ከዳያስፖራ በዓል ባሻገር ያለ መራር እውነት
ሰሞኑን ስለ ዳያስፖራው እየተለፈፈ ነው አንድ ሁለት እንበል
ከእልልታው ባሻገር ያለ ኡኡታ #Ethiopia #DiasporaDay ? Jomanex Kassaye
የሰሞኑ መንግሰት ከዳያስፖራው ጋር የያዘው ዳንኪራ እና በአፋር እና ሌሎች አካባቢዎች ከተከሰተው ድርቅ አንጻር “ታሪክ ራሱን ደገመ” ብለን በርዕስነት ወደያዝነው ጉዳይ እናምራ
ዳያስፖራነት እና ተቃውሞ
1. ወጣቱ ኢንጂነር በሙያው ይሰራ የነበረ እና በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የቅንጅት አባል በመሆን አንዳንድ አስተዋጽኦዎችን አበርክቷል፤ መጨረሻው አላማረምና እሱም ጥጉን ያዘ በስደት በደቡብ አፍሪካ ኑሮውን ተያያዘው፤
ሕይወት ቀጠለ በአገረ እንግሊዝ ከምትኖር ጉብል ጋር እጅጉን ተዋደዱ፣ ተፋቀዱ፣ ለመጋባትም ወሰኑ ይህንንም በአገራቸው መሬት ሊያደርጉት ተስማምተው አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ሰርጉ ተደገሰ፣ ከሰርጉ ሲወጣ ደህንነቶች ከፖሊስ ጋር ተቀበሉት ልንቀበለው በማይገባ ነገር ግን በፈቀድነው ከሕግ ውጪ አካሄድ ማዕከላዊ ያለጠያቂ ለወራት ከቶርቸር እና ራሱ ወንጀለኛ የሚያደርግ ፋይል በገራፊዎቹ ትዕዛዝ ሲያሰናዳ ከቆየ በኋላ ፍርድ ቤት ያለ ሃይ ባይ ዓመታት አከናነቡት…. ለወራት የታገሰች ሙሽሪት ሕመሙን መቋቋም አቅቷት ዳግም ስደትን መረጠች
ይህ የሆነው ከዓመታት በፊት ነው…ወጣቱ ዛሬም በእስር ላይ ነው
2. ከሰሞኑ
የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነው ጓደኞቹን ለማግኛነት እንጂ ከዛ ላለፈ አገልግሎት ተጠቅሞበት አያውቅም የየትኛውም ፓርቲ ደጋፊ ባይሆንም ‹‹ጽንፈኛ›› ከሚባሉት ዳያስፖራዎች ባይመደብም አክራሪ ሊባሉ የማይገባቸው ነገር ግን ምክንያታዊ ተቃዋሚ ጓደኞች አሉት፣ ወዳጆቹ ናቸው ያለሃሳብ በነጻ አገር እነሱን ያገኛል፣ የተመቸውንም በፌስ ቡኩ ያጋራል፤
ስደተኞች ነገር ግን መተዳደሪያቸውን ጆሮ መጥባት፣ ሌላውን መማገድ ያደረጉ ልወደድ ባይ የኅወኃት አባላት እና ሌሎች እነ እንትናን ያውቃል በሚል ስሙን አሳልፈው ሰጡ
በዱላ የሚያስበው እና ሕወኃትን ለዘልዓለም ስልጣን ላይ ለማቆየት ሌት ተቀን የሚሰራው የጸረ-ሽብር ግብረ ሃይል ከውጭ የመጣ መረጃን በተለየ ሁኔታ ይመለከታልና ልጁ ምንም በማያውቀው በቦሌ እረፍቱን ምክንያት አድርጎ ለዘመድ አዝማዶቹ ያቅሙን ሸክፎ ሲደርስ መድረሻው ማዕከላዊ ሆኗል፤ በሰዓቱ ብዙ ዜጎች ወደ አገራቸው የገቡ ቢሆንም በዕለቱ ወደ ሰባት የሚጠጉ ዜጎች ሊቀበሏቸው የሚጠብቋቸውን ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ ይህን በምጽፍበት ሰዓት ጭምር ቶርችን በማዕከላዊ እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
‘ሕገ-አራዊት’ ነውና የሚገዛን የኤርፖርት ፖሊሶችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በእንባ እና በሰቀቀን ላሉት ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሊነግሯቸው ፈቃደኞች አይደሉም (ገርፈው የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ከሌለም እስኪጋገርባቸው ይቆያሉ)
ይህ ከዳያስፖራ በዓል ባሻገር ያለ መራር እውነት ነው፡፡