አሳዛኙ ግድያ በታክሲ ሾፌርና ረዳት ላይ በቤተል
ነሀሴ 14, 1207 ዓ.ም የታክሲ ሾፌሩ ከነመኪናው ወደ ቤቱ አልትመለሰም፡፡ የመኖርያ ስፍራው ከወይራ ሰፈር ወደ ቤተል ሲኬድ ፓስታቤት አካባቢ በቅ/ጊዮርጊስ ክሊኒክ መግብያ 100ሜ ገባ ብሎ ነው፡፡ በነጋታውም የለም፡፡ ቤተሰቦቹ ተደናግጠው ለፖሊስ አመለከቱ። ፖሊስም ከአንድ ሳምንት የአሰሳና የምርመራ ቆይታ በሁዋላ በ20, 1207 ዓ.ም ይዞት የመጣው ዜና ግን የሾፌሩን ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን የቤተል እና አካባቢውን ነዋሪዎች ያስደነገጠና አንገት ያስደፋ ነበር፡፡
ኤፍሬም ተሾመ ገና የ23 አመት ወጣት ሲሆን የሚኒባስ ታክሲ በማሽከርከር ይተዳደራል፡፡ ስሙ ያልታወቀው የታክሲ ረዳት ደግሞ እድሜው ከ12-14 ብቻ የሚገመት ታዳጊ ህፃን ነው፡፡
የስራ ሰአት ማብቅያቸው ላይ የመጨረሻ ቢያጆ እንደሄዱ ኮንትራት ይጠየቃሉ። ጠያቂዎቹ አምስት ሲሆኑ “ቤተል ነዳጅ ማደያው ጀርባ ጋር ሰው እንጭናለን” ይላሉ። ኤፍሬምም ባለቀ ሰአት ጥሩ ስራ ተገኝ ብሎ ወደ ተባለው ስፍራ ታክሲውን ይዞ ገባ፡፡ ይሁንና ቢታይ የሚገባ ሰው የለም። አምስቱ ግለሰቦች በፍጥነት በገመድ ሾፌሩንና እረዳቱን አንቀው ይገድላሉ፡፡ ከዛም አስከሬኑን ይዘው ወደ ገፈርሳ በማምራት ድልድይ ውስጥ ይጥሏቸዋል፡፡
የቤተሰቡ አባላት ይህ መረጃ የተነገራቸው ከአምስቱ ተጠርጣሪዎች ምካከል ሁለቱን በቁጥጥር ስር በማዋሉ እና ድርጊታቸውንም ስለተናገሩ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ሰዐት ድረስ የሟች ሰፈር ልጆች የገፈርሳ ነዋሪ እና ፖሊስ አስከሬኑን እየፈለጉ ቢሆንም ማግኘት አልተቻለም፡፡ የዘረፋትን መኪና ለመሸጥ በማስማማት ላይ እንደነበሩም ተነግሯል።
ሀዘን የተቀመጡት የሾፌሩ ቤተሰቦች መኖርያ በማምራትም ህብረተሰቡ በማፅናናት ላይ ይገኛል። ፓሊስም ቀሪ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን እያደነ ይገኛል፡፡ ምርመራው መስመር ከያዘ በሁዋላ ይፋዊ መግለጫ መርማሪ ቡድኑ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን፡፡
ሁሉ አዲስ – በብስራት ኤፍ ኤም 101.1