ፕረዘዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪካ መሪዎች ሕገመንግሥቶቻቸውን እንዲያከብሩና በየሀገሮቻቸው ዴሞክራሲን በትክክል ለመገንባት ተጨባጭ ጥረት እንዲያደርጉ አሳሰቡ፡፡
ዜና መድረክ – –
ፕረዘዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪካ መሪዎች ሕገመንግሥቶቻቸውን እንዲያከብሩና በየሀገሮቻቸው ዴሞክራሲን በትክክል ለመገንባት ተጨባጭ ጥረት እንዲያደርጉ አሳሰቡ፡፡
የወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አማሪካ ፕረዘዳነት ባራክ ሁሴን ኦባማ ይህንን ማሳሰቢያ ለአፍሪካ መሪዎች የሰጡት ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ ም (እኤአ. July 28, 2015) በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽ/ቤት በነልሰን ማንዴላ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ ፕረዘዳንቱ በአዳራሹ ለተሰበሰቡት ከ2500-3000 ለሚገመቱ ተሰብሳቢዎች ባሰሙት በዚሁ ንግግራቸው ከፊታችሁ የቆምኩት እንደ አንድ ኩሩ አሜሪካዊና እንደ አንድ የአፍሪካ ልጅ ሆኜ ነው& ካሉ በኋላ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰው ልጆች ሁሉ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም፣ በፆታ ወዘተ ሳይለያዩ እኩል የሚያሲፈልጋቸውና ተግባራዊም ሊሆንላቸው የሚገባ ሥርዓት ስለሆነ አፍሪካዊያንም በትክክል ሥራ ላይ በማዋለ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤቶች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች በቅርቡ ተስፋ ሰጪ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያካሄዱ ቢሆንም አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች ራሳቸውን ከሕገመንግሥት በላይ በመቁጠር ከሕግ ውጭ በስልጣን ላይ ለመቆየትና በሀገሮቻቸው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር እንቅፋት በመሆን ሕግንና የሕዝቡን መብት በመጣስ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ እነዚህ መሪዎች ከዚህ ዓይነቱ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ተግባራት ሊታቀቡ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ፕረዘዳንት ኦባማ ንግግራቸውን በመቀጠል ዴሞክራሲ በየወቅቱ ምርጫዎችን በማካሄድ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ነፃ ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ ድምፁንም ባማክበርና የሥልጣን ባለቤትነቱን በትክክል ተግባራዊ በማድረግ እውን ሊሆን እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአንድ ጊዜ የማይጠናቀቅና በሂደት እየተሟላ የሚሄድ ቢሆንም የሥርዓቱን ግንባታ በትክክል እውን ለማድረግ በቀና መንፈስ የሚካሄዱ ተጨባጭና ጠንካራ የሆኑ ጥረቶችም ሊደረጉ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ አስመልክተው ሲናገሩም እኤአ በ2015 (በ2007 ዓ ም) በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ ያለብጥብጥ መጠናቀቁ ቢያስደስታቸውም በሀገሪቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና በጋዜጠኞች ላይ እተፈጸሙ ያሉት እስራቶችና ወከባዎች፣ እንዲሁም ነፃ የሲቭክ ማሕበራት እንዳይኖሩ የሚፈጸሙት ጫናዎችና አፈናዎች እንደሚያሳስቡዋቸው፣ የእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማግኘትም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ስለሆኑ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃይለማሪም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት መናገራቸውንና ጠቅላይ ሚ/ሩም ለወደፊቱ ተገቢው ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡

በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፎች አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ዕድገት እያሳየች መሆኑዋን የገለጹት ፕረዘዳንት ኦባማ በአህጉሪቷ እየተንሰራፋ የሚገኘው ሙስና ግን ለዕድገቱዋ ካንሰር (ነቀርሳ) ስለሆነ መወገድ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ ከአሜሪካና ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነትም በዋናነት በዕርዳታ ላይ ሳይሆን በእኩልነትና በጋራ መጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ንግድና የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ያተኮረ መሆን ይገባል ብለው ስለሚያሚኑ ግንኙነቱ በዚህ መልኩ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በበኩላቸው በዚሁ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን ተባብረው ለመፍታትና ለዓለም ሰላም መከበርም ጠንካራ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው አህጉሪቷ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ብለዋል፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የፕረዘዳንት ኦባማን የአፍሪካ ሕብረት ጉብኝት ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ጥሪ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ባለሥልጣናትና ሰራተኞች፣ የአፍሪካና የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮችና ሌሎች ዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ አባላት፣ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቭክ ማሕበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከመድረክ በኩልም አቶ ጥላሁን እንዳሻው የመድረክ ም/ሊቀመንበርና ሕ/ግ/ኃላፊ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና የመድረክ ም/ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ገብሩ አሥራት የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና አቶ በቀለ ገርባ የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር በዚሁ ስብሰባ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት ጽ/ቤት ከተካሄደው ከዚሁ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ፕረዘዳንት ኦባማ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከጠ/ሚ/ር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ሆነው በሰጡትጋዜጣዊ መግለጫም በሀገራቸውና በኤርትራ ስለሚንቀሳቀሱና መንግሥት በአሸባርነት የፈረጃቸውን ፖለቲካ ድርጅቶች በሚመለከት ከአንድ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የኢትዮጵያንም ሆነ ሌላ በሕግ የተቋቋመን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን አካሄድ እንደሚቃወሙ ገልጠው የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚለው ግን እነዚህ ድርጅቶች የሽብርተኝነት ተግባራትን በተጨባጭ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ በሀገራቸው የደህንነት መሥሪያ ቤት በኩል እስከአሁን ስላላገኙ በሽብርተኝነት ለመፈረጅና በሀገራቸው እንደይንቀሳቀሱ ለመከልከል በሚያስችል ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡