ የሚል መልእክት ነበረው” አለኝ። “ታድያ ለምን የትግራይን ህዝብ ተሳደቡ አላቹ?” ጠየኩት። “ፖለቲካ ነዋ፣ ሽማግሌው ግን ሰራንለት! የት አባቱ!” ጨመረ።
ህወሓቶች ያልተባለውን መጠምዘዝ ይወዳሉ።እናም ስም ማጥፋት ስራቸው ነው። ፕሮፌሰር መስፍን “የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና አንድ ሊሆን አይችልም” ስላሉ ምንድነው ችግሩ? “ለትግራይ ህዝብ ‘ሳሙና’ ብለው ሰደቡት” ያስብላል??? እኛም (ለምሳሌ እኔ) የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ አይደሉም፤ ህዝብ አንድ ዓይነት አመለካከት ወይ አስተሳሰብ ሊኖረው አይችልም … እያልን ኮ ነው። ይህ ደግሞ ትክክል ነው።
Abraha Desta