እኔስ ከማን ወገን ነኝ? (የትነበርክ ታደለ)
እኔስ ከማን ወገን ነኝ?
(የትነበርክ ታደለ)
ከጥቂት አመታት በፊት ኑሮዬን ለመደጎም ስል ከመደበኛው የማስተማር ሰአት ውጪ ያለውን ጊዜ ሰው ቤት እየሄድኩ ተማሪ አስጠና ነበር። በነዚህ ጊዜያት ምንም እንኳ የማገኘው ገንዘብ ከዋናው ደሞዜ አንጻር ሲታይ በእጅጉ የተሻለ ይሁን እንጂ ብዙ ለህሊናዬም ለክብሬም የማይሆኑ ነገሮችን ታዝብያለሁ።
(በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በግል ትምህርትቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን አብዛኞቹ የሚገዳደራቸውን ኑሮ ተቋቁመው የሚኖሩት በትርፍ ሰአት ቤት ለቤት በማስጠናት ነው። ትምህርት ቤቶቹም መምህራንን ሲቀጥሩ ይህንን ገቢያቸውን ታሳቢ በማድረግ የቅጥር ደሞዙን ዝቅ አድርገው ነው የሚጠሩት።
እናላችሁ ሁለት ወንድማማቾችን አስጠናለሁ። የአስራ ሁለትና የአስር አመት እድሜ ያላቸው ተማሪዎቼ። እነዚህ ልጆች ትምህርት ቤቱ በሚያቀርበው መጽሀፍ ላይ ባለ ትምህርት የሚወዳደራቸው የለም። ነገር ግን ከዚያ ወጣ ያለ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ሀገራዊ ጥያቄ ብትጠይቋቸው ድንግርግራቸው ነው የሚወጣው።
እና እኔ በግሌ አንዳንድ ታሪኮችን እንደ ተረት እያደረኩ እነግራቸዋለሁ። ላሊበላን ማን ሰራው? ፋሲል ግንብ እንዴት ተገነባ? አበበ ቢቂላ ማን ነው? አባይ ወንዝ የሀገራችን ነው……ወዘተ።
መኝታ ቤታቸው የተሞላው በስፓይደርማን ፊልሞች፣ ሀሪፖተር መጻህፍት፣ ጌሞች፣ እንዲሁም የሚገጣጠሙ የአሜሪካ ካርታ ናቸው። የመኖሪያ ጊቢው ውስጥ ሰፊ የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳ አለ። ልጆቹ በእረፍት ጊዜያቸው እዚሁ ሜዳ ላይ ቢስክሊት ሲጋልቡ ይውላሉ።
እኔ በህይወቴ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የሀብታም መኖርያ ቤት አያለሁ ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም። በኤም ቲቪ የሚቀርቡት የአሜሪካ ታዋቂ ዘፋኞችን መኖሪያ ቤቶች የሚያቀርበው “ክሪፕስ” ላይ እንኳን ሳይ አምሮዬ እውነት ነው ብሎ አይቀበልልኝም ነበር። አልኖኩበትማ!
ልጆቹን ከትምህርት ቤት ለመውሰድ አንዳንድ ጊዜ ሶስት መኪኖች ይመጣሉ። እናት በራስዋ መኪና፣ አባትም እንዲሁ፣ የልጆቹ አመላላሽ ሾፌሩ በሌላ በኩል። እኔ የሚኪና ብራንድ ስም ስለማልይዝ ነው እንጂ እነዚህ መኪኖች ወደ ትምህርት ቤቱ ሲመጡ መምህራን ለማየት ተሯሩጠው እንደሚወጡ አስታውሳለሁ።
ያው እኔ ደግሞ ልጆቹ ወደ ቤት ከሄዱ በኋዋላ ካለኝ ታክሲዬን ይዤ ከሌለኝ በእግሬ ፈጠን ፈጠን እያልኩ እሄዳለሁ። ካረፈድኩ ልጆቹ ከመክሰስ በኋዋላ ወደ ቅርጫት ኳስ ሜዳ ይሄዱብኝና ሳላስጠና መመለሴ ነው። (ልጆቹን ኑ አጥኑ! ብሎ ማስገደድ ክልክል ነዋው) ያ ማለት ደግሞ ለኔ ኪሳራ ነው። እና መሮጥ ይኖርብኛል። እዚያ ስደርስ ልጆቹ እየበሉ አገኛቸዋለሁ። ሲጨርሱ ተጣጥበው ወደ ጥናታችን።
ልጆቹ በጥናት ሰአት አማርኛን በደምብ ከኔ ጋር ማውራት ስለሚችሉ በጥቂቱም ቢሆን በኔ መምጣት ይጓጓሉ። ምክንያቱም ትምህርት ቤት ውስጥ አማርኛ ማውራት በፍጹም አይፈቀድልንም። ድንገት ስናወራ ከተገኘን እኔም ደሞዜን እቀጣለሁ። ልጆቹም የጨዋታ ሰአታቸውን አዳራሽ ውስጥ እንዲቀመጡ በማድረግ ይቀጣሉ። በጥናት ሰአት ግን እኔ ስናገር መስማት በራሱ ለነሱ ትንግርት ነው። እነሱማ አንደኛውኑ የአማርኛ አፋቸው ተቆልፏል። እንግሊዝኛ ካልሆነ ከየት ያመጡታል።
መቼም ቤቱን የምገልጽበት ቋንቋ የለኝም። ባለ ሶሥት ፎቅ ቪላ ነው። ምድር ቤቱ ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት አንዱ የድንገት እንግዳ ቢመጣ ቁጭ ብሎ አስተናጋጅ መጥቶ ወደ ዋናው እንግዳ ማረፍያ እስኪወስደው የሚጠብቅበትና እኔ ደግሞ ልጆቹን የማስጠናበት ክፍል ነው። አንዱ ክፍል የመኖርያ ቤት ውስጥ ቡና ቤት ነው። (አምላኬ! የመኖርያ ቤት ውስጥ ቡና ቤት?)
ለእዚህ አላማ የተቋቋሙት መሸታ ቤቶች እንኳ እንዲህ የተደራጁ አይመስሉኝም። መደርደርያ ላይ እኔ በወቅቱ ስማቸውን ሰምቼ የማላውቀው የመጠጥ አይነቶች ተደድረዋል፣ ባለጌ ወንበሮች አሉ፣ ወንበሮች ከጠረጴዛዎች ጋር፣ የሙሉ ባንድ የሙዚቃ መሳርያዎች ከተደራጀ መድረክ ጋር፣ የሚያንጸባርቁ መብራቶች……..
(ሌሎቹ ፎቆች ላይ ግን ማን አሳልፎኝ አያቸዋለሁ? የልጆቹንም ክፍል ታመው ልጠይቅ ሰራተኛዋ ይዛኝ ሄዳ የተጮሀባትን ጩሀት አልረሳውም።”ማን አስገቢው አለሽ?” እኔም ከዚህ ቀን ወዲህ ድርሽ ብዬ አላውቅም።
ጊቢ ውስጥ አጥሩን የሚዞሩ የአበባ ጋርደኖች ከአርተፊሻል የውሀ ፏፏቴ ጋር ያለ ሲሆን ከቅርጫት ኳስ ሜዳው እልፍ ብሎ ባለ ሰፊ ዣንጥላዎች ተዘርግተዋል- እንደ ካፌ ነገር። ከሁሉ የሚገርመኝ ደግሞ አንድም ቀን ሸራ ከላያቸው ወርዶ አይቼ የማላውቃቸው ሶስት መኪኖች ናቸው።
“ምንድናቸው?” አልኩት ዘበኛውን አንድ ጊዜ ልጆቹ ለመዝናናት ሄደው “እስኪመጡ ጠብቅ!” ተብዬ ግቢ ውስጥ ለሰአታት ቁጭ ስል ተግባብቼው። “ሚስተር፤ እባክህ መንዳት ከቻልክ እንደው ትንሽ ወዲ ወድያ ብታደርጋቸው? ይሄው ጠዋትና ማታ እያጠብኩ መልሼ ሸፍናቸዋለሁ። አመት አለፋቸውኮ አለኝ። አዳዲስ መኪኖች ከውጭ እንደ ገቡ በቆሙበት ቆመዋል። “ወይ መኪና መንዳት እቴ!” ለራሴ አጉረመረምኩ። የት አባቴ የተማርኩትን?
(የሰዎቹን ሀብትና ንብረት እዚህ መዘርዘሩ ተገቢ አይሆንም ግን ከአስሩ ክፍለ ከተማ ውስጥ ስማቸው የማይጠራበት ህንጻ፣ ሆቴልና የንግድ ተቋም የለም።)
ድህነቴን እኔ አልፈጠርኩትም። ወይም አባቴ አላወረሰኝም። “ድህነት በስራ ሳሙና ቢታጠቡት የሚለቅ ቀላል በሽታ ነው!” የሚል ጥቅስ ግድግዳ ላይ ለጥፎ ያስጠናኝን አባቴን አምኜ ተማርኩ፣ ሰራሁ፣ ሰራሁ፣ ሰራሁ…… ግን ይሄው ሰው ቤት ውስጥም ለስራ መጥቼ ልዩነቴን የምማትር ተራ ዜጋ ብቻ ሳይሆን የሌለብኝ ቅናት የሚያንገበግበኝ ተራ አስተማሪ ሆኜ ተገኘሁ።
ሰው ለምን ሀብታም ሆነ አይባልም። ግን በተነጻጻሪነትም ቢሆን ለአንዱ ሲዘንብለት ለሌላው የማያካፋለትና ምንም ጠብታ እንዳይደርሰው ያደረገውን የኢኮኖሚ ስርአት ማጠየቅ ግን ግድ ነው? ማጠየቅ ብቻም አይደለም መኮነንም ይገባል።
“እኔስ ማን ነኝ?” ብሎ መጠየቅ ደግሞ የሰውነት ባህሪ ነው። ሀገር ታናሽና ታላቅ ዜጋ የላትም። የመሮጫ ሜዳችን ተመሳሳይ ቢሆን ኑሮ ከማድ ቤታቸው ውስጥ የሚቁላላውን ምግባቸውን እያሸተትኩ ሆዴ በረሀብ እየጮሀብኝ ከስራ ወደ ሌላ ስራ እየሄድኩ በድህነት የምማቅቅ ሰው ቢዚች ምድር እንዴት ልኖር ቻልኩ? እኔስ ምን አጎደልኩ? ነው ወይስ ጥያቄው “እኔስ ከማን ወገን ነኝ?” ይሆን?!