‹‹አቅጣጫችን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የተቃጣውን ብሄራዊ ጭቆና ለዘለቄታው መግታትን ያለመ ነው!›› ድምፃችን ይሰማ

የትግላችንን አቅጣጫ አስመልክቶ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!
ሰኞ ነሐሴ 11/2007

የመግለጫው ሙሉ ቃል በፒዲኤፍ፡-
http://goo.gl/s0Zna5

የመግለጫው ሙሉ ቃል በጽሁፍ እንደሚከተለው ሰፍሯል፡-

****

‹‹አቅጣጫችን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የተቃጣውን ብሄራዊ ጭቆና ለዘለቄታው መግታትን ያለመ ነው!››
‹‹የሙስሊሙን ሁለገብ መብቶች ለማስከበር እንታገላለን!››
እሁድ ነሐሴ 10/2007 አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

ኢስላም በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለዛሬው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ትውልድ የደረሰው በርካታ የጭቆና እና የትግል ሂደት አሳልፎ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችን አርአያ ቢሆንም ፍትሃዊ ያልሆኑ መንግስታት ሙስሊሙን ህብረተሰብ መፈናፈኛ በማሳጣት ማንነቱን አና እምነቱን አንዲተው ለማድረግ ከፍተኛ ጫና አድርገዋል። ሙስሊሙ እምነቱን በይፋ እንዲተው አዋጅ እስከመታወጅ የደረሰ ቢሆንም በቀደምት አባቶቻችን መስዋእትነትና ተጋድሎ እስልምና በከፍተኛ ዋጋ ለዚህ ትውልድ ደርሷል። ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንዲሉ ዛሬ ‹‹ዘመን ተሻሽሏል፤ ስልጣኔ መጥቋል፤ የሰው ልጆች በጋራ ህገ መንግስታዊ ጥላ ስር ያለመድሎ በእኩልነት መተዳደር ጀምረዋል›› በሚባልበት ጊዜ ላይ ብንሆንም ራሱን በበደል ዙፋን ላይ ያደላደለው የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራት ስለብሄራዊ ጭቆና ዳግም እንድናስብና በገዛ አገራችን እንደ ቀደምት አባቶቻችን ሁሉ ባይተዋርነት እንዲሰማን ለማድረግ አስቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በሕዝበ ሙስሊሙ ቆራጥ ሰላማዊ ትግል እና ‹‹በአገሬ ባይተዋር አልሆንም›› ባይነትና ወኔ ይህ የመንግስት እኩይ ሕልም ሳይሳካ ቢቀርም ተግባሩ ግልፅ ፀረ ሙስሊም አዋጅ ካወጁት የቀደምት መንግስታት ጋር አንድ አድርጎታል፡፡

ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የአገሪቱ ግማሽ አካል የሆነው ሙስሊም ህብረተሰብ መከተል ያለብንን የእምነት መስመር ይፋዊ በሆነ መልኩ ከመምረጥ አንስቶ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ተቋማት በመንጠቅ ለፖለቲካ ሹመኞች ሰጥቷል፡፡ ይህንንና መሰል የመንግስት ግልጽ ጣልቃ ገብነቶችን በሰላማዊ መንገድ የተቃወሙና ‹‹ድምጻችንን ስሙ!›› ያሉ አካላትን ‹‹አክራሪ›› እና ‹‹አሸባሪ›› የሚል ታርጋ በመለጠፍ በደል አድርሷል፡፡ በተጨማሪም ተቃዋሚዎችን በመግደል፣ በመደብደብ፣ በቶርችር በማሰቃየት፣ በማሰር፣ እስረኞችን ከሰብአዊ አያያዝ በወረደ ሁኔታ ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ልዩ ኣፓርታይዳዊ ስልቶችን በመጠቀም በማንገላታትና በማስቃየት፣ ንብረትን በመቀማት፣ ከሃገር እንዲሰደዱ በማድረግ፣ ሚዲያዎችን በመዝጋት፣ ድርጅቶችን በማፍረስ፣ ሙስሊም ሴቶችን በማዋረድ እና ሙስሊም ተማሪዎችን ከትምህርት ገብታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ በሙስሊሙ ላይ ዘርፈ ብዙ በደሎችን እያደረሰ ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃው ብሎ ለቅሬታዎች መፍትሄ ለማፈላለግ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ውክልና ይዘው የተንቀሳቀሱ፣ በሂደቱም በአገራችን ታሪክ በሰላማዊነቱ የሚወሳ አኩሪ ስራ የሰሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰባቸው የ3 ዓመታት ስቃይ አልበቃ ብሎ አገዛዙ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና የፍትሐዊነት ካባ የማልበስ አገልግሎት የሚሰጠው ፍርድ ቤቱ ያሳለፈባቸው እስከ 22 ዓመት የሚደርስ የእስር ውሳኔ ደግሞ መንግስት ሙስሊሙን ህብረተሰብ ከመናቅም ባለፈ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ‹‹ብሄራዊ ጭቆና ታውጆብናል›› ብሎ እንዲያምን አስገድዶታል። በመንግስት አጠቃላይ ፕሮግራም ውስጥ የሚካተተው ሙስሊሙን አግላይ የሆነ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ስርአትም ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያለውን ሙስሊም ለስራ አጥነትና ለስደት የዳረገ ነው፡፡ ባጠቃላይ ይህ የሚያስገነዝበው መንግስት በሙስሊሙ ላይ በረጅም አመታት የታቀደ የብሄራዊ ጭቆና ፕሮግራም እንዳለው ነው፡፡

ምንም አንኳን ላለፉት አራት አመታት ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንስተን ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› ብለን ፍጹም ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ብንጠይቅም በአንጻሩ መንግስት ሶስቱን ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ያለውን ንቀትና እኩይ ተግባር እያበራከተ አጠናክሮ በዘመቻ መልክ ቀጥሎበታል። እኛም የበደሉን ልክ በመረዳት ጥያቄዎቹን በሶስት ገድቦ ማስቀመጡ ምላሽ ከማምጣት ይልቅ መንግስት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ አጠናክሮ እያስቀጠለ ላለው ብሄራዊ ጭቆና እየዳረገን በመሆኑ ትግላችን ወደ ሁሉን አቀፍ የሙስሊሙን መብት በዘላቂነት ማስከበር ወደሚችልበት የትግል ምእራፍ መሸጋገር ይኖርበታል፡፡ በዚህም መሰረት ከአሁን በኋላ የሚኖረን የትግል አቅጣጫ የተቃጣብንን ብሄራዊ ጭቆና ለመግታት የሚያስችል፤ መንግስት የጀመረውን የጥፋት ተልእኮ ከማስቆም ጀምሮ የሙስሊሙን በአገሩ ላይ ያለው ሙሉ መብት በዘለቄታዊነት እንዲከበር የሚያስችልና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ይሆናል። ይህም ሲባል ከተነሳንባቸው መሰረታዊ የትግል መርሆች ሳናፈነግጥ፣ የአገሪቱ ህገ መንግስትና ኣለማቀፍ ህግጋት ያሰፈሯቸውን የመብት እኩልነቶች መሰረት ያደረገ፣ በሶስት ጥያቄዎች ብቻ የማይገደብ፣ እንደየሁኔታው ተለዋዋጭና የማይተነበይ የህዝባዊ እምቢተኝነት እና የትብብር መንፈግን ስልቶች ያካተተ አካሄድ እንከተላለን። በመሆኑም ጥያቄ አቅራቢነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን አቅም ግንባታን መሰረት ያደረገ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንደየአቅሙ የሚያሳትፍና የሁሉም ባለቤትነት የሚንጸባረቅበት የረጅም ጊዜ የትግል ሂደት ከፊታችን ይጠብቀናል።

ቀጣይ የትግል አቅጣጫችን መንግስት ለሚያደርሳቸው የተለያዩ ክስተቶች ምላሽ በመስጠት ላይ የሚወሰን ሳይሆን አርቆ አሳቢነትን መሰረት ያደረገ፣ በርካታ ስልቶችን የቃኘ፣ ብስለትና መልካም ፈለግን የተከተለ አካሄድ በመምረጥ እንጓዛለን፡፡ ትግላችን የአሸናፊነትን ስሜት የተላበሰው ከአራት ዓመታት በፊት አምባገናዊው ስርአት ያሰፈነውን የፍርሀት ድባብ ከላዩ ላይ ገፍፎ በጣለ ጊዜ ነው፡፡ ጀግኖቹ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ኣባላትና ወንድሞች ያሳዩት ቁርጠኝነትና ፅኑነትም ብርታት ይሰጠናል፡፡ በእነሱ ላይ የተጣለባቸውን እስራት ለእኛ የቁርጠኝነትና የረጅም ወኔ እንጂ የተስፋ መቁረጥ ምንጭ አይሆንም፡፡ በተጣለባቸው ‹‹ቅጣት›› ወኪሎቻች እና ወንድሞቻችን አልተደናገጡም፤ አልኮመሸሹምም! የኮመሸሹትና የተደናገጡት አንባቢዎቹ ዳኞች እንጂ ጀግኖቻችን አልነበሩም! ይህ ፍርድ ለበደል አድራሹ የውድቀትና የሽንፈት ምልክት እንጂ ሌላ አይደለም፤ አስታራቂና መፍትሄ አፈላላጊ ኣካላት ላይ 22 ዓመታት እስር መፍረድ ከፍርሃትና ሽንፈት ዉጪ ምንስ ሊባል ይችላል!?

በደልና ሐሰት ከታጋዮችና እውነተኞት ፊት ሁሌም ሁሌም ተሸናፊዎች ናቸውና የተቃጣብንን ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆና በአሸናፊነት እንደምንወጣው በአላህ ፈቃድ እርግጠኞች ነን፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!

ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናን አንሸከምም!
በጋራ ተሳትፎ እና በአንድነት ዲናችንን እንጠብቃለን!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችንም ይሰማል!
አላሁ አክበር!

**********************************************
**********************************************