አቶ አለነ ማህፀንቱ ለነሐሴ 21 ;በ‹‹እነ አንጋው ተገኝ›› ላይ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለጳጉሜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
የአንድነት ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት አቶ አለነ ማህፀንቱ፤ ባሳለፍነው ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው እንደነበር የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ ይርዳው ገለፁ፡፡
አቃቤ ሕግ በአቶ አለነ ላይ ሁለት ምስክሮችን አሰምቶ የነበረ ሲሆን፤ በዚሁ ላይ ብይን ለመስጠት ማለትም ክሱን መከላከል ያስፈልጋቸዋል ወይም ክሱን ሳይከላከሉ በነጻ ሊሰናበቱ ይገባል፤ በሚለው ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ደምበኛቸው ውሳኔ ሳያገኙ ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም እንደተሰጣቸው የተከሳሹ ጠበቃ ገልፀዋል፡፡ ቀጠሮውን ወደ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ለመግፋት ታስቦ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ገበየሁ፤ ተቃውሟቸውን በማቅረባቸው የተነሳ ለነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሠጥ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ በችሎቱ እስካሁን ድረስ የደምበኛቸውን መዝገብ ሲመለከቱ የቆዩት እንስት ዳኛም፤ መዝገቡን ለተረኛ ችሎት ማስተላለፍቸውን ጠበቃው አያይዘው ገልፀዋል፡፡ መዝገቡን ወደ ሌላ ችሎት ማስተላለፍ ለምን አስፈለገ? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠበቃው ሲመልሱ፡- ‹‹መደበኛ ችሎቶች ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ በሥራ ላይ እንደማይገኙና ተረኛ ችሎቶች የመደበኛ ችሎቶችን መዝገብ ስለሚከታተሉ፤ መዝገቡ ለተረኛ ችሎት እንደሚተላለፍ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በተረኛ ችሎቶች ዳኞች በየአምስትና ስድስት ቀናት ልዩነት እንደሚቀያየሩ›› ገልፀዋል፡፡ ተረኛ ችሎቶች ብይን የመስጠት ሥልጣን አላቸው ? በሚል ለተነሳለቸው ጥያቄም ተከታዩን ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
‹‹ተረኛ ችሎቶች ብይን የመስጠት ስልጣን እንዳላቸው ሕጉ ቢያስቀምጥም፤ አብዛኛውን ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጡ እንጂ ውሳኔ ሲያስተላልፉ አይታዩም››
በአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 5ኛ መደበኛ ወንጀል ችሎት የአቶ አለነ ማህፀንቱን መዝገብ ሲመለከቱ የቆዩት እንስት ዳኛም፤ ብይን ሳይሰጡ ለተረኛ ችሎት መዝገቡን ያስተላለፉ መሆናቸውን ያወሱት አቶ ገበየሁ፣ በዚህም መሠረት በቀጣዩ ቀጠሮ ላይ መዝገቡን ሌላ ዳኛ እንደሚመለከተው አስረድተዋል፡፡ አቶ አለነ ማህፀንቱ ‹‹ስብሰባን በማወክ›› ወንጀል ተከሰው ከወርሃ ግንቦት 2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በሌላ ዜና የአንድነት ፓርቲ ክልል አመራሮች የነበሩት ‹‹እነ አንጋው ተገኝ›› በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርበው የነበሩ መሆኑን የገለፁት የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ፣ አቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አለኝ ያላቸውን 21 ምስክሮች ሳይዝ እንዳልቀረበና 1 ምስክር ብቻ ይዞ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡ የቀረበው ምስክርም በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) የሚገኝ እስረኛ መሆኑን ጠበቃው አያይዘው ገልፀዋል፡፡ አቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ይዞ ያልቀረበበትን ምክንያት ሲያስረዳም፡- ምስክሮቹ ሰሜን ጎንደርና አርማጭሆ ስለሚገኙ፤ እነሱን ይዞ ለማቅረብ ጊዜ እንዳጠረውና ለሕዳር ወር 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ለችሎቱ ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ገበየሁ አስረድተዋል፡፡ ደምበኞቻቸው ይህን እንደተቃወሙና አቃቤ ሕግ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ አለመሆኑን፤ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውንና ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለጳጉሜ 3፣4 እና 5 ቀን 2007 ዓ.ም መስጠቱን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የክልል አመራር የነበሩት እነ አንጋው ተገኝ ‹‹የግንቦት ሰባትን ተልዕኮ በመቀበል፤ ከአማራ ክልል ለግንቦት ሰባት አባል በመመልመል ወደ ኤርትራ በመላክና የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበር›› የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል፡፡
ፎቶ፡- አለነ ማህፀንቱ፣ አንጋው ተገኝ

