ደወል ቁጥር 2

ሰዋስው ስለሺ ዮሐነሰን

May 20, 2010

በኢትዮጵያ ምድር ያሉ የደላቸውና እና የጠገቡ ሰዎችን፣ ወይም የነሱ በረከት ተካፋይ የሆኑ ሰዎች ረሐብን እና ችግርን ከረሱት ብዙ ጊዜ ስለ ሆናቸው ብቻ፣ ሌላው ሁሉ እንደ እነርሱ የደላው ስለሚመስላቸው፣ የሚሉት ገብቶንም ይሁን ሳይገባን በማስተጋባት፣ ከአገር እየወጡ በስደት ምድር የሚያልቁትን ወገኖቻችንን፣ ስለ ደረሰባቸው መከራ እና በቤተሰብም ላይ ጥሎ ከሚያልፈው ሐዘን ከማዘን ይልቅ፣ ከአገራቸው ጥጋብ እንዳስለቀቃቸው፣ ለሚያወሩ እና በወገኔ የፈሰሰ ደም ለሚያላገጡ ሁሉ፣ ሰማይ የፈሰሰውን ደማቸውን እስክትበቀልላቸው ድረስ፣ እጃችንን ወደ ሰማይ ከማነሳት፣ እንባችንን ወደ ሰማይ ከመርጨት፣ ፀሎታችን የጸባዖትን በር ከማንኩዋኩዋት አታቁዋርጥም፡፡

ትውልድ አገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ አመታት፣ በርካታ ትውልድን ስትገብር ለመኖሩዋ በአይኔ ያየሁ፣ በጆሮዬም የሰማሁ ሕያው ምስክር ነኝ፡፡ በተለይ አገር ሊገነባ የተገባው እና የወደፊትም ተሰፋ የሚጣልበትን ወጣት ትውልድ አብዝታ ገብራለች፣ ቁጠሩ ምን ያህል እንደሆን ባላውቅም፣ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች እንዳለቁ፣ ገዳዮቻቸውም፣ ደርግ ብቻ ሳይሆን፣ የደርግ ተቃዋሚ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሁሉ እጃቸው እንዳለበት፣ ዛሬ ጊዜ ቢከድንውም እንኩዋን ፣ ሰማይ ግን መዝግባዋለችና የእዛ ዘመን ትውልድ ደምም እስከዛሬ ከመቃብር በላይ ይጮሀል፡፡

እግዚአብሔር ፈቅዶ እኔም ከዛ ትውልድ ሰለባነት አምልጬ በሕይውት ኖሬ፣ እኔም በተራዬ ወላጅ ለመሆን በቃሁ እና የሕዝቤን ወላጆች፣ መራራ ስቃይ፣ እናት አባታቸውን የተነጠቁ ልጆች መከራን፣ ባልዋን የተነጠቀች ሚሰት ጭንቀትን፣ ሚስቱን ያጣ ልጆቹን ብቻውን ማሳደግ ግራ የገባውን ባል፣ ጡዋሪ ያጡ አዛውንቶች የሰው እጅ ጠበቆ እና ለምኖ መኖር፣ ትምህርት የሚያስተምሩዋቸውን ታላላቆቻቸውን ያጡ ወንድሞች እና እህቶች መከራን፣ ባዕድ ምድር ላይ ዛሬ ላይ ቆሜ በአይነ ሕሊናዬ እያየሁ፣ ስቃያቸውን እንድጋራው የትውልዱ ሰቆቃ ግድ ይለኛል፡፡

ከሁሉ የሚከብደው ደግሞ እንደ እድል ሆኖ ሰርተንም ይሁን ዘርፈን ባገኘንው ሀብት ተመክተን የሌላውን ቸግር የምንጸየፍ እና ችግረኞችን ወይም የችግረኞችን ጩሀት የሚያሰሙትን ሰዎች የምንንቅ፣ ይህንንም ሐቅ ላለመስማት ወይም ለመካድ የምናደርገው ክህደት እና “በሐገሪቱ ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚከፈል ዋጋ ነውና መቀበል አለብን “ ተብሎ፣ ምድሪቱዋ ለአገሩ ምርጥ ልጆች እና ምርጥ ላልሆኑ ልጆቹዋ ተለይታ፣እንዱ በአገሩ እንደፈለገው የሚገባባት የሚወጣባት፣ ሌላው እንደፈለገ እንዳይገባና ወገኖቹን እንዳያገኝ ገደብ የተበጀባት፣ ዘመዱን ለመዳር፣ አለያም ለመቅበር ሳይታደል፣ የተገለለባት አገር መሆኑዋን ስናውቅ በጣም ያሳዝናል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መሐል ቀደም ሲልም በነበረው ጦረነት እና ፣ በሁዋላም በተነሳው ጦረነት የተገበረው ትውልድ፣ ልጆቻቸውን ማሳደግ፣ ወላጆቻቸውን ለመጦር ያልታደሉ የሁለቱም ምድር እናቶችና አባቶች፣ ዛሬም ዕለት ዕለት በአገር ውስጥም በውጭም እያለቀ ያለው ሕዝብ ደም ከመቃብር በላይ ይጮሀል፣ ዛሬም ሁለቱ አገሮች ከተለያዩ በሁዋላ እንኩዋን፣ ለተጋደሉበት ምድር ላይ በሰላም ለመኖር ሳይታደሉ፣ በረሐውም፣ ባሕሩም፣ ወንበዴውም እየጨረሰ ያለው፣ የኤርትራ እና የኢትጵያውያንን ወጣት ትውልድን መሆኑን፣ ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኖ፣ ዛሬም አያገባኝንም መርጠናል፣ ለሞቱት ሻማ ለማብራት የምንቸኩለውን ያህል፣ ልንሞት ነውና ድረሱልን፣ አስጠሉን ለሚለው ድምጽ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን፣ ለምን እንደመረጥን እግዜር ይወቅው?

እኔ ራሴ መረጃው በሌለኝ ወቅት ምድራችን ላይ የተገነባውን ሕንጻ ከማድነቅ ባሻገር፣ ከሕንጸው እና ከመንገዱ ጀርባ ትውልዱ እየከፈለ ያለውን ዋጋ ለመረዳት መረጃ ስላልነበረኝ፣ አገር ውስጥ ችግር አለ እያሉ የሚጮሁ አልፎ አልፎ የምሰማው ድምጽ ሳይገባኝ የቆየሁበት ጊዜ ቀላል አልነበርም፡፡ ከገባኝ በኁዋላ ግን ዝም ማለት አቅም አጣሁ፣ በግሌ የበረታ ነገር ባላድርግ እንኩዋ፣ እንደ ትውልድ እናት ከወገን ጋር በመቆም በጋራ ላበረክተው የምችለው ነገር እንደማይጠፋ ግን ገመትኩ፣ ምንም እንኩዋን ሁኔታዎች ቢያስቆጡኝም፣ እንደ ወጣትነት ዘመኔ፣ እንደ ሰው ልማድ መታገል ባልችልም እንደ አድሜ ባለጠጋ አዛውንት ግን የምችለው፣ እግዜርም ያሰማራኝ ትውልዳችንን ለማስታረቅ ጥርጊያ መንገድ ማስጀመርን፣ ስለሆነ፣ ከዚህ ቀደም ያልሄድኩበትም መንገድ ቢሆን እንኩዋን ከነድካሜ ልደፍረው አቅሜን ሰበሰብኩ አምላኬም ይረዳኛል ብዬ አምናለሁ፡፡

ብዙዎቻችን ዝምታን የመረጥንው ስላልገባን ይሁን? መረጃ ስለሌለን? መረጃ መስማት ስለማንፈልግ ይሁን? የመረጃ ምንጮቻችንን ስለማናምናቸው ይሁን? ምን ማድረግ እንችላለን? በሚል አቅመቢስነት እየተሰማን ይሁን? በዚህ ጉዳይ ላይ ብንሳተፍ ከተቃዋሚ ጎራ እንመደባለን ከሚል ፍራቻ ይሁን? ወይም እኛ እራሳችን የተነካካንበት ጉዳይ ኖሮብን፣ ይህንን ብል እነደዚህ ብለው የኔን ጥፋት ቢያነሱብኝስ ከሚል ፍራቻ ይሁን? ወይም ሌላ ምክንያት እንዳለን ባላውቅም፣ አፋችንንም፣ እግራችንንም፣ እጆችንንም፣ ጆሮአችንንም፣ መሰብሰቡን ለመምረጥ የተገደድን ጥቂት የምንባል አየደለንም፡፡እግዚአበሔር ግን ምርኮን ለማስመለስ አቅም ካጣንበት ሁኔታ ውስጥ ሁላችንን ከዚህ ችላ ባይነት ይፈውሰን?

2

ደጋግመው የህዝቡን መከራ ወደ አደባባይ ሊያወጡት የሚሞክሩትም መፍትሔ እንፈልግ የሚሉትም ጥቂቶች ናቸውና፣ ለእነርሱም ቢሆን የተለያየ ስም ስለተሰጣቸው፣ እነርሱን መቅረብም፣ ችግራችሁ ምንድነው? የሚያስጮሀችሁስ ምንድን ነው? ብለን ከመጠየቅ ይልቅ፣ ወይ በእነርሱ ላይ እንፈርዳለን፣ ከእነርሱ ጋር ላለመታየት ላለመነካካት በፍርህት ውስጥ መቀመጥን እንመርጣለን፣ ከእያንዳንዱ ከሚጮሀው ግለሰብ ጀርባ ግን፣ ያለፈበት ስንት ለጆሮ የሚዘግንን ታሪክ ልንሰማ እንደምንችል ምን ያህል አቅም እንደሚያስፈልገን ቤት ይቁጠረው? ለራሳችንም ነጻነትን አጥተን ለሌሎችም ነጻነት መፍትሔ ማምጣትን ትተን፣ ስለሌላው የሚጨሁትንም ወቅሰን ፣ተያይዝን በዝምታ ማለቅን የመረጥን ይመስላል፡፡ እነዚሁ ለፍትህ የሚጮሁ ሰዎች ግን ተሰፋ የቆረጡና የደከሙ ዕለት ግን ምን እንደሚኮን ያሳስበኛል፡፡

ምናልባትም ሌሎቻችን በስውር ለችግሩ መፍትሔ መፈለግና በዝምታ መስራትንም መርጠን እንደሆን ባላውቅም፣ መልካም ስራ ለመስራት፣ ወገንን በሰላማዊ መንገድ ለመታደግ ግን ሰው ራሱን መሰውር ያስፈልገዋል ብዬ በግሌ አላምንም፣ ባይሆን መልካም ስራ በመስራታችን እግዚአብሔርም ይከበርበታል እኛም በውጤቱ እንደሰታለን፣ ሌሎችም ይባረኩበታልና ነው፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ» ማቴዎስ 5;16 እንደሚል

እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም ስለማልፈልገው ሳየይሆን ስለማልችልበት ነው፣ ነገር ግን እንደ ወንጌል ሰራተኛ ለትውልድ መከራ ግድ ሊለኝ ይገባል ብዬ አምናለሁ፣ ወንጌል ማለት የምስራች ዜና ማለት ነው፣ የምስራች ደግሞ የምስራች የሚሆነው፣ ለተመቸው፣ ለደላው፣ ለተሳካለት፣ ለጻደቁ ሳይሆን፣ በችግር እና በመከራ ላይ ላለው፣ ጊዜ ላዘነበለበት፣ መከራህ ያመኛል፣ ስቃይህ ይሰማኛል፣ ብለን እኛ ራሳችንን ረጂ፣ ሌላውን ተረጂ አድርገን ዝቅ አድርገን በመመልከት ሳይሆን፣ መልካም ስራ ለመስራት እንደታደለ ሰው ደስ እያለን ለሌላው መድረስ ስንችል፣ የእኛንም የመከራ፣ የችግር፣ የስደት ጊዜ ወደ ሁዋላ መለስ ብለን ስናይ፣ ሌሎች በእኛም ችግር ጊዜ የታደጉንን ስናስብ ነው፡፡

ለትውልዳችን ፈውስ ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፣ ፈውስን ለመቀበል በሽታችንን ማለትም ችግራችንን በግልጽ መነጋገር አለብን ብዬ አምናለሁ፣ በሽታውን የደበቀ መድሐኒት አይገኝለትም የሚል አባባል አለና፣ አንዳችን መላ አምጪ፣ አንዳችን መላ ተቀባይ መሆን የለብንም፣ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ በመወጣት ለትውልዱ እና ለትውልድ ምድራችን ፈውስን ማቅረብ ይኖርብናል፣ መፍትሔ አለኝ የሚል ሁሉ በአንድ ልብ ልንረባረብበት የሚገባን ጊዜው አሁን ነው፣ ፖለቲከኛው በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚሰቱ በኢኮኖሚው፣ የማሐበራዊ ኑሮ ባለሙያው በሙያው፣ ሌላውም እንደችሎታው ቢያበረክት፣ የሰው እና የእውቅት ሁሉ ሀብት ክምችት ይዘን፣ ተበትነን ላለንበት ምድር ሁሉ እንኩዋን ተርፈን እያበለጸግን፣ ፈረንጆቹ ሶሺያል ካፒታል የሚሉት ነገር ነው መሰለኝ፣ የታመቀ ሐይል ይዘን፣ ዛሬም ለእኛው ችግር ከሌላው መፍትሔ ጠብቀን ዘወትር እርዳታን ከሌሎች የምንለምን ለማኞች ሆነን እስከመቼ እንዘልቃለን?

እኛስ ራሳችን የናቅንውን ማንነታችንን ፣ መከራና ችግራችንንስ ማን ይሸከምልናል፣ ኀያላን የምንላቸው አገሮች ራሳቻው፣ እኮ መላ የሚፈልጉላቸው በርካታ ኀያላን ችግሮች አሉባቸው፣ እኛም የዛሬን አያድርገው እንጂ ከታሪክ እንደምንሰማው ኀያላን ከሚባሉ የታረክ ቀደምት አገሮች አንዱ እንደነበርን ስንሰማ ኖረናል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው አካልም እኮ አልቻልኩበትም ብሎ በቃሉ አያረጋግጥልን እንጂ፣ ሁኔታዎች ሁሉ እኮ እንዳልቻለበት ያሳብቃሉና ችላ የሚባል ጉዳይ እይደለም፡፡

ቢያንስ እኛ መጻተኛ የሆንበት አገር ቢያስጠልነንም፣ ሕዝባችን እና ወገናችን ግን በዛች ምድር አለና ግድ ይለናል፣ ለበርካታ አመታት በስደት ሳንወድ በግድ የተለየናቸው ወገኖቻችን ሕንጻና ንብረት ባናፈራላቸውም፣ እኛ በልተን ስናድር እነርሱም ጦማቸውን እንዳያድሩ ስንል በመጠኑ የምንወረውርላቸው እርዳታ የእነርሱን ኑሮ ፈቀቅ ባያደርግም፣ለሐገሪቱ ግን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን አገሪቱዋን ስንገነባ ከርመናልና፣ ከምርጦቹ ዜጎች ተርታ ባንመደብም፣ የዛች አገር እጣ ፈንታ ያገባናል እና ዝም የምንልበት ጊዜ አይደለም፣ ለዚህ ሁሉ ስደት እና መከራ ምንጩ ያለው ከትውልድ አገራችን ነውና፣ ባእዳን አገሮችም ያምጡት፣ በሥልጣን ላይ ያለው አካል ያምጣው፣ እኛም እናምጣው፣ አንድ ነገር ላይ ግን መተማመን አለብን፣ የችግሩ ምንጭ መነሻው ትውልድ አገራችን ላይ ነውና ከምንጩ ለማድረቅ በችግሩ ወላፈን እሳት ላይ ያለውን ሕዝብ ለበለጠ መከራ እንዲጋፈጥ መግፋት ሳይሆን፣ እኛ በነጻነት ምድር ላይ ያለን ፣ በተለይም በተደላደለ ኑሮ ላይ ያለን ወገኖች በምንችለው ሁሉ መላ ለማምጣት በነጻነት መምከር ያስፈልገናል፡፡

እንዴት እንደምትሉኝ አልጠራጠርም፣ እኔ በግሌ ለእንዴታው መጠነኛ መልስ ይኖረኛል፣ አንተም እንዳለህ አምናለሁ፣ አንቺም እንዳለሽ አምናለሁ፣ እርስዎም እንዳልዎት አምናለሁ፣ ለችግሩ መፍትሔ ላይ ከመነጋገር እና ከመጣላታችን በፊት አስተሳሰቤን ሳይሆን እኔን እንደ እህት፣ አንተን እንደ ወንድም መቀባበል ስንችል፣ እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደ ሐይማኖተኛ፣ እንደ ጎሰኛ፣ አንደ…..ወዘተ ሳይሆን እንደ ሰው ተቀባብለን፣ ተከባብረን ፊት ለፊት መተያት ስንችል ነው፣ ፈውሳችን የሚጀምረው ብዬ አምናለሁ፡፡ቢያንስ በስደት ምድር የበለጠ ልንቀራረብ ሲገባን ተራራቅን፣ ጥቂት ጥሪት ያፈራን ሲመስለን፣ ጥቂት እውቀት የጨበጥን ሲመስለን ተናናቅን መሰል፣ ያችው ያለንን በፍቅር ተካፍለን የበላንባት የድህነት ዘመናችንን እስከሚያስናፍቅን ድረስ አድርሶናል፡፡

3

እንዳንንቀራረብ ባለፉት ሀያ አራት አመታት የተሰራው የቤት ስራ ይበቃል፣ ለምን ሁል ጊዜ የቤት ስራውን በሰጡን ሰዎች ወይም ቡድኖች ለ ላይ ብቻ እናላክካለን? እኛም ቤት ስራውን ለመስራት ወደንም ይሁን ተገደን ገብተንበታል፣ ከዛ ውስጥ መውጣቱን ግን እንደ ግዙፍ ተራራ አድርገን እንድናየው ሁኔታዎች ሁሉ አስገድደውናል ፣ በቅንንነት እና በመግባባት ከሰራን ግን ከእግዚአብሔር ጋር ተራራው ደልዳላ ሜዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡

አንዳንድ በውጭ አገር የምንኖር ሰዎች አገሪቱዋ ስላምና ብልጽግና ያጥለቀለቃት ናትና ችግር አለ ብላችሁ ለምን ታወራላችሁ? ለምን የተሰራውንስ በጎ ነገር አታወሩም? አለያ ችግሩን ለምን አገር ቤት ገብታችሁ አታቃልሉም? ብለን ስንወቅስ ይደመጣል፤ ችግሩን አቃልላለሁ፣ መንግሰትንም እረዳዋለሁ፣ አግዘዋለሁ፣ ብለው፣ የምእራቡን አለም ምቾት ጥለው የገቡ ሰዎች ላይ የደረሰውን መከራ ወይ ካለማወቅ፣ አለያም ለማወቅ እና ለመስማት ካለመፈለግ ነው መሰል፣ ልናምን አንፈልግም፣ ምናልባት ጥቂት የደላቸውን ሰዎች ጉዳይ ብቻ ምሳሌ ልንጠቀም እንሞክራለን፣ የእነርሱም ገደብ ታዛዥ እስከሆኑ ድረስ ነውና፡፡ከአገሩ ምድር በተለያየ ችግር ምክንያት አገር ለቆ ተሰዶ መጻተኛ ሆኖ ተዘልሎ በተቀመጠበት ባእድ አገርስ ምን እናደርጋለን? አገሪቱ አለምንም በደል እና መከራ የለማችና የመነጠቀች አገር ከሆነች፣ ለምን እዛ የለማው አገር ላይ ሄደን አንኖርም? ችግር ለመኖሩማ ዋነኛ ማሰረጃዎቹ ገነት ነው ተብሎ በተሰበከላት አገር መኖር አለመቻሉ ነው ሀቁ፡፡ ሁላችን በዘመናችን ሁሉ እንሳሳታለን፣ ተሳስተን ነበር ብሎ ማለትም ለራስም ለሌላውም ፈውስ እኮ ነው፣ ይልቁን ሆዳችን እያወቀ በትእቢት ከምንወጠር፣ ራሳችንን ለጥቂት ጊዜ ዝቅ አድርገን ለረጅም ጊዜ የሚሆን ከራስ እና ከወገን ጋር የታረቀ ማንነትን እና ከዛ ጋር የሚከተለውን ነጻነትንም መጎናጸፍ ፈውስ ነውና አቅምን እንለምን?

በተለይ የእምነት ሰዎች ስለ አገር እና ስለ ትውልድ መከራ ከተናገሩ ሰለ ሐይማኖታችሁ ብቻ ካልሆነ በቀር ሌላ ነገር አታውሩ፣ የትውልዱን ነገር አታንሱ፣ አሱንም ቢሆን ከቤተ እምነታችሁ ውጭ አትናገሩ ብለው ለመገደብ እና ለመገሰጽ ይሞከራል፡፡ ፖለቲከኞቹ ሁሉ ቦለቲካውን የሚያወሩለት እኮ ለእምነት ሰው ሁሉ ነው፣ የእነርሱን ሐሳብ፣ ሐይማኖተኛው እንዲሰማላቸው እንዲተባበራቸው ከፈለጉ፣ ሐይማኖተኛውስ ያለውን ሐሳብ ቢያካፍላቸው ላለመስማት የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ስለ እምነት መነጋገር፣ እግዚአብሔር የለም የሚለው ማርክሲዝም ሌኒንንዝም ስታሊንዝም ያደራጃቸው እና ያሰለጠናቸው ፖለቲከኞቻችን ያሳደሩብን ተጽዕኖ፣ ስለ እምነት ማንሳትን እንደነውር ወይም እንደ ኋላ ቀርነት ስለምናየው ይሆንን? ከእኛ በጣም ሰልጥነዋል የሚባሉት የሐያላን አገራት መሪዎች እንኩዋን የእግዚአብሔርን ስም ሲጠሩ አላፈሩም እና ግድ የለም አምላካችንን በሰውም ፊት አንካደው? ወንጀል የሚሆነው የተቀደሰ ሰሙን አለአግባብ ስንጠቀምበት ነው እና ከዛ ይሰውረን?

ሐይማኖተኞች ስለ አገር ግድ የላቸውም ብለው ሲያበቁ፣ ሐይማኖተኞች ወደ እነርሱ መንደር ሲመጡ፣ ቦለቲከኞቹ የእነርሱንም ሐሳብ ላለመስማት ጆሮአቸውን የማይከፍቱስ ለምንድን ነው ? አንዳችን ለሌላችን የግድ እንደምናስፈልግ መተማመን ላይ መድረሳችን ራሱ ፈውስ ነውና፣ በግድ የተጣለብንን ግድብ አጥር አፍርሰን፣ ወገኔ ትጠቅመኛለህ፣ ተጠቅሚኛለሽ እንባባል? በምድራችን በዘመናት ሁሉ እንዱ የሌላውን እምነት እያከበረ እና እየተከባበረ የኖረበትን ዘመን ኖሬበታለሁና እግዚአብሔር ያንን ፍቅር ሁሌም አይንፈገን?

እምነት አለን የምንል ሁሉ በተለይ ስለ ክርስትናው ያለኝ መጠነኛ እውቀት እንዳስተማረኝ እና እንደተረዳሁት፣ የእምነታችን ሠነድ በሆነው መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ ያለው ታሪክ ሁሉ የሚያስረዳን፣ እግዚአብሔር የጽድቅ እና ፍትህ አምላክ እንደሆነ፣ እግዚአብሔርን የሚያምኑ እና የሚያመልኩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰው አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ወንዶቹም ሆነ ሴቶቹ ፍትህ ሲጉዋደል ሲጮሁ፣ ነገስታትን ሲገስፁ፣ ለተበደለው ሕዝባቸው ሲሙዋገቱ፣ በነፍሳቸው እየተወራረዱ መላ ለማምጣት ሲጥሩ፣ በአገር ላይ መከራ ሲደርስ ለአገርም ለሕዝብም መብት መከበር ሲተጉ፣ በፀሎት እግዚአብሔርን ሲማፀኑ፣ የምድርንም ነገስታት ሕዝባችንን ታደጉልን? በሕዝባችን ላይ የታወጀውን የሞት አዋጅ አሽሩልን ? እያሉ እነርሱም እጆቻቸውን አጥፈው ሳይቀመጡ፣ እውቀታቸው እና ጉልበታቸው የፈቀደውን ያህል የሚችሉትን እያበረከቱ፣ ታሪክ ሲሰሩ ነው የተማርንው፡፡ ለዛውም ከእኛ የበለጠ እምነት ያላቸው የእምነት ምሳሌ የሆኑት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ታሪክ የሚያስተምረን፣ ታዲያ እኛ ላይ ሲደርስ ምን ነካን?

የእምነት ሰው የተለመደ የእምነት ሥርዐቶችን፣ ሰንበትን እየጠበቅን ከማከናወን ውጪ ሰለ አገሩ አያገባውም የሚል አደንዛዥ አባዜ፣ ከየት እንደመጣብን፣ እኛም ይህን አሜን ብለን ተቀብለን ስናስተናግድ መክረማችንን ወደ ሁዋላ መለስ ብዬ ሳየው፣ የሰው ልጅ ስለ አገሩ ወይም ስለ ወገኑ አያገባውም ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ ለማግኘት ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡ ከሁሉ የተለየው ደግሞ መንግስት የሚሰራው ስራ ትክክል ነው፣ የሚሉ አማኞች ይህን ሲናገሩት ፖለቲካ ነው ተብሎ አይፈረጅም፣ ሌሎች አማኞች ግን መንግሥት የሰራው ነገር ትክክል አይደለም ብለው ሲሉ እንዴት ፈጥኖ ፖለቲካ እንደሚሆን ነው ግራ የሚገባኝ? ወይ እኔ ያልገባኝ ከኔ መረዳት ያለፈ ስውር ነገር ይኖር ይሆን? እኔጃ ጌታ ግን ሁሉን ያውቃል፡፡ ሁኔታዎች ግን ሕሊና ላለው ሰው ዝም የሚያስብለበት ወቅት ላይ ያሉ አይመስልም፣ በተለይ እምነት አለን የምንል የየትኛውም እምነት ተከታዮች ብንሆን?

4

በእርግጥ ምድራችን የደም መሬት እየሆነች፣ ትውልዱዋም ለመከራ መጋለጡን ዘማሪዎችም በመዝሙራቸው፣

Mezmur Pastor Tamerat Haile #5 ́ ́ Akeldama ́ ́

ዘፋኞችም በዘፈናቸው New Gossaye Tesfaye Music: AKELDAMA for Ethiopias national mourning of Slaughtered Christians https://www.youtube.com/watch?v=CBkjDmug9rw

አኬልዳማ እያሉ ይገልጹታል፣ መልእከቱ ግን አንድ ነው፣ ለምድራችን የእግዚአብሔር እጅ ጣልቃ እንዲገባ የሚማፀን የሰቆቃ ድምፅ፣ ነገር ግን ከመልእክቱ ይልቅ መልእክቱን ያመጣው ሰው የእኛ ጎራ መንደር አባል ሰላልሆነ ብቻ፣ ከመልእክቱ ይልቅ በመልእክተኛው ላይ ስንረባረብ መልእክቱ እያመለጠን ተቸገርን እንጂ!

ሰለዚህ ሁላችንም በምንችለው አቅም እና እንደተሰጠን ጸጋ መጠን፣ በየቦታው በተግባር የምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለምድራችን ፈውስ እንዲመጣ መጸለይን በያለንበት የእምነት መረዳት ልክ፣ በአደባባይ ቢሆን በአንድ ልብ ሆነን፣ በጉዋዳም በእልፍኛችንም ደግሞ በስውር ለሚያየን አምላክ ማስተጋባትን አናቁዋርጥ? በግል የግላችንን ሐጢያት፣ በጋራ ደግሞ የምድራችንን ሐጢያት እና መተላለፍ ይቅር እንዲለን፣ በምህረቱም እንዲጎበኘን አምላካችንን ደጅ እንጠና፣ እግዚአብሔር በእርግጥ አንድ ቀን ዘንበል ይላል፡፡ “ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፣በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ

ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።ጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።1ኛ የዮሐንስ መልእክት» 1‹6-10 ይላል እና፡፡

ስለዚህ ለትውልድ እርቅ የሚመጣው ነገሮችን ሸፋፍነን የሌለውን አርቴፊሻል ሰላም እንዳለ በማስምሰል፣ የውሸት እየተሳሳምን፣ በልባችን ቅር እየተሰኘን፣ እየተሸነጋገልን፣ በአራዳው ቁዋንቁዋ እየተፎጋገርን፣ ቁስሉን በሚገባ ሳይሆን በጥቂቱ ብቻ እያከምን፣ ዘለቄታዊ ፈውስን የሚያመጣ መላ በጋራ ከመፈለግ ይልቅ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገረው “የሕዝቤንምስብራትበጥቂቱይፈውሳሉሰላምሳይሆን፦ሰላምሰላምይላሉ።«ኤርምያስ6‹14 እንደሚልጦርነት የተጀመረው ተኩስ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን፣ ሰው በልቡ ከተራራቀ እና ወንድም ወንድሙን መጥላት ከጀመረበት ሰአት ነውና፣ ትውልዳችን እርስ በእርስ መጠላላት ከጀመረም ከርሞአልና፣ ቤተሰብ ከቤሰተቡ፣ ጉዋደኛ ከባልንጀራው ጋር የማይተማመንበት ወቅት ላይ ደርሰን፣ እርስ በእርስ በጥርጣሬ አይን እየተያን፣ የደፈረሰውን ሠላም፣ እውነተኛ ሠላም እንዳለ አድርገን፣ በእውነት ላይ እየዋሸን፣ አንጻራዊ ሰላም አለ ብለን ለራሳችንም፣ ለእርስ በእርሳችንም ሳንወሻሽ፣ የትዕቢትን ነገር አስወግደን፣ እንዳችን ለሌላችን በማስመሰል ሳይሆን በእውነት ዝቅ የምንልበትን ጸጋ እንዲሰጠን እየለመንን፣ ልንሰማ ከማንፈልገው እና ከማይመቸንም እውነት ጋርም ቢሆን፣ ፊት ለፊት በመጋፈጥና ፣ ለራሳችን እና ለትውልዳችንም ፈውስ ለማምጣት በጋራ ለመቆም፣ ከምንግዜውም በላይ እጅ ለእጅ መያያዝ የሚገባን ጊዜ አሁን ነው፡፡ስለ ትውልዱስ ያገባናል ማለትስ የምንጀምረው ስንት ሚሊዮን ሕዝብ በአገር ውስም በውጪም እስኪያልቅ ድረስ ነው? ይህንንስ ስራ ለፖለቲከኞች ብቻ ተተቶ ሌላው ለእኛ ታግሎ ዋጋ እንዲከፍልልን የምንፈልገውሰ እስከ መቼስ ነው?

የሰው መከራ አያገባንም ስለሚሉ ሰዎች እንድ ቀን የክርስትና እምነታችን መሰረት የሆነው ጌታችን እና መድሐኒታችን ኢየሱሰ ክርሰቶሰ ሲናገር፣ «ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ፣ እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፣አንድ ሳምራዊግንሲሄድወደእርሱመጣአይቶትምአዘነለት፣ቀርቦምዘይትናየወይንጠጅበቍስሎቹላይአፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው፣እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል አለው፣እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለትአለ።ኢየሱስም፦ሂድአንተምእንዲሁአድርግአለው።» የሉቃስወንጌል10‹30-37

ዛሬ በዘመናችን የሰው መከራና ችግር የሚከብዳቸው እና የሚያስጨንቃቸው ሰዎች፣ መንፈሳዊ ነን ያሉ ሰዎች የሚንቁዋቸው እና አለማውያን ብለው የተፀየፉዋቸው ናቸው፣ እነእርሱም ፖለቲከኛ፣ አመጸኛ፣ ተብለው ተፈርጀው፣ እያደረጉ ላሉት የሰው ልጅ መበት መከራከር፣ ምስጋናው ቢቀርባቸው እንኩዋን ሊወቀሱ አይገባም ነበር፣ ሁላችን ሌላው በሚሰራው ስራ ላይ ከመፍረድ ታቅበን፣ ሰማይም ምድርም እንደ አንድ ዜጋ የምትጠብቅብንን መልካም ስራ እምነት ስላለን ወይም ስለሌለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን መልካም ስራ ለመስራት እንድንተጋ፣ እግዚአብሔርም ፀጋውን ያብዛልን፣ ምህረትንም ለእኛም ለምድራችንም ያምጣልን አሜን፡፡

ለዛሬ ከላይ ያለውን የአኬልዳማ ዜማ መልእክት እየጋበዝኮት ለሚቀጠለው ጊዜ ችር ይግጠምን በማለት የምሰናበትዎ ትውልደ ኢተዮጵያዊት እናት ከሰሜን ዋልታ ስር ካለች የገጠር መንደር ነው፡፡

ከማክበር ሰላምታ ጋር
ሰዋስው ስለሺ ዮሐነሰን
The Ark of the New Covenant Healing Ministry www.adonairapha.org
[email protected]

 

 

 

 

 

 

 

 

______________________________________________