አሜሪካ፣ የኢህአዴግ “አድናቂ” ትሆናለች ብሎ ማን አሰበ!
Addis Admass.com ኢህአዴግ፤ “ኒዮሊበራል” በማለት አሜሪካን መዝለፍ ያዘወትራል። ታዲያ እንዴት፣ ኦባማ “ድንገት”
ተነስተው ዋና የኢህአዴግ አድናቂ ይሆናሉ? (ድንገተኛ አይደለም፡፡ አባማ ነባር ሃሳባቸውን ላለፉት
6 ዓመታት በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡)
· የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፤ ለኦባማ የምርጫ ዘመቻ ቀስቅሰዋል። ዛሬ ግን፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ
ክህደት ሆኖባቸው የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂዳሉ። (ክህደት አይደለም፡፡ ኦባማ, የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን
አልቀየሩም)።
· “ኦባማ ቢያሸንፉ፤ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም” (ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ
የወጣ ትንታኔ። የኦባማ የሃሳብ ቅኝት ለኢህአዴግ እንደሚመች የሚተነትን ጽሑፍ ነው፡፡)
የዘንድሮ ፖለቲካ፣ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጭ፣… በግራ በኩል ሲጠብቁት በቀኝ በኩል የሚነጉደው ለምንድነው? “ግራ መጋባት” ይሉሃል ይሄ ነው። እንዲህ የምንሆነው፣ ሳናስተውል ስለቀረን ወይም ሚዛን ስለጠፋብን ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ ጥፋቱ የኛ ነው።
ግን፣ ሌላውስ ዓለም መች ከግራ መጋባት ዳነ! “ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የዘመኑ ፖለቲካ መላ የለውም’ኮ” ሊባል ይችላል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ከሚጠብቁት ውጭ፣ ዓለማችን ከዳር ዳር እየተናጠች ነው። ግራ መጋባት የተበራከተው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ኢትዮጵያ ላይ በዛ፣ ተደጋገመ፣ ተደራረበ።
በተለይ በተለይ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋምና ጉብኝት በፍፁም ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፡፡ ከስድስት ዓመት በላይ ካላንቀላፋን በስተቀር፣ የኦባማ አስተሳሰብና አዝማሚያ ገና ድሮ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባ ነበር። ለምን?
አንደኛ ነገር፣ የትርምስ ዘመን ላይ ነን፡፡
“በአረቦች አብዮት” ሳቢያ፣ በርካታ አገራት ከድጡ ወደ ማጡ ተሸጋግረው ማብቂያ ወዳልተገኘለት ትርምስ መግባታቸው፣ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓም አሳሳቢ ሆኗል። “የፖለቲካ ለውጥ መጣ” ማለት፣ “መልካም ለውጥ መጣ” ማለት ላይሆን እንደሚችል አይተዋላ።
አሳዛኙ ነገር፣ የዘመኑን ትርምስ በማየት የተሳሳተ ድምዳሜ መያዛቸው ነው፡፡ እናም፤ “በአለም ዙሪያ የግለሰብ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ምርጫዎችንና የነፃ ገበያ አሰራርን የሚያስፋፋ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ተፅእኖ ማድረግ ዋጋ የለውም። እንዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብለዋል – አውሮፓና አሜሪካ። “በአፍሪካና በአረብ አገራት… በተለይም ደግሞ፣ እንደ አፍሪካ ቀንድ በመሳሰሉ የውጥረት አገራት ውስጥ፣ የተረጋጋ መንግስትና የኢኮኖሚ እድገት ከተገኘ በቂ ነው” ወደሚል ተስፋ ቢስነት እየወረዱ ነው።
አውሮፓና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የፖለቲካ ምርጫ ሲሰጡት የነበረ ትኩረት ምን ያህል እንደቀነሰ በዘንድሮው ምርጫ በግልፅ ታይቶ የለ!!
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በተረጋጋ ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገት እስካስመዘገበ ድረስ፣ ለአካባቢው አገራት መረጋጋት እስካገዘ ድረስ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የወዳጅነት እርዳታ ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነው – በዛሬ አለማቀፍ የትርምስና የሽብር ዘመን።
ይህንን ማስተዋልና ማገናዘብ ከቻልን፣ የኦባማ ጉብኝት በጭራሽ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ አይሆንብንም፡፡
ሁለተኛ ነገር፡-
ባራክ ኦባማ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያሳዩት የወዳጅነት አቋም ግን፣ ከዚህም ያለፈ፣ ከዚህም የቀደመ ነው። ገና ሳይመረጡ በፊት የያዙት አቋም ነው።
“የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው።
(አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አሜሪካን በጥሩ አይን የሚያይ ቢሆንም፤ ለአሜሪካ በጎ አመለካከት የሌላቸውና አሜሪካን ማብጠልጠል እንደ አዋቂነት የሚቆጥሩ ብዙዎቹ የአገራችን ፖለቲከኞች፣ የኢህአዴግና የተቃዋሚዎችም ጭምር፣ እንዲሁም ምሁራንና ጋዜጠኞች… በአብዛኛው በዚህ የኦባማ አስተሳሰብ እንደሚስማሙ እገምታለሁ)።
“ከሁሉም ከሁሉም በፊት፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ይቀድማል”… ማለትም በቁንፅሉ… ምግብ፣ መጠለያ፣ የስራ እድል የማሟላት ጥያቄ ይቀድማል ባይ ናቸው ኦባማ። እዚህ ላይ የአሜሪካ ድርሻ፣ “የግለሰብ መብት፣ የፖለቲካ ምርጫና ነፃ ገበያ” የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ትታ፣ እርዳታ መስጠት ብቻ ይሆናል። ኦባማ ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በተግባርም እየሰሩበት ይሄውና ስድስት አመታት ተቆጥረዋል።
ታዲያ፣ ይህንን ሁሉ ሰምተንና አይተን፣ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚከተሉ መገመት ያቅተናል? ቢያንስ ቢያንስ፣ ፖለቲካን እንጀራቸው ወይም ፖለቲካን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች፣ ይህንን መሳት አልነበረባቸውም።
ግን ስተውታል፤ በረዥም ርቀት ስተውታል። በቃ፣ የባራክ ኦባማ አቋምና የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ ለአገራችን ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ ሆኖባቸዋል።
በአንድ በኩል፣ ኢህአዴግ፣ በተለመደው የሶሻሊስቶች ፈሊጥ “ኒዮሊበራል” እያለ ከሚያጣጥላት አገር… ካልጠበቀው አቅጣጫ… ከአሜሪካ፣ ለዚያውም ዝነኛው ባራክ ኦባማን የመሰለ አድናቂ ማግኘቱ ያስገርመዋል።
ተቃዋሚዎችስ?
ያኔ በ2001 ዓ.ም፣ “ባራክ ኦባማ ከተመረጡ፣ በኢህአዴግ ላይ ጫና በማሳረፍ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ይረዱናል” በማለት፣ ኮሚቴ አቋቋመው ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችስ? በነሱ ቅስቀሳ ባይሆንም፣ ኦባማ ተመርጠው በፕሬዚዳንትነት ሲሰሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄን ሁሉ አመት የኦባማን አስተሳሰብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይገነዘቡ የቆዩ የአገራችን የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በኦባማ አቋም ተበሳጭተው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት አሁን ነው – የኦባማ ጉብኝት፣ ድንገተኛ ክህደት ሆኖባቸው።
ላለፉት ስድስት አመታት፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፣ የባራክ ኦባማን የውጭ ፖሊሲ ለማወቅ ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት ባልተፈጠረ ነበር። ለኢህአዴግ፣ ድንገተኛ አድናቆት አይሆንበትም ነበር። ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ ክህደት ሆኖ ባልታያቸው!
ኢህአዴግና የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ለአመታት ያህል እንዲህ ግራ የተጋቡት ለምንድነው?
በእርግጥ፣ ነገሩ ከተፈፀመ በኋላ፤ የጉብኝት ዜናው ከዳርዳር ከተወራ በኋላ… “ነገሩን መሳት አልነበረባችሁም፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ ማወቅ ነበረባችሁ፤ መገመት ነበረባችሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። ነገር ግን፣ ዛሬ ሳይሆን ከስድስት ዓመት በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ሁለት ፅሁፎችን ማስታወስ ይቻላል።
አንደኛው ፅሁፍ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2000 ዓ.ም፡፡
“ባራክ ኦባማ ለኛ ምናችን ናቸው?” በሚል ርዕስ የወጣ ፅሁፍ ነው። ባራክ ኦባማ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ላይ የፖለቲካ ጫና ለማሳደር እንደማይፈልጉ ከነምክንያቱ ይተነትናል ፅሁፉ። እንዴት? ከርዕሱ ስር፣ የፅሁፉን ይዘት የሚገልፁ ዋና ዋና ነጥቦች በጉልህ ተዘርዝረዋል።
ባራክ ኦባማ፣ “ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት በአለም እንዲስፋፋ አደርጋለሁ አላሉም” ይላል አንዱ ነጥብ።
ሌሎቹንም ነጥቦች ልጥቀስላችሁ፡-
ባራክ ኦማባ … “ለድሃ አገራት የኢኮኖሚ እርዳታ በእጥፍ እጨምራለሁ ብለዋል፤ የምርጫ ውድድርን በመተግበር አገራትን አሻሽላለሁ አላሉም፡፡”
ባራክ ኦባማ … “ትምህርትና ጤና በማስፋፋት በአለም ለውጥ ይመጣል ብለዋል፤ በድሃ አገራት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መጠናከር ይገባዋል አላሉም፡፡”
እነዚህን የባራክ ኦባማ መርሆች በማገናዘብ ነው፤ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚኖራቸው በፅሁፉ የተተነተነው።
ሁለተኛው ጽሑፍ ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም።
በአዲስ አድማስ የወጣው ይሄኛው ፅሁፍም ተመሳሳይ ትንታኔ ያቀርባል። ርዕሱ እንዲህ ይላል፡
“ኦባማ ቢያሸንፉ፤ ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም”
ኦባማ ቢመረጡ፣ “የአፍሪካ መንግስታት፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ጭምር ከአሜሪካ የፖለቲካ ተፅእኖ ይገላገላሉ፡፡ በዚያ ላይ ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ያስገኝላቸዋል” የሚል ይዘት አለው ፅሁፉ።
(“ኦባማ ቢያሸንፉ፤ ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም” የሚለው ፅሁፍ፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ የሚገልፅ በመሆኑ ትክክለኛ ትንታኔ ነው። ነገር ግን፣ ስህተትም አለው። ኢህአዴግ ነገሩን አገናዝቦ፣ በኦባማ መመረጥ ይደሰታል ብሎ መተንበዩ ስህተት ነው። ኢህአዴግ ነገሩን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልተገነዘበውማ። ተቃዋሚዎችም እንዲሁ።)
ለማንኛውም፣ እነዚህን ፅሁፎች ለመጥቀስ የፈለግሁት ለምንድነው? የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተጨባጭ መረጃን በማገናዘብ፣ ያኔ ድሮ የኦባማ አስተሳሰብንና አዝማሚያን ማወቅ ይችሉ እንደነበር ለማሳየት ነው የፈለግኩት። ለማወቅ ያልቻሉት፣ ነገሩ ከባድ ስለሆነ አይደለም። በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ነው እንዲህ ለስህተት የሚዳርጋቸው።
written by ዮሃንስ ሰ
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=16520%3A%E1%8A%A0%E1%88%9C%E1%88%AA%E1%8A%AB%E1%8D%A3-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%88%85%E1%8A%A0%E1%8B%B4%E1%8C%8D-%E2%80%9C%E1%8A%A0%E1%8B%B5%E1%8A%93%E1%89%82%E2%80%9D-%E1%89%B5%E1%88%86%E1%8A%93%E1%88%88%E1%89%BD-%E1%89%A5%E1%88%8E-%E1%88%9B%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%88%B0%E1%89%A0