የእነ አቡበከር ጉዳይ የሙስሊሞች ሳይሆን የፍትህ ነው
ጉዳዩ የዚህ ሀይማኖት ወይም የዚያ ሐይማኖት ተከታይ በመሆንና ባለመሆን የሚቀርብና የሚርቅ አይደለም፡፡ በየትኛውም ቦታ፣በማንኛውም ቡድንና ግለሰብ ላይ የሚፈጸም ኢ ፍትሀዊነት ካለንበት ክበብ ወጣ ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል፡፡
መንግስት በጠረጴዛ ዙሪያ ሲደራደራቸው የነበሩትን ሰዎች ድንገት ጠራርጎ‹‹ሽብርተኞች ናቸው ››ማለቱም ከመነሻው በመታሰራቸው ዙሪያ ‹‹ትልቅ ጥያቄ ››እንድናጭር ያደርገናል፡፡
ሰብአዊ ክብራቸውን በሚነካ መልኩ በማዕከላዊ ቃላቸውን እንዲሰጡ መደረጋቸውና እንደ እነርሱዉ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ጭምር ‹‹ሽብርተኞችና እስላማዊ መንግስት ለመገንባት ያሴሩ›› ተብለው የነበሩ ከዓመት እንግልት በኋላ በፍርድ ቤት ነጻ መለቀቃቸውም ደግመን ደጋግመን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ባልሆኑበት ሁኔታ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ለማስተባበል የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች ስውሩን የፖለቲካ እጅ በማይበልጡበት መንገድ ዜጎች ‹‹ጥፋተኞች›› እየተባሉ ወህኒ ቤት መወርወራቸውን ከራሳችን ሐይማኖት፣ቡድንና ጎሳ አንጻር ከመዘነው ‹‹ፍትሐዊነት››መቀመቅ ትወርዳለች፡፡
በእነ አቡበከር መዝገብ ተከሰው የፊታችን ሰኞ ለውሳኔ የተቀጠሩት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና እነርሱን ይደግፋሉ ተብለው የተያዙት ለእስር ከመዳረጋቸው አስቀድሞ ጥያቄዎቻቸውን ለህዝብ ያቀረቡ በመሆኑ ስውር ላልነበረው እንቅስቃሴያቸው የተሰወረ ወንጀል ፈጥሮ ጥያቄያቸውን ለማፈን መሞከሩን አጥብቀን በመቃወም በሰኞው ችሎት ‹‹መዝገባቸው ተዘግቶ መልካም ስማቸው እንዲመለስላቸው ለመጠየቅ ፍርድ ቤቱ ይህንን ገፍቶም በዚያው መንገድ ለመወሰን ከቆረጠም ህመሙ ለሁላችንም መሆኑን ለማሳየት ይህ አጋጣሚ መልካም ይመስለናል፡፡እናም ፍትህ ይሰፍን ዘንድ በህብረት እንቁም፡፡ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በዚህ ጉዳይ ብቻቸውን እንደማይቆሙም ለመንገር የተዘጋጀውን ዕድል እንጠቀምበት፡፡
(ዳዊት ሰለሞን)