መለስ የሞተው 100 ፐርሰንት ነው ( ሄኖክ የሺጥላ )

መለስ የሞተው 100 ፐርሰንት ነው ( ሄኖክ የሺጥላ )

ህወሓት ምርጫውን 100 ፐርሰንት እንዳሸነፈ ሁሉ ፣ የመለስንም ሞት 100 ፐርሰንት እንደሆነ ያሳውቅልን ! እስከሚገባን መለስ የሞተው 100 ፐርሰንት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መድረክም ይሁን ሰማያዊ ፣ የስላሴ ቤ/ክርስቲያን የመለስን ሞት አጭበርብሯል ብሎ ክስ እንዳላሰማ አውቃለሁ ።
ጉዳዩን የያዘው ምርጫ ቦርድ ከሆነም ፣ የተለመደው ቅንነቱ አይለየን ።

ቀዳማዊ እመቤቲቱ እንኳ ፣ ሞት ብርቅ ሆኖባት እንዴት ምርር ብላ እንዳለቀሰች ረሳችሁት እንዴ ? << ይህ የመለስ ቤት ነው !>> እያለች ስታሳየን፣ ፈልገን ያጣነው ይመስል ። እኛ ሴትዮ ተረስተዋችሁ ነው << አንበሳ ሐወይ !>> እያሉ ሲፎክሩ የነበሩት ። ምን ዋጋ አለው ፣ << ከሞተ አንበሳ የቆመ ፣ ጥንብ አንሳ ይሻላል >>። ለነገሩ እውነት እናውራ ከተባለ ፣ እሱ እንኳ አንበሳ ፣ አንባዛም አልነበረ ።

ለማንኛውም መለስ ሞቷል ። ደሞ መሞት ያን ያህል ብርቅ አይደለም ። ነብዩስ ሞቶ የለም እንዴ ? አሰፋ ማሩስ ሞቶ የለም እንዴ ? አስራት ወልደየሥ ሞቶ የለም እንዴ ? የኔሰው ገብሬስ ሞቶ የለም እንዴ ? እኛን ያስቸገረን ፣ << መለስ እንደ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚያብሔር ጋር አደረገ >> ለማለት የሚዳዳቸው ናቸው ። በይበልጥ ደሞ የሚያበሽቀኝ ፣ እንዲህ በሰው ሀገር ፣ ሀዘኑ ሳይወጣልኝ ፣ እያስታወሱ የምያሰቃዩኝ ወዳጅ ተብዬዎቹ ።

በነገራችን ላይ ያን ሰሞን የኔ ሰው ራሱን ባቃጠለ ጊዜ ፣ እኝህ ሟች << እብድ ስለሆነ ነው >> ብለውን ነበር። ታዲያ እንደው እሳቸው ምን ነክቷቸው አበዱ ?

ለማንኛውም ፣ መለስ ቢነሳ ኖሮ ፣ የዛሬ ሶስት ዓመት ፣ ሀገር ደረት ሲደልቅለት በተነሳ ። ግን ምን ያረጋል ሞቶ ፐርሰንት ነው የሞተው ! አይነሳም ።
በታሪክ ውስጥ በአንድም በጎ ነገር አንስታውሰውም ፣ ግን ደሞ በደሉን አንረሳውም !

ግዜ ለኩሉ !